ፈጥነውም ሥራውን ረሱ፥ በምክሩም አልታገሡም። በምድረ በዳም ምኞትን ተመኙ፥ በበረሃም እግዚአብሔርን ተፈታተኑት። የለመኑትንም ሰጣቸው፤ ለነፍሳቸው ግን ክሳትን ላከ። መዝሙር 106፡13-15
እግዚአብሄር ለክብሩ ፈጥሮናል፡፡ ሰው የተፈጠረው ለእግዚአብሄር አላማ ነው፡፡ ሰው የተፈጠረው ለእግዚአብሄር ነው፡፡ ስለዚህ ነው እግዚአብሄር ሰውን ሲነግረው ለሁለት መሆን እንደማይችልና እርሱን መታዘዝ ባቆምን ጊዜ ከእግዚአብሄር ጋር እንደሚቆራረጥ አስቀድሞ አስጠነቀቀው፡፡
እግዚአዘብሄር ኩሩ ነው፡፡ እግዚአብሄር ለክብሩ የፈጠረውን ሰው ከሌላ ከማንም ጋር ሊጋራው አይፈልግም፡፡
እግዚአብሔር አምላክም ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው፦ ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና። ዘፍጥረት 2፡16-17
ሁለት ወዶ አይሆንም ይላል ያገሬ ሰው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ሰው እንዴት ለሁለት ጌቶች እንዴት መገዛት እንደሚችል በብዙ ቃላት ሊያስረዱን ቢሞክሩም ኢየሱስ ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም ይለናል፡፡ ኢየሱስ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል ይለናል በግልፅ ቃል፡፡
ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም። ማቴዎስ ወንጌል 6፡24
የእግዚአብሄርን የፈለገ ሰው የእግዚአብሄርን ያገኛል፡፡ የእግዚአብሄርን መንገድ ያልፈለገ ሰው ግን የእግዚአብሄርን ነገር አያገኝም፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር የምንገናኘው በእርሱ መንገድ ነው፡፡ እግዚአብሄር ለማንም ብሎ ቃሉን አይለውጥም፡፡ እግዚአብሄር ንጉስ ነው፡፡
የእግዚአብሄርን ነገር ስትመርጡ የእግዚአብሄርን ሙሉ ነገር ታገኛላችሁ፡፡ የእግዚአብሄርን መንገድ ስትፈልጉ አብሮ የሚመጣ የነፍስ ብልፅግናን ታገኛላችሁ፡፡ የእግዚአብሄርን መንገድ ለመከተል ስትፈልጉ አብሮ የሚመጣ ጉርሻ አለው፡፡ የእግዚአብሄርን ነገር መከተል ጥቅማ ጥቅም አለው፡፡ አንድን እቃ ስትገዙ ምርቃት ሊኖረው ይችላል፡፡ ምንም ሳትገዙ ምርቃት መጠበቅ ሞኝነት ነው፡፡
አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፤ በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና፥ በመንፈስ ግን የሚዘራው ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል። ገላትያ ሰዎች 6፡7-8
የእስራኤል ህዝብ እግዚአብሄርን አልፈለጉም፡፡ የእስራኤል ህዝብ የራሳቸውን መንገድ መረጡ፡፡ ያን ጊዜ የእግዚአብሄርን አብሮነት አጡት፡፡ የእግዚአብሄርን ነገር ሳንፈልግ የእግዚአብሄርን ነገር የሚፈልጉ ሰዎች የሚያገኙትን ለማግኘት መሞከር አጉል ብልጣብልጥነት ነው፡፡
የእግዚአብሔር በረከት ባለጠጋ ታደርጋለች፥ ኀዘንንም ከእርስዋ ጋር አይጨምርም። ምሳሌ 10፡22
እግዚአብሄር በሰጠን ካልረካንና በራሳችን እጃችንን ዘርግተን እግዚአብሄርን ያልሰጠንን ከወሰደን እግዚአብሄር እጁን ያወጣል፡፡ እግዚአብሄር ለእያንዳንዳችን የራሱ ልዩ አላ አለው፡፡ እግዚአብሄር ከእኛ አላማ ጋር አይተባበርም፡፡ በራሳችን የምንወስደው እርምጃ የእግዚአብሄርን አብሮነት አያስተማምንም፡፡ የእግዚአብሄርን እርምጃ ሳንታገስ የምንወስደው እርምጃ ለነፍሳችን ጉስቁልናን ያመጣል፡፡
በምንም ሁኔታ ውስጥ የእግዚአብሄርን ነገር ስንከተል ነው ሰላምና እረፍት እርካታን የምናገኘው፡፡
ፈጥነውም ሥራውን ረሱ፥ በምክሩም አልታገሡም። በምድረ በዳም ምኞትን ተመኙ፥ በበረሃም እግዚአብሔርን ተፈታተኑት። የለመኑትንም ሰጣቸው፤ ለነፍሳቸው ግን ክሳትን ላከ። መዝሙር 106፡13-15
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
No comments:
Post a Comment