እግዚአብሄር ሰውን ሲፈጥር በምድር ላይ ያለውን ችግር እንዲፈታ ነው፡፡ ማንኛውም ሰው የሚፈጠረው ለሰዎች ከሚያስፈልገው ልዩ ችሎታና /talent/ ተሰጥኦ ጋር ነው ፡፡
በምድር ላይ የተፈጠርነው ከእኛ ለተሻለ ነገር ነው፡፡ የእኛ በምድር ላይ የመወለድ አላማ ከእኛ ለሚበልጥ አላማ ነው፡፡ እኛ በምድር ያለነው በዋነኝነት ለሌላው ሰው ነው፡፡ በምድር ያለነው ሌላውን ለማገልገልና ለመጥቀም ነው፡፡ ሰውን እውነተኛ እርካታን የሚያገኘው ሌላውን የማገልገል ሃላፊነቱን ሲወጣ ብቻ ነው፡፡
ሰው ሌላውን ማገልገል ቸል ሲል ሁሉ ነገሩ ይዘበራረቃል፡፡ ሰው ሌላውን ከማገልገል ይልቅ ራስ ወዳድ ሲሆን ምንም የተሟላ ነገር ቢኖረውም እንኳን ህይወቱ ሰላም የሌለው ጎስቋላ ይሆናል፡፡
ለራሱ ብቻ ለመኖር እንደተፈጠረ በተሳሳተ መልኩ የሚያስብ ሰው ምንም ነገር ቢኖረው ባለው ነገር አይረካም፡፡ ራስ ወዳድ ሰው የእኔነት ጥማቱንና ረሃቡን አርክቶ አይዘልቀውም ስለዚህ ሰው ባለው ነገር አይረካም፡፡
ነገር ሁሉ ያደክማል፤ ሰው ይናገረው ዘንድ አይችልም፤ ዓይን ከማየት አይጠግብም፥ ጆሮም ከመስማት አይሞላም። መክብብ 1፡8
ሰው ግን የተፈጠረው ለሌላው ሰው እንደሆነ ሲረዳና ሌሎችን ማገልገል ላይ ሲያተኩር በህይወቱ ይረካል የሚያጣውም ምንም ነገር አይኖርም፡፡ ሰው የተፈጠረበትን ሰዎችን የማገለገል አላማ ሲያሳካ የራሱ ኑሮ ጥያቄ አይሆንበትም፡፡
ሰው ሌላውን ለማገልገል ለሌላው ጥቅም ስለተሰራ የምትፈልገውንም ነገር ሁሉ እንሰጥሃለን ስራ ግን አትስራ ቢባል ስራን ካልሰራ እንደተገደለ ይቆጥረዋል፡፡
ሰው የተፈጠረበትን ሰውን የማገልገል ክብር ሲረዳ ለሰዎች በመኖር ሰዎችን በማንሳት ሰዎችን በመጥቀም ይረካል፡፡ ሰው ሊያገለግል የሚችል በመልካምነት የተሞላ ሰውን ሊያነሳ የሚችል በሰው ህይወት ላይ ዋጋን መጨመር የሚችል ሰውን ማስደሰትና መጥቀም የሚችል እንደሆነ መተማመን ሲኖረው በህይወቱ ዘመን ሁኩ ሌሎች ላይ ዋጋ በመጨመር ላይ ያተኩራል፡፡
ምስኪን እኔ አስተሳሰብ ያለበት ሰው ግን ነጥቆ ሰብስቦ አከማችቶ ለራሱ ብቻ ኖሮ ምንም መልካም አሻራ ሳይተው ያልፋል፡፡ ስለዚህ ነው ለራሱ ብቻ የሚኖር ታሪኩ በመቃብር ያልቃል ለሌሎች የሚኖር ግን በጠቀማው ባነሳቸውና ባገለገላቸው ሰዎች አማካኝነት አሻራው ለዘመናት ይቆያል የሚባለው፡፡ እኔ ህይወትም መንገድም እውነትም ነኝ ያለው እየሱስ እንዲህ ይላል፡፡
እንዲሁም የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም። ማቴዎስ 20፡28
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር ያድርጉ ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakum...
No comments:
Post a Comment