Popular Posts

Follow by Email

Thursday, January 25, 2018

የንጉሱና የባለትዳርዋ ሴት ታሪክ

በድሮ ዘመን ነው አሉ አንድ ንጉስ ነበረ፡፡ ይህ ንጉስ ከውበትዋ የተነሳ ወደ አንድ ባለትዳር ሴት ይሳባል፡፡ እናም እርሱዋን ማግባት እፈልጋለሁ ይላል፡፡ ሰዎች ግን ተው እንጂ ይህች ባለትዳር ሴት ነች እርሷንና ባልዋን ተዋቸው ብለው ይለምኑታል፡፡ እርሱ ግን አይ አይሆንም እኔ አርሷን ነው የማገባው ብሎ በውሳኔው ይፀናል፡፡
ውሳኔውን ልታስለውጥ እንዳልቻለች ያወቀችውና ባልዋንና ቤትዋን የምትወደው ይህች ባለትዳር ሴት እሺ አገባሃልሁ ብላ ትስማማለች፡፡ ነገር ግን የማገባህ አንድ ቅድመ ሁኔታ ከተሟላ ብቻ ነው ትላለች፡፡ ንጉሱም ምንድነው አንቺን የማገባበት ቅድመ ሁኔታ ደግሞ ብሎ ሲጠይቅ አይ እኔን ማግባት ካለብህ የሰርጉን ድግስ ሁሉ የምደግሰው እኔ ነኝ ብላ ሃሳቡዋን ትገልፅለታለች፡፡ በዚህ ከተስማማህ አገባሃለሁ ትለዋለች፡፡ እርሱ ግን እኔ ንጉስ ነኝ እኔ ነበርኩ መደገስ የነበረብኝ አንቺ ግን ካልሽ ይሁን ብሎ እርስዋ እንድትደግስ ይስማማል፡፡
የሰርጉ ቀን ደረሰ፡፡ ምግብ ሁሉ ተዘጋጅቶ በመሶብ በመሶብ ተሸፍኖ ተቀምጦአል፡፡ ንጉሱ ከምግቡ እንዲያነሳ ቅድሚያ ተሰጠው፡፡ ከዚያም የመጀመሪያው ምግብ ሲታይ ተልባ ነው፡፡ ንጉሱ ከተልባው ጥቂት አነሳና ወደሚቀጥለው መሶብ ሄዶ ሲከፍተው ሁለተኛው መሶብ ተልባ ነው፡፡ ሶስተኛው አራተኛው አምስተኛው መሶቦች ሁሉ ሲከፈቱ ተልባ ናቸው፡፡ እንዲያውም ሁሉም መሶቦች ሲከፈቱ ተልባ ሆነው ተገኙ ፡፡
ንጉሱ ተናደደ፡፡ ለምንድነው እንደዚህ ያደረግሽው ብሎ ሲጠይቃት ተመልከት ሴት ሁሉ አንድ ነው፡፡ ይህንን ትምህርት ላስተምርህ ስለፈልኩ ነው አለችው ይባላል፡፡
የሰው ምኞት አንዴ ቀዩዋን ፣ አንዴ ጠይምዋን ፣ አንዴ ቀጭንዋን ፣ አንዴ ወፍራምዋን ፣ አንዴ ረጅምዋን አንዴ ደግሞ አጭርዋን ሊፈልግ ይችላል፡፡
አስተማሪዬ እንዲህ ይላል፡፡ ሴት ሁሉ ግን አንድ ነው፡፡ ለመርካት አንድ ሴት በቂ ነው፡፡ አንድ ወንድ በአንድ ሴት መርካት ካልቻለ ችግሩ እርሱ ጋር ነው ማለት ነው፡፡ በአንድ ሴት መርካተ ካለቻለ ያልገባው ነገር አለ ማለት ነው፡፡ በአንድ ሴት መርካት ካልቻለ ራሱን ትሁት እድርጎ መማር እንጂ በብዙ ሴቶች ለመርካት መሞከር ከንቱ ድካም ራስን ማባከን ነው፡፡ ምክንያቱም የሴቶች ሁሉ መሰረታዊ ፍላጎት አንድ ነው፡፡ አንድን ሴት መያዝ ካልቻለ በአጠቃላይ ሴትን መያዝ አልቻለም ማለት ነው፡፡
በአንድ ሴት መርካት ያልተቻለ ሰው በብዙ ሴቶች እረካለሁ ዘበት ነው፡፡ በእንድ ሴት የመርካት እድሉ እጅግ ከፍተኛ ነበር፡፡ በብዙ ሴቶች ለመርካት መሞከር እድሉን እያጠበበው ነው የሚሄደው፡፡
ከዝሙት እንድትርቁ፥ እግዚአብሔርን እንደማያውቁ አሕዛብ በፍትወት ምኞት አይደለም እንጂ፥ ከእናንተ እያንዳንዱ የራሱን ዕቃ በቅድስናና በክብር ያገኝ ዘንድ እንዲያውቅ፤ . . . ማንም በዚህ ነገር አይተላለፍ ወንድሙንም አያታልል። 1ኛ ተሰሎንቄ 4፡4-6
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ህይወት #አንድ #ጋብቻ #ትዳር #ባል #ሚስት #ፍቅር #መውደድ #ይተዋል #ይጣበቃል #አንድስጋ #እውነት #ትህትና #ትንሳኤ #ህይወት #ወንጌል #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ  #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

No comments:

Post a Comment