Popular Posts

Follow by Email

Tuesday, January 30, 2018

ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ

ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ። 1ኛ ቆሮንቶስ 9፡27
ስጋዊ ምኞት ከእግዚአብሄር በረከት የሚያጎድለን ጠላታችን ነው፡፡ ስጋ ወዳጅ አይደለም አይለመንም፡፡ ስጋ እንደ እኩያ ኣ እንደወዳጅ አይደራደሩትም፡፡ ወደ እሳት እየሄደ ያለን ህፃን እንደማይለምኑት ፣ እንደማይደራደሩትና ሮጠው በግድ እንደሚነጥቁት ስጋም እንዲሁ ነው፡
ስጋ የምታስብለት የምትንከባከበው አይደለም፡፡ ስጋ የምትጨክንበት ፣ የምታስርበውና የምትገድለው ነው፡፡ ስጋ የሚጠይቀውን ሃጢያት በከለከልከው መጠን እየደከመ ይሄዳል፡፡ ስጋ የሚፈልገውን ሃጢያት ባልሰጠኸው መጠን አቅም እያጣ ይሄዳል፡፡ ስጋ ላይ በጨከንክበት መጠን ይደክማል፡፡
ነገር ግን እላለሁ፥ በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ። ገላትያ 5፡16
የስጋ ጥያቄ ይችን ብቻ ስጠኝ ነው፡፡ የስጋ ጥያቄ አሁን ብቻ ነው፡፡ አሁን ብቻ ይህችን ብቻ ለሚለው ጥያቄ እሺ ካልከውና ሃጢያትን ካመቻቸህለት ስጋን ታበረታዋለህ፡፡ ስጋን ሃጢያት በሰጠኸው መጠን ፍላጎቱ እየጨመረ ፣ ተጨማሪ እየጠየቀና የጩኸቱ ድምፅ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ስጋን ደግሞ አይ አይሆንም እምቢ ባልከው መጠን ድምፁ እየቀነሰ እየደከመ እየሞተ ይሄዳል፡፡
ስጋ እንደታሰረ ውሻ ነው፡፡ የታሰረ ውሻ ያስፈራራል ፣ መጣሁልህ ይላል ፣ በላሁህ ይላል፡፡ ግን እንደታሰረ ካወቅን ቦታ አንሰጠውም አንሰማውም፡፡ ስጋ እንደታሰረ ውሻ ቸል ሊባል ይገባዋል፡፡ ስጋ ካልሰማኸኝ አለቀልህ የሚለው ፉከራው ካለሰማኸው እጣ ፈንታው መድከምና መሞት እንጂ ምንም ማድረግ አይችልም፡፡ ስጋ ሊራብ ይገባዋል፡፡ ስጋ የሚፈልገው በመከልከል ሊሰቀልና ሊገደል ይገባዋል፡፡  
ስለዚህ ነው መፅሃፍ ቅዱስ ቅዱሳን የሚፈልገውን ባለማድረግ ስጋን ከምኞቱ ጋር እንደሰቀሉት የሚናገረው፡፡
የክርስቶስ ኢየሱስም የሆኑቱ ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ። ገላትያ 5፡24
ስጋ ያለልክ እንዳይጠግብ ምግቡን ሃጢያት በመከልከል ልክ ማስገባት ያለብን እኛ ነን፡፡ ስጋን መጨቆን ያለብን እኛ ነን፡፡ ስጋን የመጨቆን ሃላፊነት የተጣለው በእኛ ላይ ነው፡፡ ስጋ ላይ መጨከን ያለብን እኛ ነን፡፡
ይህ እንደ ገዛ ፈቃድህ በማምለክና በትሕትና ሥጋንም በመጨቆን ጥበብ ያለው ይመስላል፥ ነገር ግን ሥጋ ያለ ልክ እንዳይጠግብ ለመከልከል ምንም አይጠቅምም። ቆላስይስ ሰዎች 2፡23
ስለዚህ ነው መፅሃፍ ቅዱስ ለስጋ ምኞት እንዳናስብ እንዳናመቻችለት የሚያስጠነቅቀን፡፡
በቀን እንደምንሆን በአገባብ እንመላለስ፤ በዘፈንና በስካር አይሁን፥ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፥ በክርክርና በቅናት አይሁን፤ ነገር ግን ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤ ምኞቱንም እንዲፈጽም ለሥጋ አታስቡ። ሮሜ 13፡13-14
መንፈስ የሚቃወመውን ስጋን የምናዳክመው ስጋን በመጨቆን ነው፡፡ ለስጋ ባለማሰብና ለእርካታው ባለማቅረብ ነው መንፈስ እንዲያሸንፍ የምንረዳው፡፡ ስጋን በማስራብና በማዳከም ነው መንፈስ እንዲመራ የምናደርገው፡፡ ስጋ የምንቀርበው ሃሳቡን እህህ ብለን የምንሰማው አይደለም፡፡ ስጋን በፍጥነት የምንቃወመው ፣ ብዙ እንዲያወራ የማንፈቅድለት ፣ በሃይል የምንጎሽመውና ለእግዚአብሄር ሃሳብ የምናስገዛው ነው፡፡  
ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ። 1ኛ ቆሮንቶስ 9፡27
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #የመንፈስፍሬ #ፍቅር #ሰላም #ስጋ #ምኞት #ማሰብ #ህይወት #ሞት #ደስታ #ዘር #ባህሪ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #የእግዚአብሄርህይወት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #በጎነት #የዋሃት #ራስንመግዛት #ትግስት #ትህትና

No comments:

Post a Comment