Popular Posts

Sunday, July 23, 2017

የመንግስቱ ኢኮኖሚ - ገንዘብን መጠቀም

በህይወት ለመሳካት ጥበብ ያስፈልገናል፡፡ ገንዘብን እንዴት እንደምናገኝ እንደምንጠቀምና እንደምንሰጥ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ገንዘብን በአግባቡ ለመያዝ ጥበብ በበዛልን መጠን ገንዘባችንን በትክክል መጠቀም እንችላለን፡፡  
በወርቅና በብር ከመነገድ ይልቅ በእርስዋ መነገድ ይሻላልና። ምሳሌ 3፡14
በእጃችን ያለውን ገንዘብ ለመጠቀም የሚበላውን መብልና የሚዘራውን ዘር መለየት ወሳኝ ነው፡፡
እግዚአብሄር የሚሰጠን የሚበላም ነው የሚዘራም ነው፡፡ እግዚአብሄር የሚሰጠን ሁሉ የሚበላ አይደለም እንዲሁንም እግዚአብሄር የሚሰጠን ሁሉ የሚዘራ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር የሚሰጠን የምንጠቀምበትና የምንሰጠው ነው፡፡ ገንዘብን ግን እንዴት እንደምንጠቀም ካወቅን ገንዘብን የተቀበልንበትን አላማ መፈፀም ያስችለናል፡፡
ለዘሪ ዘርን ለመብላትም እንጀራን በብዙ የሚሰጥ እርሱም የምትዘሩትን ዘር ይሰጣችኋል ያበረክትላችሁማል፥ የጽድቃችሁንም ፍሬ ያሳድጋል፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 9፡10
ገንዘብን በሚገባ ለመለየት መሰረታዊ ፍላጎትንና ቅንጦትን መለየት ወሳኝ ነው፡፡ እግዚአብሄር እንድንጠቀም የሚፈልገው መሰረታዊ ፍላጎታችንን ብቻ ነው፡፡ ከመሰረታዊ ፍላጎታችን በላይ ያለውን ወይ እንድንሰጠው ወይም መልሰን ኢንቨስት እንድናደርገው ነው የሚፈልገው፡፡ እግዚአብሄር ቃል የገባው የሚያስፈልገንን እንደሚያሟላ ነው፡፡ ከሚያስፈልገን በላይ ከተጠቀምን ወይ ወደፊት እንደገና ኢንቨስት ማድረግ ካለብን ላይ ነው ወይም ደግሞ ለሌላ መስጠት ካለብን ላይ ነው፡፡
ገንዘብን ስለመጠቀም ስናስብ በገቢ መጠን መኖርን ይጠይቃል፡፡ ገንዘብ ውስን ነው፡፡ ውስን ያልሆነ ገንዘብ ያለው ሰው በምድር ላይ የለም፡፡ ከቢሊየነሩ እስከመጨረሻው ሰው ያለው ገንዘብ ውስንና ካልታቀደበት ባክኖ የሚያልቅ ነው፡፡ ሰው ያለው ገንዘብ ውስን በመሆኑ በእቅድ ገንዘቡን ሊያወጣ ይገባዋል፡፡ በእቅድና በበጀት መሰረታዊ ፍላጎትን ቅድሚያ በመስጠት ያልወጣ ገንዘብ ይባክናል፡፡
አንዳንድ ሰው ብዙ ገንዘብ የሚፈልገው መሰረታዊ ፍላጎቱን ስለማይለይ እንጂ አጥቶ አይደለም፡፡ መሰረታዊ ፍላጎታችን ምን እንደሆነ መለየት ያሳርፈናል፡፡
አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል። 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡8
መጠቀም ያለብን ገንዘብ ያለንን ገንዘብ ብቻ ነው፡፡ ያለውን ገንዘብ ብቻ የማይጠቀም ሰው ከሌላው ይበደራል፡፡ ብድር ደግሞ በጊዜ እስካልተመለሰ ድረስ እዳ ነው፡፡ ብድር ሰውን ነፃ አያደርግም፡፡ ስለዚህ ሰው ነፃ መሆን ከፈገለገ ባለው ገቢ መጠን ብቻ መኖር መማር ራሱን ማስለመድ ይኖርበታል፡፡
ባለጠጋ ድሆችን ይገዛል፥ ተበዳሪም የአበዳሪ ባሪያ ነው። ምሳሌ 22፡7
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ብልፅግና #የብልፅግናወንጌል #ስራ #ትጋት #በረከት #ስኬት #ስምረት #መሰረታዊፍላጎት #ጥበብ #ሁሉየእናንተነውና #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #የተትረፈረፈህይወት #መፅሃፍቅዱስ #መድከም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment