Popular Posts

Wednesday, January 24, 2018

የእውነተኛ ምሁር ባህሪያት

1.      እውነተኛ ምሁር በእውቀቱ አይመካም
እውነተኛ ምሁር እውቀቱን ትልቅ ነገር አያደርገውም፡፡ እውነተኛ የተማረ ሰው እውቀት ስላለው ሌላ እውቀት የለሌለውን አይንቅም፡፡ እውነተኛ ምሁር ሌላውን በማክበሩና በትህትናው ይታወቃል፡፡ እውነተኛ ምሁር ሌሎችን በእውቀት እንዲያገለግል ስጦታ እንደተሰጠው አገልጋይ ራሱን ያያል፡፡  
እነሆ፥ እግዚአብሔር ኃያል ነው፥ ማንንም አይንቅም እርሱም በማስተዋል ብርታት ኃያል ነው። ኢዮብ 36፡5
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጠቢብ በጥበቡ አይመካ፥ ኃያልም በኃይሉ አይመካ፥ ባለ ጠጋም በብልጥግናው አይመካ፤ ኤርሚያስ 9፡23
2.     እውነተኛ ምሁር የትምህርትን ውስንነት ያውቃል፡፡
እውነተኛ ምሁር ሂሳብ ከተማረ ያልተማራቸው እጅግ ብዙ የትምህርት መስኮች እንዳሉ ይረዳል፡፡ እውነተኛ ምሁር ባልተማረበት ክፍል ራሱን አዋርዶ ከሌሎች ይማራል፡፡ እውነተኛ የተማረ ከእርሱ የተሻሉ እውቀት ያላቸው ሰዎች እንዳሉ ይረዳል፡፡
ማንም አንዳች የሚያውቅ ቢመስለው ሊያውቅ እንደሚገባው ገና አላወቀም፤ 1 ቆሮንቶስ 8፡2
3.     እውነተኛ ምሁር ቀለምነት ስጦታ እንጂ የትጋት ማረጋገጫ እንዳልሆነ ያውቃል
ሁሉ ሰው ቀለም እንዲሆን አልተጠራም፡፡ አንዳንዱ አርቲስት ሌላው ደግሞ የቴክኒክ ባለሙያ እዲሆን ተጠርቶዋል፡፡ እውነተኛ ምሁር የአእምሮ የትምህርት መያዝ ችሎታ የእግዚአብሄር ስጦታ እንጂ የትጋት ማረጋገጫ እንዳይደለ ያስባል፡፡ ከእርሱ የተሻለ የሚተጉ ሰዎች ያ የእውቀት መረዳት ችሎታው ስለሌላቸው የተማሩ እንዳይደሉ ያስባል፡፡
. . . የጥበብ መግዣ ገንዘብ መኖሩ ስለ ምንድር ነው? ጥበብን ይገዛ ዘንድ አእምሮ የለውምና።
4.     እውነተኛ ምሁር እውቀትን ለሌሎች ቀላል ያደርጋል፡፡
እውነተኛ ምሁር እርሱ ብቻ እንደተመረቀ ሌላው ደግሞ እንደማይመለከተው አያስብም፡፡ እውነተኛ ምሁር ስለሚያውቀው አውቀት በተራ ሰው ቋንቋ ይናገራል ያስረዳል፡፡ እውነተኛ ምሁር ነገሮችን በማቅለል እንጂ በወሳሰብ አይታወቅም፡፡
የመበለቶችን ቤት የሚበሉ ጸሎታቸውንም በማስረዘም የሚያመካኙ እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ። ማርቆስ 12፡40
5.     እውነተኛ ምሁር የተማረውን ለማካፈል ይተጋል፡፡
እውነተኛ ምሁር እውቀቱን እጅግ የተቀደሰ ለጥቂት ሰዎች ብቻ የተለየ አያደርገውም፡፡ እውነተኛ የተማረ ትምህርቱን በሰዎች ውስጥ በማብዛት ይታወቃል፡፡ እውነተኛ የተማረ እውቀቱን በማካፈሉ የእርሱ ተፈላጊነት እንደሚጨምር እንጂ እንደሚቀንስ አያስብም፡፡ እውነተኛ ምሁር እውቀቱን በማካፈሉ ሌሎች ይበልጡኛል የሚል ስጋት የለውም፡፡ እውነተኛ ምሁር የሚኖረው በእውቀቱ ሳይሆን በእግዚአብሄር እንደሆነ ያስባል፡፡ እውነተኛ ምሁር ስኬቱ በእግዚአብሄ እንጂ በእውቀት እነዳይደለ ጠንቅቆ የሚረዳ ነው፡፡
እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሐይ በታችም ሩጫ ለፈጣኖች፥ ሰልፍም ለኃያላን፥ እንጀራም ለጠቢባን፥ ባለጠግነትም ለአስተዋዮች፥ ሞገስም ለአዋቂዎች እንዳልሆነ አየሁ፤ ጊዜና እድል ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል። መክብብ 9፡11
6.     እውነተኛ ምሁት አእምሮው ብቻ ሳይሆን ልቡም ሰፊ ነው፡፡ እውነተኛ ምሁር ሰዎችን ይወዳል፡፡ እውነተኛ ምሁር ከእርሱ የተለዩት ሰዎች የተሳቱ እንዳይደሉ ያውቃል፡፡ እውነተኛ ምሁር ከእርሱ ለተለዩት ሰዎች በልቡ ቦታ አለው፡፡
እግዚአብሔርም ለሰሎሞን እጅግ ብዙ ጥበብና ማስተዋል በባሕርም ዳር እንዳለ አሸዋ የልብ ስፋት ሰጠው። 1ኛ ነገስት 4፡29
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እውቀት #ትምህርት #ቀለም #ምሁር #ስኬት #እረኛእግዚአብሄር #ስምረት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መፅሃፍቅዱስ #እውነተኛ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment