ህዝብ በፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ላይ ያለውን ሚና ወሳኝ ነው፡፡ ሰው የፖለቲካ መሪዎች መልካምን ሲያደርጉ ሊያመሰግናቸውና
ሊያበረታታቸው ይገባል፡፡ ፍትህ ሲዛባ ደግሞ ይህ ትክክል አይደለም እንደዚህ መሆን የለበትም ብሎ ድምፁን በማሰማት በየደረጃው ያሉ
የመንግስት ባለስልጣኖችን ማሳሰብ ይኖርበታል፡፡
የሰው ሃሳብና አስተያየት የሃገር ሃብት እንደመሆኑ መጠን መንግስትም ሃገር የሚገነባው ከህዝብ ጋር አብሮ እንደሆነ ተረድቶ
ህዝብን በማክበር ለህዝብ ድምጽ ጆሮ መስጠት አለበት፡፡ መንግስት የህዝቡን ጥያቄ በቅንነት መስማትና ራሱን በሚገባ መፈተሽ እንጂ ህዝብን ሁልጊዜ በጥርጣሬ ማየት የህዝብ የመንግስት ግንኙነት የሰመረ
እንዳይሆን ያደርገዋል፡፡ መንግስት ግን የህዝብ ድምፅ አያስፈልገኝም ካለ ከፍተኛ ችግር ይፈጠራል፡፡
ህዝብም የህሊና ነፃነትና ሃሳቡን በነፃነት መግለፅ ለአገር ግንባታ እንደሚጠቅም ተረድቶ ሃሳቡን መስጠት አለበት፡፡ እንዲሁም
ህዝብም ሃገር ማስተዳደር ቀላል እንዳልሆነ ተረድቶ በትእግስት ፍላጎቱን ለመሪዎቹ ሊያስረዳቸው ትኩረታቸውን ሊስብ ያስፈልጋል፡፡
መንግስት የህዝብ አገልጋይ ነው፡፡ የመንግስት አላማ ህዝብን በሚገባ በማስተዳደር ወደ ብልፅግና ማድረስ ነው፡፡ መንግስት
ህዝብን በሚገባ ካላስተዳደረ በሰዎች መካከል የሚያደላ ከሆነ ፣ መንግስት ለህዝቡ የሚገባውን አክብሮት ካልሰጠ ፣ መንግስት ህዝብን
ማገልገል ላይ ካላተኮረና ህዝብን በፍትህ ካላስተዳደረ የህዝብን ልብ እያጣው ይሄዳል፡፡
የንጉሥ ክብር በሕዝብ ብዛት ነው፤ በሰው ጥቂትነት ግን የገዥ ጥፋት አለ። ምሳሌ 14፡28
በተሉያየ ደረጃ ያሉ የመንግስት አካላት የራሳቸውን ጥቅም ብቻ የሚፈልጉ ከሆነና ህዝብን ከማገልገል ይልቅ የራሳቸው ጥቅምና
ስልጣናቸውን ማስጠበቅ ላይ ካተኮሩ ስልጣናቸውን መጠበቅ ከባድ ይሆንባቸዋል፡፡ የሚያድጉት ጥቂት ሰዎች ብቻ ከሆኑና አብዛኛው የህብረተሰብ
ክፍል እየከበደው ከሄደ የሃብታምና የደሃው ልዩነት እየሰፋ ከሄደ መንግስት እንደሚናወጥ ለመናገር አይቸግርም፡፡
ግፍን መሥራት በንጉሥ ዘንድ ጸያፍ ነገር ነው፥ ዙፋን በጽድቅ ይጸናልና። ምሳሌ 10፡12
ረብሻንና መቁሰልንና መሞትን የሚፈልግ ማንም ሰው የለም፡፡ መንግስት እንደ አባት ልጆቹን በእኩልነት እያየ ሁሉም የሚያድጉበትና
የሚለወጡበትን መንገድ ከቀየሰና ከተገበረ በዚህ የህዝብን አመኔታ ካተረፈ ህዝብ በደስታ ከመንግስት ጋር ይሰራል፡፡
መንግስት ይበልጥ የሚፈለገውና የሚከበረው እንዲሁም እየጠነከረ የሚሄደው ህዝብ ሲረካበት ብቻ ነው፡፡ የህዝብ ልብ ከመንግስት
ጋር ካልሆነ ተሰሚነቱ እየጠፋ ይሄዳል፡፡
ለድሀ በእውነት የሚፈርድ ንጉሥ፥ ዙፋኑ ለዘላለም ይጸናል። ምሳሌ 29፡14
እኛ ደግሞ የመንግስት መሪዎች ሃላፊነታቸውን በሚገባ እንዲወጡና ህዝቡም በሰላም እንዲኖር እንዲሁም ሰው ሁሉ ከዚህ ሁሉ
በላይ የሆነውን የነፍስ ከሃጢያት ነፃነት እንዲያገኝ ለመንግስት ባለስልጣኖችና ለህዝቡ ሁሉ እንድንፀልይ ተጠርተናል፡፡
እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር፥ ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ። ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው። 1ኛ
ጢሞቴዎስ 2፡1-4
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ፀሎት #አማርኛ #ቤተክርስትያን #ኢትዮጲያ
#ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ
No comments:
Post a Comment