Popular Posts

Friday, July 7, 2017

ፍቅር እና ራስ ወዳድነት

አለምን የሚመሩት የፍቅርና ራስ ወዳድነት ምክኒያቶች ናቸው፡፡ በህይወት የተሳካለት ለመሆን የፍቅርንና የራስ ወዳድነትን ልዩነት መረዳት በጣም ወሳኝ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ፍቅርን በትክክል ስለማይረዱ ራስ ወዳድነትን ፍቅር ያደርጉታል፡፡ ራስ ወዳድነትና ፍቅር የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ስለፍቅርና ስለራስ ወዳድነት ለመረዳት ፍቅርና ራስ ወዳድነት ስለባህሪያቸው መረዳት ወሳኝ ነው፡፡
ፍቅር ሙሉ ነው ራስ ወዳድነት ግን ጎዶሎ ነው
ፍቅር የተቀበለ ፣ የረካና የሞላለት ነው፡፡ መውደድ ፣ መስጠትና ማካፈል የሚችለው ሙሉ የሆነ ሰው ነው፡፡ ጎዶሎ የሆነ ሰው ከሌላው ይጠብቃል እንጂ መስጠትን አያውቅም፡፡ ሙሉ የሆነ ሰው ሊሰጥና ሊያካፍል የተዘጋጀ ነው፡፡ ራስ ወዳድነት ግን የለኝም ይጎድለኛል ከሚል የምስኪንነት አስተሳሰብ ይመነጫል፡፡ 
እኔ እንደ ማርሁህ ባልንጀራህ የሆነውን ያን ባሪያ ልትምረው ለአንተስ አይገባህምን? አለው። ማቴዎስ 18፡33
ፍቅር ድፍረት አለው ራስ ወዳድነት ፈሪ ነው
ፍቅር ብሰጥም አይጎድለኝም ብሎ ያስባል፡፡ ፍቅር ብሰጥም ይሰጠኛል ብሎ ያምናል፡፡ ራስ ወዳድነት ግን ብለቀው አጣዋለሁ ብሎ በስጋት ይኖራል፡፡
ስጡ ይሰጣችሁማል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ተመልሶ ይሰፈርላችኋልና፥ የተጨቈነና የተነቀነቀ የተትረፈረፈም መልካም መስፈሪያ በእቅፋችሁ ይሰጣችኋል። ሉቃስ 6፡38
ፍቅር ትሁት ነው ራስ ወዳድ ግን ትእቢተኛ ነው
ፍቅር ሌላው ከእርሱ እንደሚሻል ያስባል፡፡ ራስ ወዳድነት እርሱ ከሁሉ እንደሚሻል ያስባል፡፡ ፍቅር ሌሎችን ለማገልገል እንደተፈጠረ እድለኛ ሰው ሲመለከት ራስ ወዳድነት ግን ሌሎች እርሱን እንዲያገለግሉት የተፈጠሩ መጠቀሚያዎች አድርጎ በትእቢት ያስባል፡፡
ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር፤ ፊልጵስዩስ 2፡3-4
ፍቅር አገልጋይ ነው ራስ ወዳድነት ተጠቃሚ ነው
ፍቅር ሌሎችን እንዲያገለግል እንደተፈጠረ ያውቃል፡፡ ራስ ወዳድነት ግን ሰው እርሱን እንዲያገለግለው ይፈልጋል፡፡ የፍቅር ሰው ሌሎችን የሚባርክ መልካም ነገር በእርሱ እንዳለ ያውቃል፡፡ ያንን መልካም ነገር ካለስስት ለሌሎች ይሰጣል፡፡ ራስ ወዳድነት  በእርሱ ያለውን ለሌሎች የሚጠቅመውን በጎነት አያየም፡፡ ራስ ወዳድነት የእርሱ በጎነት በሌሎች እንደተያዘ ይመስለዋል፡
ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የእናንተ ባሪያ ይሁን፤ ማቴዎስ 20፡27
ፍቅር ደስተኛ ነው ራስ ወዳድ ሃዘንተኛ ነው
ፍቅር የሚቀናበት ሙሉ ነው፡፡ ራስ ወዳድነት የሚታዘንለት መከረኛ እና ሃዘንተኛ ነው፡፡ ፍቅር ደስ የሚሰኘው በማይለወጠው በእግዚአብሄር ስለሆነ ሁሌ ደስተኛ ነው፡፡ ራስ ወዳድነት ደስ የሚሰኘው በቁሳቁስ ስለሆነ ደስታው ተለዋዋጭ ነው፡፡
ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፥ ደስ ይበላችሁ። ፊልጵስዩስ 4፡4
ፍቅር ለመኖር ብዙ አያስፈልገውም ራስ ወዳድነት ምንም ነገር አይበቃውም
ፍቅር ባለው ነገር ይረካል ባለው በነገር ሌሎችን ያገለግላል፡፡ ፍቅር ባለው ነገር እንዴት እንደሚኖር ያውቃል፡፡ ለራስ ወዳድነት ለእርሱ ምንም ነገር በቂ አይደለም፡፡ ፍቅር የተባረከበትን በረከት ያያል ፣ ያከብራል እውቅናም ይሰጣል፡፡ ራስ ወዳድነት የጎደለውና የሌለው ላይ ነገር ላይ ብቻ ያተኩራል፡፡ 
ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡6
ፍቅር በእርሱ ዘንድ ያለው ለሌሎች ሰዎች እንደሆነ ራስ ወዳድነት ደግሞ በሌሎች ውስጥ ያለው ለእርሱ እንደሆነ ያምናል
ፍቅር ለሌሎች የሚጠቅም ሌሎችን የሚያነሳ ሌሎችን የሚያሻግር ስጦታዎች በእርሱ እንዳለ ያምናል፡፡ ፍቅር በሌሎች ላይ ዋጋን ለመጨመር ፣ ሌሎችን ለማነፅ ፣ ሌሎችን ለመገንባት ፣ ሌሎችን ለማፅናናት እና ለማፅናት ተግቶ ይሰራል፡፡ ራስ ወዳድነት ሌሎች ካልረዱኝ ፣ ሌሎች ካልሰጡኝ ፣ ሌሎች ካላሰቡኝ ዋጋ የለኝም ብሎ ያስባል፡፡ ፍቅር ለሌሎች የሚጠቅም ነገር በእርሱ እንዳለ ሲያምን ራስ ወዳድነት ግን ምስኪንነት አስተሳሰብ ያለው ከመሆኑ የተነሳ እጅግ ሃብታም ካልሆነ ከታላቅ ከውርደቴ ሊያነሳኝ አይችልም ብሎ ያስባል፡፡
ልዩ ልዩን የእግዚአብሔርን ጸጋ ደጋግ መጋቢዎች እንደ መሆናችሁ፥ እያንዳንዳችሁ የጸጋን ስጦታ እንደ ተቀበላችሁ መጠን በዚያው ጸጋ እርስ በርሳችሁ አገልግሉ፤ 1ኛ ጴጥሮስ 4፡10
ፍቅር በሌለው ያምናል ራስ ወዳድነት ራሱ ብቻ የምናል
ፍቅር ሌላው እንደሚነሳ ፣ እንደሚሄድ ፣ እንደሚሳካና እንደሚከናወን ያምናል፡፡ ፍቅር ሌላውን ስለሚያምን የሌላው መሳካት የእርሱ መሳካት እንደሆነ ይቆጥራል፡፡ ራስ ወዳድነት ግን ከእርሱ ውጭ ማን እንዳማይሳካለት ፣ ማንም እንደማይከናወንለትና ማንም እንደማይወጣ ስለሚያስብ በሌላው ላይ መዝራት ብክነት ይመስለዋል፡፡
ሁሉን ይታገሣል፥ ሁሉን ያምናል ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፥ በሁሉ ይጸናል። 1ኛ ቆሮንቶስ 13፡7
ፍቅር ኩሩ ነው ራስ ወዳድነት ስግብግብ ነው
ፍቅር አስቀድሞ የረካ ስለሆነ ቢጠቅሙትም እንኳን የማያደርጋቸው ነገሮች አሉ፡፡ ፍቅር የሚንቀው ጥቅም አለ፡፡ ራስ ወዳድነት ግን ጥቅም ሆነ የሆነውን ሁሉ ነው የሚውጠው፡፡
ነውረኛ ረብ የማይወዱ፥ በንጹሕ ሕሊና የሃይማኖትን ምሥጢር የሚይዙ ሊሆኑ ይገባቸዋል። 1ኛ ጢሞቴዎስ 3፡9
ፍቅር ክብሩን ያውቃል ራስ ወዳድነት መዋረዱን ያያል
ፍቅር እንደከበረ ያውቃል፡፡ ፍቅር ከዚህ በላይ ሊከብረው የሚችል ምንም ነገር እንደሌለ ያውቃል፡፡ ራስ ወዳድነት ግን የሚታየው መዋረዱ ነው፡፡ እንዴት ከውርደቱ እንደሚወጣ ሌት ተቀን ያቅዳል ያልማል፡፡
ፍቅር ሌት ተቀን የሚያስበውና የሚያተኩረው እርሱ በሚሰጠው በሚባርከው በሚጠቅመውንና በሚያካፍለው ላይ ነው፡፡ ራስ ወዳድነት ሌት ተቀን የሚያስበውና የሚያተኩረው ለእርሱ በሚያገኘው በሚጠቀመውና በሚተርፈው ነገር ላይ ነው፡፡ ፍቅር ሰውን የሚፈልገው ለሰውየው ጥቅም ነው፡፡ ራስ ወዳድነት ሰውን እንኳን እወድሃለሁ የሚለው የሚጠቀመው ነገር እስካለ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ፍቅር ግን ሌላው ሲደክም ያን ጊዜ ነው ይበልጥ እንደሚያስፈልግ የሚረዳው፡፡
. . . ያመንሁትን አውቃለሁና፥ የሰጠሁትንም አደራ እስከዚያ ቀን ድረስ ሊጠብቅ እንዲችል ተረድቼአለሁ። 2ኛ ጢሞቴዎስ 1፡12
ፍቅር ማንነቱን ያውቃል ራስ ወዳድነት ማንነቱን አያውቅም
ፍቅር ማን እንደሆነ ስለሚረዳ ለመውደድ ለማካፈል ለማንሳት ለመበረክ አይከብደውም፡፡ ራስ ወዳድነት ስለራሱ እርግጠኛ ስላይደለ መውደድ ለሌች መፍሰስ አይችልም፡፡
ኢየሱስ አብ ሁሉን በልጁ እንደ ሰጠው ከእግዚአብሔርም እንደ ወጣ ወደ እግዚአብሔርም እንዲሄድ አውቆ፥ ከእራት ተነሣ ልብሱንም አኖረ፥ ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ፤ በኋላም በመታጠቢያው ውኃ ጨመረ፥ የደቀ መዛሙርቱንም እግር ሊያጥብና በታጠቀበትም ማበሻ ጨርቅ ሊያብስ ጀመረ። ዮሃንስ 133-4
ፍቅር ይተጋል ራስ ወዳድነት ይመኛል
ፍቅር እውነታን ይቀበላል፡፡ ካለበት ተነስቶ ይተጋል፡፡ ራስ ወዳድነት ግን በእድል ብቻ ያምናል፡፡ ሁሌ ይመኛል ይፈልጋል፡፡
ኀጥእ ቀኑን ሁሉ ምኞትን ይመኛል፤ ጻድቅ ግን ይሰጣል፥ አይሰስትም። ምሳሌ 21፡26  
ፍቅር ደፋር ነው ራስ ወዳድነት ግን ፈሪ ነው
ፍቅር ድፍረት አለው፡፡ ፍቅር ብሰጥም አይጎድልብኝም የሚል መተማመን አለው፡፡ ራስ ወዳድነት ግን ከፍርሃት ይመነጫል፡፡ ራስ ወዳድነት ይጎድልብኛል አጣለሁ ከሚል የፍርሃት ስሜት ይመነጫል፡፡
የሚበልጥና ለዘወትር የሚኖር ገንዘብ በሰማይ ራሳችሁ እንዳላችሁ አውቃችሁ፥ በእስራቴ ራራችሁልኝ የገንዘባችሁንም ንጥቂያ በደስታ ተቀበላችሁ። እንግዲህ ታላቅ ብድራት ያለውን ድፍረታችሁን አትጣሉ። ዕብራውያን 10፡34-35
ፍቅር ባለጠጋ ነው ራስ ወዳድነት ደሃ ነው
ፍቅር የሞላለት ነው፡፡ ፍቅር የረካ ነው፡፡ ራስ ወዳድነት ግን የተራበ ነው፡፡ ራስ ወዳድነት የእጦት የጉድለት የድህነት ምልክት ነው፡፡
የምትባረክ ነፍስ ትጠግባለች፥ የረካም እርሱ ደግሞ ይረካል። ምሳሌ 11፥25
ፍቅር ሰጪ ነው ራስ ወዳድነት ንፉግ ነው
ፍቅር የሚታወቀው በመስጠት ነው፡፡ ፍቅር የሚታወቀው በማካፈል ነው፡፡ ራስ ወዳድነት የሚታወቀው በመቀበል በማስወጣት በመበዝበዝ ነው፡፡ ፍቅር ሰጪ ሲሆን ራስ ወዳድነት ግን ጠባቂ ነው፡፡ ፍቅር ሲያካፍል ራስ ወዳድነት ግን የተራበ ጠባቂ ብቻ ነው፡፡ ፍቅር ሰዎችን ፍቅር በመስጠት በማስተላለፍ በመጠቀም ይረካል፡፡ ራስ ወዳድነት ግን በመሰብሰብ በማከማቸት በማጋበስ ይረካል፡፡ ፍቅር ሌሎችን በማንሳት በሌሎች ላይ ዋጋን በመጨመር ይረካል፡፡ ራስ ወዳድነት ራሱ ላይ ብቻ በማከማቸት ይረካል፡፡  ፍቅር ራሱን በሌሎች ያበዛል፡፡ ራስ ወዳድነት ግን ከራሱ ጋር ይሞታል፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ፍቅር #መውደድ #ምስኪንእኔ #ድፍረት #መስጠት #ማካፈል #ሙላት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #ቸርነት #ትግስት #ፍርሃት #መታበይ #ራስወዳድነት #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment