Popular Posts

Tuesday, July 4, 2017

መንፈስ ቅዱስ በእኛ

ክርስትና ስርአትንና ወግን የምንፈፅምበት ባዶ ሃይማኖት አይደለም፡፡ ክርስትና በምድር እግዚአብሔርን መስሎ የመኖር ህይወት ነው፡፡ ክርስትና ሁለንተናን ለእግዚአብሔር መንግስት መስጠት ነው፡፡ ክርስትና በሁለንተና ጌታ ክርስቶስን መከተል ነው፡፡ ክርስትና ኢየሱስ ያዘዘውን ሁሉ በመፈፀም እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት ነው፡፡ ክርስትና እግዚአብሔርን በመታዘዝ የተፈጠርንበትን አላማ ማሳካት ነው፡፡
ይህ ከፍ ያለ የክርስትና የህይወት ደረጃ ወግና ስርአትን በመፈፀም ብቻ የሚገኝ አይደለም፡፡ ይህ ከፍ ያለ የክርስትና የኑሮ ደረጃ የእግዚአብሔርን ሃይል ይጠይቃል፡፡ ካለ እግዚአብሔር ሃይል ይህ ደረጃ የማይታሰብ ከፍ ያለ የህይወት ደረጃ ነው፡፡
ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሰራልንን ስራ የተቀበልብን ሁላችን የእግዚአብሔር ልጆች ሆነናል የእግዚአብሔር መንፈስ በውስጣችን ይኖራል፡፡ ክርስትናን ከሌሎች ሃይማኖቶች ልዩ የሚያደርገው ክርስቶስ በተከታዮቹ ውስጥ መኖሩ ነው፡፡ ጌተራ ኢየሱስን አዳኛችን ያደረግን ሁላችን የእግዚአብሔር ልጅነት ስልጣንን አግኝተናል፡፡ የእግዚአብሔር ልጅነትን ደረጃ ለመኖር የሚያስፈልገን ሃይል ሁሉ ተሰጥቶናል፡፡
ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ ዮሃንስ 1፡12
በክርስትና የእግዚአብሔር ልጆች ሆነን እንድኖር ብቁ የሚያደርገን የእግዚአብሔር መንፈስ በውሰጣችን ስለሚኖር ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ስራ የምንሰራው በራሳችን ይል አይደለም፡፡ እግዚአብሔርን መስለን የምንኖረው በሰው ጉልበት አይደለም፡፡ የእግዚአብሔር ልጅነትን የህይወት ደረጃ የምናሟላው በውስጣችን በሚኖረው በእግዚአብሔር መንፈስ ነው፡፡
በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ፤ ወይስ ምናልባት የማትበቁ ባትሆኑ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ እንዳለ ስለ እናንተ አታውቁምን? 2ኛ ቆሮንቶስ 13፡5
መንፈስ ቅዱስ በእኛ ውስጥ ይኖራል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ወደ እውነት ሁሉ ሊመራን በውስጣችን ይኖራል፡፡ መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ቃል እንድንኖር ሊያግዘን በልባችን ይኖራል፡፡
ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ። ዮሃንስ 14፡15-17
የእግዚአብሔርን ልጅነትን የህይወት ደረጃ የምናሟላው በእግዚአብሔርን መንፈስ ረዳትነት ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሔር በልቡና በነፍሱ እንዳለ የምንኖረው በውስጣችን ባደረው በእግዚአብሔር መንፈስ ምሪት ነው፡፡
እናንተስ ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ይኖራል፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም፤ ነገር ግን የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራችሁ፥ እውነተኛም እንደ ሆነ ውሸትም እንዳልሆነ፥ እናንተንም እንዳስተማራችሁ፥ በእርሱ ኑሩ። 1ኛ ዮሐንስ 2፡27
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #የመንፈስፍሬ #ቅባት #መንፈስቅዱስ #የእግዚአብሔርመንፈስ #መሪ #ቤተመቅደስ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #የእግዚአብሔርህይወት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment