ብዙዎቻችን እግዚአብሄር ፀሎታችንን እንደሚሰማ እናምናለን እንፀያለንም፡፡ እውነትም እግዚአብሄርም ፀሎትን የሚመልስ ህያው
አምላክ ነው፡፡
ግን ስንቶቻችን ነን የፀሎት መልሳችንን እንዴት ከእግዚአብሄር እንደምንቀበል የምናውቅ? መፀለያችን ብቻ ሳይሆን እንዴት
የፀሎታችንን መልስ ከእግዚአብሄር እንደምንቀበል ካላወቅን በስተቀር እግዚአብሄር ፀሎትን የማይመልስ ሁሉ ሊመስለን ይችላል፡፡
ወይም ደግሞ እግዚአብሄር እንደሚባርክ አምነን ለእግዚአብሄር ገንዘባችንን እንሰጣለን፡፡ ለእግዚአብሄር ገንዘባችንን በመስጠታችን
ምንም እንደማይጎድልብን እናምናለን፡፡ እውነትም ነው ለእግዚአብሄር ሰጥቶ የጎደለበት ሰው የለም፡፡
ለእግዚአብሄር ገንዘባችንን ስንሰጥ እግዚአብሄር ገንዘብን ሊሰጠን ይችላል፡፡ ነገር ግን እኛ ለእግዚአብሄር ገንዘባችንን
ስንሰጥ እግዚአብሄር የሚሰጠን ገንዘብ ብቻ አይደለም፡፡
በህይወታችን ከእግዚአብሄር የምንፈልገው ነገር ገንዘብ ብቻ አይደለም፡፡ ከእግዚአብሄር የምንፈልገው ብዙ አይነት ነገር
አለ፡፡ ገንዘብ ውስን ስለሆነ ገንዘብ ሊመልሳቸው የማይችላቸው ብዙ ጥያቄዎች በህይወታችን አሉ፡፡
እግዚአብሄርም መሃሪ ስለሆና የህይወታችንን የጊዜውን ጥያቄ በሚገባ መመለስ ስለሚፈልግ ለእግዚአብሄር ገንዘባችንን ስንሰጥ
የሚሰጠን ወይም መልሶ የሚባርከን በገንዘብ ብቻ አይደለም፡፡ ከገንዘብ በላይ እጅግ አስፈላጊና ውድ ነገሮች በህይወታችን አሉ፡፡
እግዚአብሄር ገንዘብን ይሰጣል ገንዘብ ብቻ አይደለም እግዚአብሄር ሰላምን ይሰጣል፡፡ እግዚአብሄር እርካታን ይሰጣል፡፡
እግዚአብሄር ሞገስን ይሰጣል፡፡ እግዚአብሄር እረፍትን ይሰጣል፡፡ የምንበላውን እህልና ውሃ እንኳን የሚባርከው እግዚአብሄር ነው፡፡
እግዚአብሄር በሽታን ከመካከላችን ያርቃል ፡፡ ዘጸአት 23፡25
እግዚአብሄር ሲባርክ አንድን ጥሩ ነገር እንድናደርግ በምሪት ይባርከናል፡፡ ትክክለኛውን ነገር እንድናደርግ እግዚአብሄር
በልብ መነሳሳት ይባርከናል፡፡ የማይቻለውን ነገር እንድናደርግ ያልተለመደ ድፍረትን ይሰጠናል፡፡ እርሻን አርሰን እንድንበላ ጉልበትን
የሚሰጠን እንኳን እግዚአብሄር ነው፡፡
በልብህም፦ ጉልበቴ የእጄም ብርታት ይህን ሀብት አመጣልኝ እንዳትል። ዘዳግም 8፡17
ነግደን እንድናተርፍ እግዚእብሄር ጥበብን ይሰጠናል፡፡ እግዚአብሄር እንዲከናወንልን በሮችን ይከፍትልናል፡፡ ካለንበት
ሁኔታ ውስጥ እንድንወጣ ቃልን በጊዜው የሚሰጠው እግዚአብሄር ነው፡፡ እነዚህን ፈላጊና ተፈላጊ የሚያገናኘው እግዚአብሄር ነው፡፡
እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሐይ በታችም ሩጫ ለፈጣኖች፥ ሰልፍም ለኃያላን፥ እንጀራም ለጠቢባን፥ ባለጠግነትም ለአስተዋዮች፥
ሞገስም ለአዋቂዎች እንዳልሆነ አየሁ፤ ጊዜና እድል ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል። መክብብ 9፡11
እግዚአብሄርን በህይወታችን የማንፈልግበት ሁኔታ የለም፡፡ እግዚአብሄርንም የሚባርከን በሁሉም መንገዶች ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ
ብልፅግና ማለት ብዙ ገንዘብ ማግኘት ብቻ ሳይሆን የምንፈልገውን ነገር በምንፈልግበት ጊዜ ማግኘት ነው፡፡
እንግዲህ በእኛ እንደሚሠራው ኃይል መጠን ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ ይልቅ እጅግ አብልጦ ሊያደርግ ለሚቻለው፥
ኤፌሶን 3፡20
ከእግዚአብሄር መቀበላችን የተረጋገጠ ነውና ወደእግዚአብሄር መፀለያችንንና ለእግዚአብሄር መስጠታችንን እናብዛ፡፡
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
No comments:
Post a Comment