Popular Posts

Sunday, January 28, 2018

የእምነት ያለህ አትበል

እግዚአብሄር ከሰው ጋር ግንኙነት ማድረግ ስለፈለገ ሰውን በመልኩና በአምሳሉ ፈጠረው፡፡ ሰው በሃጢያት ምክንያት ከእግዚአብሄር ከተለያየም በኋላ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር እንዲገናኝ በዘመናት ሁሉ እግዚአብሄር ሁኔታዎችን ሲያመቻች ቆይቷል፡፡
እግዚአብሄር አሁንም ከሰው ጋር ግንኙነት ማድረግ ስለሚፈልግ ከእርሱ ጋር የሚገናኝበትን መንገድ አዘጋጅቷል፡፡ እግዚአብሄር መንፈስ ነው፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር መገናኘት የሚችለው በእምነት ነው፡፡ ሰው እግዚአብሄርን የሚደርሰው በእምነት ነው፡፡ ሰው እግዚአብሄርን የሚያገኘው በእምነት ነው፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ጠይቆ የሚቀበለው በእምነት ነው፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ተግባብቶ የሚኖረው በእምነት ነው፡፡ ሰው እግዚአብሄርን የሚሰማውና የሚታዘዘው በእምነት ነው፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር የሚራመደው በእምነት ነው፡፡
ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ዕብራውያን 11፡6
እምነትን ለማግኘት ሰው እጅግ የተመረቀ ሰው መሆን የለበትም፡፡ እምነትን እንዲኖረው ሰው ቅዱስ መሆን አይጠበቅበትም፡፡ ሰው እምነት እንዲኖረው ሰማእት መሆን የለበትም፡፡
እምነት እጅግ ርቆ የተሰቀለ ዳቦ አይደለም፡፡ እምነት አንዳንድ ሰዎች ብቻ በድንገት የሚያገኙት እድል አይደለም፡፡ እምነት ለጥቂት ለተመረጡ ሰዎች የሚመጣ ገጠመኝ አይደለም፡፡ እምነት እጅግ ጥቂት ሰዎች ተመራምረው የሚደርሱበት ረቂቅ ነገር አይደለም፡፡
እምነት የሚመጣው ከመስማት ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል መስማት የሚችል ሰው ሁሉ እምነት ሊኖረው ይችላል፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል የሚያነብ ሰው ሁሉ እምነት ሊመጣለት ይችላል፡፡ እምነት የሚመጣው የእግዚአብሄርን ቃል ከመስማት ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል የሚሰማ ማንኛውም ሰው እምነት ይመጣለታል፡፡
ሰው ዝም ብሎ እምነትን መመኘት የለበትም፡፡ ሰው እምነት እንዲኖረው ቁጭ ብሎ መጓጓት የለበትም፡፡ ሰው እምነት ያላቸውን ሰዎች ተመልክቶ በተስፋ መቁረጥ መቋመጥ የለበትም፡፡ ሰው እኔ እንግዲህ እምነትን ከየት አመጣዋለሁ ማለት የለበትም፡፡
ከእምነት የሆነ ጽድቅ ግን እንዲህ ይላል፦ በልብህ፦ ማን ወደ ሰማይ ይወጣል? አትበል፤ ይህ ክርስቶስን ለማውረድ ነው፤ ወይም፦ በልብህ፦ ወደ ጥልቁ ማን ይወርዳል? አትበል፤ ይህ ክርስቶስን ከሙታን ለማውጣት ነው። ነገር ግን ምን ይላል? በአፍህ በልብህም ሆኖ ቃሉ ቀርቦልሃል፤ ይህም የምንሰብከው የእምነት ቃል ነው። ሮሜ 10፡6-8
እምነት ቀርቧል፡፡ እምነት በማንም ሰው ይገኛል፡፡ እምነት ለማንም ሰው የተሰወረ አይደለም፡፡ እምነት ከማንም ሰው ሩቅ አይደለም፡፡ ሰው እግዚአብሄርን የማገኝበት እምነት ከየት ይገኛል ማለት አይችልም፡፡ ሰው የእምነት ያለህ እንዳይል እምነት እንዴት እንደሚገኝ በመፅሃፍ ቅዱስ ተፅፏል፡፡
እምነት የሚገኘው የእግዚአብሄርን ቃል በመስማት ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል አንብብ እምነት ይሆንልሃል፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል ስማ የእምነት ሰው ትሆናለህ፡፡
እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው። ሮሜ 10፡17
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እምነት #ማየት #አለማየት #ቃል #የእግዚአብሄርሃይል #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #እወጃ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

No comments:

Post a Comment