Popular Posts

Friday, August 12, 2016

ሁላችንም ሯጮች ነን

በእሽቅድምድም ስፍራ የሚሮጡት፥ ሁሉ እንዲሮጡ ነገር ግን አንዱ ብቻ ዋጋውን እንዲቀበል አታውቁምን? እንዲሁም ታገኙ ዘንድ ሩጡ። የሚታገልም ሁሉ በነገር ሁሉ ሰውነቱን ይገዛል፤ እነዚያም የሚጠፋውን አክሊል ሊያገኙ ነው፥ እኛ ግን የማይጠፋውን። ስለዚህ እኔ ያለ አሳብ እንደሚሮጥ ሁሉ እንዲሁ አልሮጥም፥ ነፋስን እንደሚጎስም ሁሉ እንዲሁ አልጋደልም፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 9፡ 24-26 
 
ሁላችንም እንሮጣለን ፡፡ ሁሉም ሩጫ ወደውጤት አያመጣም፡፡ ውጤታማ ሩጫ አለ ከንቱ ሩጫ አለ፡፡ የሁላችንም ሩጫ ለኦሎምፒክ ላይሆን ይችላል፡፡ ሁላችንም የኦሎምፒክን ሚኒማ ላናሟላ እንችላለን፡፡ 
 
ግን ሁላችንም በህይወት ለመሮጥ በሩጫው ባለቤት እግዚአብሄር በእየሱስ አዳኝነት ካመንን ብቁ ልንሆንና ሚኒማውን አሟልተናል መሮጥም እንችላለን፡፡ እንደ ማንኛውም ሩጫ ይህም የዘላለም ሩጫ ህግ አለው፡፡ ስለዚህ የዘላለም ውጤት ስለሚያስገኘው ሩጫ ህግ መፅሃፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡
  • ውጤት ለሁሉም አይደለም፡፡ የክርስትናውን ሩጫ ከሌላ የሚለየውና ደግነቱ ከአንድ እስከ ሶስት የወጣ ብቻ የሚሸለምበት እንደ አካል ብልት ሁላችንም ለተለያየ ተግባር ስለተጠራን በዚህ ሩጫ በሚገባ የሮጠ ሁሉ ይሸለማል፡፡ 
     
  • ለመዳን እየሱስ በመስቀል ላይ በሰራው ስላ ማመን ብቻ ሲጠይቅ ለመሸለም ግን ውሳኔን ይጠይቃል፡፡ በክርስትና ህይወት የሚሸለመው በድንገት አይደለም፡፡ ለአክሊል በትጋት በውሳኔና በእውቀት የሰራ ይሸለማል፡፡ ለዚህ ነው መፅሃፍ ታገኙ ዘንድ ሩጡ የሚለው። 
     
  • ሩጫ ትግስትንና ጥበብን ይጠይቃል፡፡ ሩጫ ሰውነትን መግዛትና ዲሲፒሊን ይጠይቃል፡፡ ውጤት ቁጥብነትን ስለሚጠይቅ ሯጭ የሚያደርጋቸውና የማያደርጋቸው ነገሮች አሉ፡፡ ሯጭ የሚበላውና የማይበላው አለ፡፡ ሯጭ በሩጫው ውጤት ለማምጣት ሰውነቱን በነገር ሁሉ ይገዛል፡፡ 
     
  • የህይወት ሩጫ ሽልማት ከማንኛውም የኦሎምፒክ ሽልማት ይበልጣል፡፡ የምድር ሽልማት የሚጠፋ ሽልማት ነው፡፡ ይህ ሽልማት ስንሞት አብሮን የሚሄድ ሽልማት አይደለም፡፡ ይህ ሽልማት የመሬት ስበት ይዞ የሚያስቀረው ከነፍስና ከመንፈሳችን ጋር አብሮን ወደሰማይ የሚሄድ አይደለም፡፡ የህይወት ሽልማት የዘላለም ነው፡፡
ለሚጠፋ መብል አትሥሩ፤ ነገር ግን ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር መብል የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ሥሩ፤ እርሱን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና። ዮሃንስ 6፡27 5.
  • ይህ የዘላለም ሽልማት ሩጫ በትኩረትና በአላማ የሚሮጥ ነው፡፡ በዚህ ሩጫ ላይ ስናተኩር በፊታችን ከሩጫችን የሚያስተጓጉሉንን እንቅፋቶች እናልፋለን፡፡ መንፈሳዊ ህይወታችን በቃሉ ሙሉ ፍሬ እንዳያፈራ ትኩረታችንን ሊከፋፍል የሚመጣውን የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት መታለል እንቃወማለን፡፡
በእሾህ መካከል የተዘራውም ይህ ቃሉን የሚሰማ ነው፥ የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት መታለል ቃሉን ያንቃል፥ የማያፈራም ይሆናል። ማቴዎስ 13፡22 6.
  • ሩጫ ትግስት ፡ ጥበብና እርጋታን ይጠይቃል፡፡ የህይወት ሩጫ ማራቶን እንመሆኑ መጠን ጉልበት አለኝ ተብሎ የሚበረርበት አይደለም፡፡ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ ዕብራውያን 12፡1 
     
  • የሩጫ ወደር የሌለው ምሳሌያችን ኢየሱስ ነው፡፡ እርሱን ተመልክተን እንደሱ ከሮጥን የማናሸንፍበት ምክኒያት የለም፡፡ እየሱስ በፊቱ ስላለው ዘላለማዊ ደስታ ብዙ ነገሮችን ንቋል፡፡
እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና። ዕብራውያን 12፡1-2 
 
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
 
#ሩጫ #ትግስት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #የእግዚአብሄርቃል #የእግዚአብሔርፈቃድ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment