Popular Posts

Tuesday, August 2, 2016

የሚያስፈልገው አንድ ነገር



በህይወት እግዚአብሄር እንዳለልን በልቡና በነፍሱ እንዳለ መኖር የከበረ ነገር ነው፡፡ እግዚአብሄር የሚፈልገው ይህ ነው ብለን በግምት በመኖር ህይወታችንን ከምናባክን እግዚአብሄር የሚፈልገውን አግኝተንና አድርገን ማለፍ ወደር የማይገኝለት መታደል ነው፡፡ 


እግዚአብሄር ምን እንደሚፈልግ እንድንገምትለትና እንድናደርገው አልጠየቀንም፡፡ እግዚአብሄር የሚፈልገውን ግልፅ አድርጓል፡፡ የሚያስፈልገው ብዙ ነገር አይደለም፡፡ 


ሰዎች እግዚአብሄርን ለማስደሰትና ለማስደነቅ በራሳቸው የሚሄዱት ብዙ መንገዶች እግዚአብሄርን አያስደንቁትም፡፡ ሰዎች የሚያስፈልገውን ነገር ሳያደርጉ በአገልግሎት ስም ጭምር እግዚአብሄርን ለማስደሰት የሚያደርጉት ነገሮች እግዚአብሄር ጎሽ አይላቸውም፡፡  


እግዚአብሄር የሚፈልገውን ያውቃል የሚፈልገውም እንዲደረግለት ይፈልጋል ይጠብቃል፡፡ 


እየሱስ እነማርያም ቤት ሲሄድ አላማው ቤተሰቡ የእግዚአብሄርን ቃል እንዲሰሙና ፈቃዱን እንዲረዱ ነው፡፡ ማርታ ግን በቤት ስራ ልታገለግለው ጉድ ጉድ በማለትዋ እየሱስ ወደቤተሰቡ የሄደበትን አላማ ፈፅሞ ሳተችው፡፡ እየሱስና ማርታ ተላለፉ፡፡  
በዚያ ሰአት የማርታ ከምንም አስቀድሞ የእግዚአብሄርን ቃል መስማት ወደር የማይገኝለት የህይወት ምርጫ ነበር፡፡ እርስዋ ግን እየሱስ ይፈልጋል ብላ ያሰበችውን እንጂ እየሱስ የፈለገውን አላደረገችም፡፡ 


እርስዋ ለእየሱስ መልካም ነው ብላ የገመተችውን በማድረግ ልታገለግለው ደፋ ቀና ትል ነበር፡፡ ያ እየሱስን አላስደሰተውም፡፡ ብዙ ነገር በማድረጉዋ እያገለገለች እያስደሰተችው መሰላት፡፡ 


እግዚአብሄር በህይወታችን ቅድሚያ እንድንሰጠው የሚፈልገው ነገር ቃሉን መስማት ነው፡፡ ከኑሮ ከስራ ከአገልግሎትም ከሩጫም በፊት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚያስፈልገው ቃሉን መስማት ነው፡፡ 


እንዲያውም እየሱስ የሚያስፈልገው ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው አለ፡፡ የሚያስፈልገው በአለም ሩጫና ባተሌነት ሳይወሰዱ ረጋ ብሎ እግዚአብሄር ከኔ ምን ይፈልጋል ብሎ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ለማግኘት ጊዜን መስጠትና ያንን ማድረግ ነው፡፡


ሲሄዱም እርሱ ወደ አንዲት መንደር ገባ፤ ማርታ የተባለች አንዲት ሴትም በቤትዋ ተቀበለችው። ለእርስዋም ማርያም የምትባል እኅት ነበረቻት፥ እርስዋም ደግሞ ቃሉን ልትሰማ በኢየሱስ እግር አጠገብ ተቀምጣ ነበረች። ማርታ ግን አገልግሎት ስለ በዛባት ባከነች፤ ቀርባም፦ ጌታ ሆይ፥ እኔ እንድሠራ እኅቴ ብቻዬን ስትተወኝ አይገድህምን? እንኪያስ እንድታግዘኝ ንገራት አለችው። ኢየሱስም መልሶ፦ ማርታ፥ ማርታ፥ በብዙ ነገር ትጨነቂአለሽ ትታወኪማለሽ፥ የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው፤ ማርያምም መልካም ዕድልን መርጣለች ከእርስዋም አይወሰድባትም አላት። ሉቃስ 10፡38-42


ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር  share ማድረግ ቢወዱ 




#ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment