Popular Posts

Sunday, August 14, 2016

ብርቅ ነው እንዴ?!

ክርስትና በእግዚአብሄር ሃይል የሚኖር ልዩ የህይወት ዘይቤ ነው፡፡ በክርስትና እንደ ብርቅ የምናያቸው ነገር ግን ብርቅ ያልሆኑ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህ ብርቅ ያልሆኑ ነገሮች ለምስክርነታችን ምንም የሚጠቅሙት ነገር የለም፡፡ ከእግዚአብሄር ስለተቀበልነው ሃይል የማይመሰክሩና የተቀበልነውን የእግዚአብሄር ፀጋ /የሚያስችል ሃይል/ የማያሳዩ ለየት ያላሉ የህይወት ዘይቤዎች ናቸው፡፡
ይህን የኢየሱስን አዳኝነት ስንቀበል የተቀበልነውን የእግዚአብሄር ፀጋ ለየት ባለው የህይወት ዘይቤያችን ካልገለፅን በስተቀር ለሌሎች ምስክር ልንሆንና ሌሎችን ወደጌታ ልንማርክ አንችልም፡፡

የሚወዱዋችሁን ብትወዱ ብርቅ ነው እንዴ? ብርቅ አይደለም፡፡ ብርቅ የሚሆነው ጠላታችሁን ስትወዱ ለሚያሳድዱዋችሁ ስትፀልዩ ነው፡፡ ይህ ለየት ያለ የህይወት ዘይቤ ነው፡፡
የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? ቀራጮችስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? ማቴዎስ 5፡46
የሚረግሙትን መራገም ብርቅ ነው እንዴ? አይደለም፡፡ ማንም ሰው የሚረግመውን ለመራገም ይፈተናል፡፡ ግን የሚረግሙዋችሁ ብትመርቁ ይህ ብልጫ ያለው የህይወት ደረጃ ነው፡፡
የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ስለሚበድሉአችሁም ጸልዩ። ሉቃስ 6፡28
በሰላሙ ቀን መበርታት ብርቅ ነው አንዴ? አይደለም፡፡ ብርቅ የሚሆነው ሰው በመከራ ቀን ጉልበቱ ሲፈተን በፅናት ሲያልፍ ነው፡፡ በመከራ ቀን ብትላላ ጉልበትህ ጥቂት ነው። ምሳሌ 24፡10
ጠላታችሁን ብትጠሉ ብርቅ ነው እንዴ? ብርቅ አይደለም፡፡ ጠላትን መውደድና ለሚጠሉን መልካም ማድረግ ግን ከፍ ያለ ምስጋና ያለው የህይወት ዘይቤ ነው፡፡ ነገር ግን ለእናንተ ለምትሰሙ እላችኋለሁ፥ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ ለሚጠሉአችሁ መልካም አድርጉ፥ መልካምም ለሚያደርጉላችሁ መልካም ብታደርጉ፥ ምን ምስጋና አላችሁ? ኃጢአተኞች ደግሞ ያን ያደርጋሉና። ሉቃስ 6፡27፣33
ያየነውምን ተስፋ ብናደርግና ያየነውን ብናምን ብርቅ ነው እንዴ? ብርቅ አይደለም ፡፡ ብርቁ ያላየነውን ተስፋ ስናደርግና ያላየነውን ስናምን ነው፡፡
ነገር ግን ተስፋ የሚደረግበቱ ነገር ቢታይ ተስፋ አይደለም፤ የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል? ሮሜ 8:24
ኢየሱስ ሞትን ድል አድርጎ መነሳቱን የሰማው ቶማስ በአይኔ ካላየሁ አላምንም ብሎ ነበር፡፡ እየሱስንም ሲያየው አምናለሁ አለ፡፡ እየሱስ ግን ስለአየህ ነው፡፡ ያመንከው ሳያዩ የሚያምኑ ብፁአን ናቸው ሲል ሳያዩ ማመን ከፍ ያለ ደረጃ መሆኑን አሳየው፡፡
ኢየሱስም፦ ስለ አየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው አለው። ዮሃንስ 20፡29
በኢየሱስ አዳኝነት ስናምንና ኢየሱስን ወደልባችን ስንጋብዝ የእግዚአብሄርን ፀጋ ተቀብለናል፡፡ ከእግዚአብሄር የተቀበልነውን የፀጋ ባለጠግነት ለሌሎች የምናሳየው በዚህ መንገድ ነው፡፡ በህይወታችን የሚሰራውን የጌታን ፀጋ / የሚያስች ሃይል / በመግለፅ ነው ለሌሎች የምንመሰክረው፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ቃል #ብልጫ #ፀጋ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #የእግዚአብሄርቃል #የእግዚአብሔርፈቃድ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment