Popular Posts

Sunday, July 9, 2017

ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል

እግዚአብሔር፥ ሁልጊዜ በነገር ሁሉ ብቃትን ሁሉ አግኝታችሁ ለበጎ ሥራ ሁሉ ትበዙ ዘንድ፥ ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል። 2ኛ ቆሮንቶስ 9፡9
እግዚአብሄር ሙሉ ነው፡፡ እኛ የኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝነት የተቀበልን ሁላችን የእግዚአብሄር ልጆች ነን፡፡ እግዚአብሄር በነገር ሁሉ ሙሉ እንደሆነ ሁሉ በነገር ሁሉ ሙሉ ሊያደርገን ይችላል፡፡
ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ ዮሃንስ 1፡14
ሁልጊዜ
እግዚአብሄር ሁል ጊዜ ከእኛ ጋር ነው፡፡ እኛ እንኳን ንቁ ባልሆንበት ጊዜ እግዚአብሄር ግን ሁል ጊዜ ከእኛ ጋር ነው፡፡ እግዚአብሄር እንደሰው አይተኛም አያንቀላፋም፡፡ እግዚአብሄር ሁልጊዜ በስራ ላይ ነው፡፡  
ኢየሱስ ግን፦ አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ ብሎ መለሰላቸው። ዮሃንስ 5፡17
በነገር ሁሉ
እግዚአብሄር ስለዝርዝር ጉዳያችን ግድ ይለዋል፡፡ እኛ አንኳን አንዳንድ ጊዜ ስለምንረሳው ጥቃቅን ጉዳያችን እግዚአብሄር ግድ ይለዋል፡፡ እግዚአብሄር በነገር ሁሉ የተሳካለት ስለሆነ እኛ ልጆቹ በነገር ሁሉ እንዲሳካልን ይፈልጋል፡፡ በህይወታችን ስላለው ስለእያንዳንዱ ሃላፊነት ሁሉ ጌታ ግድ ይለዋል፡፡ ይህ አይመለከተኝም የሚለው ነገር የለም፡፡ እግዚአብሄር በነገር ሁሉ ብቃትን ሊያበዛልን ይችላል፡፡
አምስት ድንቢጦች በአሥር ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱም አንዲቱ ስንኳ በእግዚአብሔር ፊት አትረሳም። ነገር ግን የእናንተ የራሳችሁ ጠጕር ሁሉ እንኳ የተቈጠረ ነው፤ እንግዲያስ አትፍሩ ከብዙ ድንቢጦች ትበልጣላችሁ። ሉቃስ 12፡6-7
ብቃትን ሁሉ
ህይወት ብዙ ጥያቄዎች አሉት፡፡ ህይወት አንድ መልስ የለውም፡፡ የተለያየ የህይወት አቅጣጫ የተለያየ መልስ ይፈልጋል፡፡ እያንዳንዱ የህይወት ሃላፊነት ሃይልና ጥበብ ይጠይቃል፡፡ እግዚአብሄር ደግሞ የትኛው ጥያቄ በሃይል የትኛው ጥያቄ ደግሞ በጥበብ እንደሚመለስ ያውቃል፡፡ እግዚአብሄርም በምድር ላይ አላማውን በሚገባ እንፈፅም ዘንድ ብቃትን ሁሉ ሊሰጠን ይችላል፡፡
ብዙ ልዩ ልዩ የእግዚአብሔር ጥበብ አሁን በቤተ ክርስቲያን በኩል በሰማያዊ ስፍራ ውስጥ ላሉት አለቆችና ሥልጣናት ትታወቅ ዘንድ፤ ኤፌሶን 3፡10
ለበጎ ስራ ሁሉ
እግዚአብሄር እንድንሰራው ያዘጋጀውን መልካም ስራ ሁሉ መፈፀም እንችላለን፡፡ እግዚአብሄር ወደምድር ያመጣን ስራውን ለመፈፀም የሚያስችልን ሃይል አዘጋጅቶ ነው ፡፡ በምድር ስንኖር እግዚአብሄር ካዘጋጀልን በጎ ስራ አንጎድልም፡፡ ለበጎ ስራ ሁሉ የሚያስፈልገው ብቃት በእኛ ውስጥ አለ፡፡ በጎ ስራ ከሆነ ልንፈፅመው እንችላለን፡፡ እግዚአብሄር ላዘጋጀው በምድር ላይ ሰርተን ለምናልፈው በጎ ስራ ሁሉ ብቃቱ አለን፡፡
እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን። ኤፌሶን 2፡10
ፀጋን ሁሉ
ፀጋ የሚያስችል ሃይል ነው፡፡ ካለሃይል ምንም ነገር ማድረግ አይቻልም፡፡ በሃይል ደግሞ ማድረግ የማይቻል ምንም ነገር የለም፡፡ በፀጋ ሁሉም ይቻላል፡፡ በእግዚአብሄር የሚያስችል ሃይል ሁለም ይከናወናል፡፡ በእግዚአብሄር ፀጋ ሁሉ ይሳካል፡፡
በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ ራሱ ፍጹማን ያደርጋችኋል ያጸናችሁማል ያበረታችሁማል። 1ኛ ጴጥሮስ 5፡10
እግዚአብሔር፥ ሁልጊዜ በነገር ሁሉ ብቃትን ሁሉ አግኝታችሁ ለበጎ ሥራ ሁሉ ትበዙ ዘንድ፥ ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል። 2ኛ ቆሮንቶስ 9፡9
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መሪ #ፀጋ #የሚያስችልሃይል #እውቀት #ምስጋና #ሁልጊዜ #ልብ #በነገርሁሉ #ብቃትንሁሉ #ለበጎስራሁሉ #ፀጋንሁሉ #እምነት #ፀሎት #ማማጠን #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment