Popular Posts

Thursday, August 25, 2016

የእውነተኛ አርነት ጥሪ!

እንግዲህ ልጁ አርነት ቢያወጣችሁ በእውነት አርነት ትወጣላችሁ። ዮሃንስ 8፡36
የትኛውንም ባርነት ለሰው ልጅ አልተሰራም፡፡ሰው የራሱ ፈቃድ ያለው ተደርጎ ስለታቀደና ስለተሰራ ከፍጥረቱ ጋር ስለማይሄድ ሰው ባርነት አይመቸውም፡፡ የተለያየ አይነት ባርነት እንዳለ የተለያየ አይነት ነፃነት አለ፡፡ ነፃነት ሁሉ ግን ይጣፍጣል፡፡
በምድር ላይ ብዙ አይነት የባርነት ደረጃዎች እንዳሉ ብዙ አይነት የነፃነት ደረጃዎች ይገኛሉ፡፡ እንደ ባርነቱ ክብደት ነፃነቱም እንደዚያው ነው የሚያስደስተው፡፡
ለምሳሌ ተበዳሪም የአበዳሪ ባሪያ እንደሆነና ተበዳሪ ነፃነቱን በተወሰነ መልኩ ለአበዳሪው እንደሚሰጥ መፅሃፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡
ባለጠጋ ድሆችን ይገዛል፥ ተበዳሪም የአበዳሪ ባሪያ ነው። ምሳሌ 22:7
ሰው ለእግዚአብሄር እየተገዛ የእግዚአብሄርን ፈቃድ በምድር ላይ ሊያስፈፅም ነው የተላከው፡፡ ሰው ግን ለእግዚአብሄር አልገዛም ሲልና በእግዚአብሄር ላይ ሲያምፅ እጅግ ክፉ ባርነት ውስጥ ወደቀ፡፡
የሃጢያት ባርነት ከባርነቶች ሁሉ ባርነት ነው፡፡ የኃጢአት ባሪያዎች ሳላችሁ ከጽድቅ ነፃ ነበራችሁና። ሮሜ 6፡20
ለመታዘዝ ባሪያዎች እንድትሆኑ ራሳችሁን ለምታቀርቡለት፥ ለእርሱ ለምትታዘዙለት ባሪያዎች እንደ ሆናችሁ አታውቁምን? ሮሜ 6፡16
የሰይጣን አላማ መግደልና መስረቅ ማረድ ነው፡፡
ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤ ዮሃንስ 10፡10
አላማው መስረቅ ማረድና ማጥፋት ብቻ በሆነው በሰይጣን ባርነት አገዛዝ ውስጥ መውደቅ እጅግ የከፋው ባርነት ነው፡፡ በምድር ላይ መድሃኒት በማይገኝለት በሃጢያት በሽታ መያዝ ከባርነቶች በላይ ባርነት ነው፡፡ ስለዚህ ነው ስጋችን ከተለያየ ጭቆና ነፃ ለመውጣት እንደሚፈልግ ነፍሳችን ከሃጢያት ባርነት ነፃ መውጣት ፈልጋ ትጮኻለች፡፡
ሰው ከሌላ ከምንም ባርነት ነፃ ቢወጣም ከሃጢያት ባርነት ነፃ ካልወጣ በእውነት ነፃ አይደለም፡፡
በምድር ላይ ከባርነቶች ሁሉ የከፋው ባርነት የሃጢያት ባርነት ነው፡፡ ሰው በምድር ላይ ከሁሉ ነፃ ወጥቶ በሃጢያት ባርነት ምክኒያት ለዘላለም ግን ከእግዚአብሄር ከተለየ ምን ይጠቅመዋል?
እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ። ዮሃንስ 10፡10
ሰው እግዚአብሄር ባዘጋጀው የመዳኛ መንገድ በእየሱስ ካመነና እየሱስን እንደጌታውና እንደአዳኙ ከተቀበለ እውነተኛ አርነትን ያገኛል፡፡ እንግዲህ ልጁ አርነት ቢያወጣችሁ በእውነት አርነት ትወጣላችሁ። ዮሃንስ 8፡36
#ነፃነት #ፍቅር #ምህረት #ይቅርታ #አርነት #ሐጢያት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #የዘላለምህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment