Popular Posts

Follow by Email

Sunday, January 21, 2018

ራሳችንን የምንወድበት ሰባት ዋና ዋና መንገዶች

መፅሃፍ ቅዱስ ራስን ስለመውደድ ያስተምራል፡፡ ራስን ስለመውደድ መፅሃፍ የሚናገረው ሌላውን የምንወደው ራሳችንን በምንወድበት መጠን መሆኑን ሲናገር ነው፡፡ ሰው ራሱን ከሚወደውና ለራሱ ካለው አክብሮት በላይ ሌላውን ሰው ሊወድና ሊያከበር አይችልም፡፡
ሰው ሌላውን ግፋ ቢል የሚወደው ራሱን የሚወደውን ያህል ነው፡፡ ሰው ሌላውን የሚወደው ራሱን በመውደድና የሚገባውን ክብር ለራሱ በመስጠት ተለማምዶ ነው፡፡ ሰው ከራሱ ጋር ሲኖር በራሱ ላይ ያልተገበረውን ፍቅር በሌላው ላይ ሊተገብር አይችልም፡፡ ሰው ራሱን ከሚወደው በላይ ሌላውን ሊወድ አይችልም፡፡ ሰው አጠገቡ ያለውን ራሱን ካልወደደ ሌላውን ሊወድ አይችልም፡፡
የሌላውን የፍቅር ፍላጎት የምንረዳው የራሳችንን የፍቅር ፍላጎት ስንረዳ ነው፡፡ እኛ እንዴት እንድንወደድ በማየት ሰው እንዴት እንደሚወደድ እንማርበታለን፡፡ የእኛ መወደድ ሌላውን ለመውደድ መነሻ ነጥብ ነው፡፡
እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ ሕግም ነቢያትም ይህ ነውና። ማቴዎስ 7፡12
እግዚአብሄር እርሱን እንዴት እንደ አይኑ ብሌን እንደሚያየው የሚያውቅ ሰው እግዚአብሄር ሌላውን እንዴት እንደ አይኑ ብሌን እንደሚያየው ይረዳል፡፡ የእግዚአብሄርን ፍቅር በራሱ ያልቀመሰ ሰው ግን ሌላውን ሊወድ አይችልም፡፡ እግዚአብሄር እንዴት እንደወደደው የሚያውቅ ሰው ራሱን ይወዳል ሌላውን እንደራሱ ሊወድ ይችላል፡፡  
ሁለተኛይቱም፦ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የምትል እርስዋን የምትመስል ይህች ናት። ከእነዚህ የምትበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለችም። ማርቆስ 12፡31
ራሳችንን የምንወድበት ሰባት መንገዶች
1.      ራስን መውደድ እግዚአብሄር ያዘጋጀውን የመዳኛ መንገድ መቀበል ነው፡፡ ራሱን በሚገባ የሚወድ እና የሚያከብር ሰው ለዘላለም ከእግዚአብሄር መለያየት አይፈልግም፡፡ ራሱን የሚወድ ሰው እግዚአብሄር ያዘጋጀውን የመዳኛ መንገድ ይቀበላል፡፡ ራሱን የሚወድ ሰው የእግዚአብሄርን ፍቅር ይቀበላል፡፡
በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም። ዮሃንስ 3፡36
2.     ራስን መውደድ ራስን ማክበር ራስን ከሚያዋርድና ዝቅ ዝቅ ከሚያደርግ ክፉ ነገር መሸሽ ነው፡፡
ራሱን በሚገባ የሚወድ ሰው ሃጢያትን በመስራት ራሱን አያዋርድም፡፡ ራሱን የሚወድ ሰው እግዚአብሄርን ባለመፍራት ከፈጣሪው ጋር አይጣላም፡፡
ሥጋችሁ የክርስቶስ ብልቶች እንደ ሆነ አታውቁምን? እንግዲህ የክርስቶስን ብልቶች ወስጄ የጋለሞታ ብልቶች ላድርጋቸውን? አይገባም። 1ኛ ቆሮንቶስ 6፡15
3.     ራስን መውደድ ራስን አለመኮነን ነው፡፡
ራሴን ስወድ እግዚአብሄር ይቅር ያለውን ራሴን ይቅር እላለሁ ራሴን አልኮንነውም፡፡ ራስን መውደድ የሰይጣንን ክስ ሰምቶ ራስን ላለመኮነን  መጠንቀቅ ነው፡፡ ራስን መውደድ እግዚአብሄር ያላለውን ማንኛውም ወቀሳና ፍርድ አለመቀበል ነው፡፡
ነገር ግን በእናንተ ዘንድ ወይም በሌላ ሰው ዘንድ ብፈረድ ለእኔ ምንም አይደለም፤ እኔም በራሴ እንኳ አልፈርድም፤ በራሴ ላይ ምንም አላውቅምና፥ ነገር ግን በዚህ አልጸድቅም፤ እኔን የሚፈርድ ግን ጌታ ነው። 1ኛ ቆሮንቶስ 3-4፡4
4.     ራስን መውደድ ራስን መቀበል ነው፡፡
እግዚአብሄር ውብና ድንቅ አድርጎ ፈጥሮናል፡፡ እግዚአብሄር በምድር ላይ እንድንሰራው ፣ እንድናገኘውና እንድንሆነው  ለጠራን ነገር ያለን ፈጥረት በልኩ ነው አያንስም አይበዛም፡፡ ራስን መቀበልና ራስን መውደድ ከእኛ ለተለየ አላማ የተጠራውን ሌላውን ሰው ለመሆን አለመጣር ነው፡፡ ራስን መውደድ በእግዚአብሄር አሰራር መርካት ነው፡፡  
ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፥ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች። መዝሙር 139፡14
5.     ራስን መውደድ እግዚአብሄር ያላለውን ነገር ላለማደርግ መጠንቀቅ ነው፡፡
ያለን ህይወት አንድ ህይወት ነው፡፡ በምድር ላይ ያለነው ለእግዚአብሄር አላማ ነው፡፡ ራሱን የሚወድ እና ለራሱ አክብሮት ያለው ሰው እግዚአብሄር ያለውን እንጂ እግዚአብሄር ያልመራውን ነገር ላለማድርግ ይጠነቀቃል፡፡ ራስን መውደድ እግዚአብሄር ለእኛ ያለውን አላማ ፈልጎ ማግኘትና እርሱን ብቻ መከተል ነው፡
ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። ኤርሚያስ 29፡11
6.     ራስን መውደድ ውጤት በሌለው በጭንቀት ራስን አለማባከን ነው፡፡
ራሱን የሚወድ ሰው የሚያስጨንቀውን በጌታ ላይ ጥሎ በትኩረት የእግዚአብሄርን መንግስትና ፅድቁን ይፈልጋል፡፡
እንግዲህ፦ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡31-33
7.     ራስን መውደድ ማለት እግዚአብሄር እንደሚያይ ራሰን ማየት ነው፡፡
እግዚአብሄር ልጄ ነህ ሲል እንደ እግዚአብሄር ልጅ ራስን ማየት እንደእግዚአብሄር ልጅ ከፍ ያለ የክርስትና ህይወት ደረጃን መኖር ራስን መውደድ ነው፡፡
እንግዲህ በጌታ እስር የሆንሁ እኔ በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤ በትሕትና ሁሉና በየዋህነት በትዕግሥትም፤ እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ፤ ኤፌሶን 4፡1-2
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ፍቅር #መውደድ #የህግፍፃሜ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ዲዛይን #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ራስንመውደድ #መንፈስቅዱስ #ራስንማክበር #ልብ #መሪ

No comments:

Post a Comment