Popular Posts

Saturday, January 27, 2018

የኢየሱስና የእኛ ልጅነት እንድነት እና ልዩነት

ሰላም ለእናንተ ይሁን፡፡ ፅሁፌን ከሚከታተሉ ቅዱሳን መካከል በኢየሱስና በእኛ ልጅነት መካከል ስላለ ልዩነት ብታስረዳ የሚል ጥያቄ ተቀብያለሁ፡፡ እኔም ይህ ለትምህርት ለሁላችን ይጠቅማለ ብዬ ስላሰብኩ ዛሬ ስለዚህ ሃሳብ በአጭሩ አንዳንድ ነገሮችን ላነሳ ወደድኩ፡፡ ትምህርቱ በጣም ሰፊ ጊዜ የሚጠይቅ ትምህርት ነው፡፡ ስለዚህ በጣም አስፈላጊ ናቸው የምናለውን ብቻ መርጬ በአጭሩ አስረዳለሁ፡፡
የኢየሱስንና የእኛን የልጅነት አንድነትና ልዩነት ለመረዳት መጀመሪያ አንድነታችንን ብንመለከት ጥሩ መንደርደሪያ ይሰጠናል፡፡
የኢየሱስና የእኛ አንድነት
1.      ኢየሱስ በስጋ ነው የተወለደው እኛም በስጋ ነው የተወለድነው፡፡
ኢየሱስ የእኛን ስጋ ነው የለበሰው፡፡ የኢየሱስ ስጋ ከእኛ ስጋ በምንም አይለይም፡፡
እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ . . . በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ። ዕብራዊያን 2፡14-15
2.     ኢየሱስ እኛ በምንፈተንበት ፈተና ሁሉ ተፈትኗል፡፡ አንዳንድ ሰዎች የኢየሱስ ስጋ ሃጢያትን የሚያሙዋልጭ ስጋ ነው ይላሉ፡፡ በዚህ አልስማማም፡፡ ኢየሱስ በስጋው ሃጢያት መስራት ባይችል ኖሮ አይፈተንም ነበር፡፡ ፈተና ያለው መውደቅ ስላለ ነው፡፡ አግዚአብሄር ይመስን ኢየሱስ ግን በሃጢያት ተፈተነ እንጂ በሃጢያት አልወደቀም፡፡
ኢየሱስ በሃጢያት የማይወድቅ ስጋ ቢኖረው ኖሮ ለእኛ የቅድስና ምሳሌ ሊሆንልን አይችልም ነበር፡፡
ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ፥ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም። ዕብራዊያን 4፡15
3.     ኢየሱስ በተፈጥሮአዊ መንገድ በጥበብ እና በሞገስ ያደግ ነበር እኛም እናድጋለን
እኛ የእግዚአብሄርን ነገር አንድ ብለን ተምረን በእግዚአብሄር ነገር እንደምናድግ ሁሉ ኢየሱስን ወደምድር ሲመጣ ራሱን ባዶ በማድረጉ የተነሳ የእግዚአብሄርን ነገር አንድ ሁለት ብሎ መማርና ማደግ ነበረበት፡፡
ኢየሱስም ደግሞ በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ያድግ ነበር። ሉቃስ 2፡52
4.     ኢየሱስ የሚያበረታው መንፈስ ቅዱስን መቀበል ነበረበት
በስጋው ወራት ካለመንፈስ ቅዱስ አሸናፊ የእግዚአብሄ ልጅ ሆኖ ማለፍ ስለማይችል መንፈስ ቅዱስን መሞላት አስፈልጎታል፡፡
ኢየሱስም መንፈስ ቅዱስ መልቶበት ከዮርዳኖስ ተመለሰ፥ በመንፈስም ወደ ምድረ በዳ ተመርቶ፥ ሉቃስ 4፡1
5.     በእግዚአብሄር ከኢየሱስ ጋር እኩል ተወደናል
እግዚአብሄር ኢየሱስን ከሚወደው ያነሰ እኛን አይወደንም፡፡  
እንዲሁም ዓለም አንተ እንደ ላክኸኝ በወደድኸኝም መጠን እነርሱን እንደ ወደድሃቸው ያውቃል። ዮሃንስ 17፡22-23
6.     ከኢየሱስ ጋር ወንድማማቾች ነን
ኢየሱስ የእግዚአብሄር ልጅ ነው እኛም የእግዚአብሄር ልጆች ነን፡፡ ኢየሱስ ወንድሞቼ ብሎ ሊጠራን አላፈረብንም፡፡
የሚቀድሰውና የሚቀደሱት ሁሉ ከአንድ ናቸውና፤ ስለዚህም ምክንያት፦ ስምህን ለወንድሞቼ እነግራቸዋለሁ በማኅበርም መካከል በዜማ አመሰግንሃለሁ፤ ደግሞም፦ እኔ በእርሱ እታመናለሁ፤ ደግሞም፦ እነሆኝ እኔን እግዚአብሔር የሰጠኝንም ልጆች ሲል ወንድሞች ብሎ ሊጠራቸው አያፍርም። ዕብራዊያን 2፡11-13
7.     ኢየሱስን እንድንመስል ነው የተወሰንነው
ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤ ሮሜ 8፡29
ኢየሱስ ወደምድር የመጣው የእግዚአብሄር ልጅነትን ምሳሌ ሊያሳየን ናሙና ሊሆንልን ነው፡፡ አንድ ልጅ በአባቱ ዘንድ ያለውን ክብር ሊያሳየን ነው፡፡
ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን። ዮሃንስ 1፡14
8.     ኢየሱስ በምድር ላይ እንደተላከ እኛም ተልከናል፡፡
ኢየሱስም ዳግመኛ፦ ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ አላቸው። ዮሃንስ 20፡21

በኢየሱስና በእኛ ልጅነት መካከል ምንም ልዩነት የለም፡፡ ነገር ግን ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ነገሮች መመልከት ይጠቅመናል፡፡
የኢየሱስና የእኛ ልዩነት
1.      ኢየሱስ ሃጢያት ሰርቶ አያውቅም እኛ ግን በንስሃ ከሃጢያታችን ተመልሰን ነው፡፡
እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡21
2.     ኢየሱስ የሞተ መንፈስ ኖሮት አያውቅም እኛ ግን በአዳም በሃጢያት ከእግዚአብሄር የተለየው መንፈሳችን ዳግመኛ ተወልዶ ነው፡፡
ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው። ዮሃንስ 3፡3
3.     ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት የእግዚአብሄር ብቸኛ ልጁ ነበር፡፡
በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዮሃነስ 3፡16
4.     እኛ ከዳንን በኋላ የእግዚአብሔር ልጆች በመሆናችን ኢየሱስ የመጀመሪያ ልጅ ሆኗል
ኢየሱስ የሃጢያታችንን እዳ ከከፈለ በኋላ እና እኛም ለእኔ ነው ብለን ስንቀበለው የእግዚአብሄር ልጆች በመሆናችን የእግዚአብሄር አንድያ ልጅ የነበረው ኢየሱስ የመጀመሪያ ልጅ ሆኗል፡፡ አሁን ኢየሱስ የመጀመሪያ ልጅ እንጂ አንድያ ልጅ አይደለም፡፡  
ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ ዮሃነስ 1፡12
ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤ አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው። ሮሜ 8፡29-30
5.     ኢየሱስ አዳኛችንና ቀዳሻችን ነው
ሁላችንም በሃጢያት እስራት ውስጥ ወድቀን በነበርን ጊዜ ስለሃጢያታችን እዳ መስዋእት የሆነልን ኢየሱስ ነው፡፡
የሚቀድሰውና የሚቀደሱት ሁሉ ከአንድ ናቸውና፤ ስለዚህም ምክንያት፦ ስምህን ለወንድሞቼ እነግራቸዋለሁ በማኅበርም መካከል በዜማ አመሰግንሃለሁ፤ ደግሞም፦ እኔ በእርሱ እታመናለሁ፤ ደግሞም፦ እነሆኝ እኔን እግዚአብሔር የሰጠኝንም ልጆች ሲል ወንድሞች ብሎ ሊጠራቸው አያፍርም። ዕብራዊያን 2፡11-13
6.     ኢየሱስ ጌታችን ነው እኛ ተከታዮቹ ነን
ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ ሮሜ 10፡9
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #የልጅነትክብር #ናሙና #አንድያ #በኩር #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ቃል #ሞዴል #መምሰል #የእግዚአብሄርእቅድ #የእግዚአብሄርፈቃድ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment