Popular Posts

Follow by Email

Friday, January 12, 2018

ከሞተ ስራ ንስሃ

በመፅሃፍ ቅዱሳችን ውስጥ ካሉት ለሰመረ የክርስትና ህይወት መሰረት ከሆኑት መሰረታዊ ትምህርቶች መካከል ንስሃ አንደኛው ነው፡፡፡
ንስሃ ሃሳብን መለወጥ ሲሆን ሰው በፊት ከሚኖርነት የኑሮ አስተሳሰብ እእምሮው ተለውጦ በአዲስ አስተሳሰብ መኖር ሲጀምር ንስሃ ገባ ይቨባላል፡፡
ንስሃ መግባት ማለት የተለያዩ ሃይማኖታዊ ስርአቶችን ማድረግ ማለት አይደለም፡፡ ንስሃ ከምንሄድበት መንገድ ቀኝ ኋላ ዙር ብሎ መመለስ ነው፡፡ ሃሳባችንን ለውጠን ካልተመለስን በስተቀር የምናደርጋቸው ማንኛውም ሃይማኖታዊ ስርአቶች ሃይማኖተኛ እንደሆንን እንዲደሰማን ያደርጉ ይሆናል እንጂ ለእውነተኛ መንፈሳዊነት አይጠቅሙም፡፡ እግዚአብሄር መመለስን ይባርካል፡፡  
እንግዲህ ከጌታ ፊት የመጽናናት ዘመን እንድትመጣላችሁ አስቀድሞም ለእናንተ የመረጠውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲልክላችሁ፥ ኃጢአታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ ተመለሱም። ሐዋርያት 3፥19-20
በአለማችን ላይ በአስተምሮት ትምህርቶች በከፍተኛ ሁኔታ ያስነሳቸው የመፅሃፍ ቅዱስ አስተማሪው ዴሪክ ፕሪንስ ሲናገሩ በክርስትና ህይወት ላለማደግና ላለመለወጥ ትልቁ ፈተና ንስሃ አለመግባት ነው ይላሉ፡፡ እንዲሁም በቤተክርስትያን ውስጥ ከፍተኛ ችግር የሚፈጥሩ ሰዎች ንስሃ ያልገቡ ሰዎች ናቸው ይላሉ፡፡
ሰው በአለም አስተሳሰብ በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ ሊሰራ ሲሞክር ሁሉ ነገር ይዛባበታል፡፡ የአለም ሃሳቡን ለመተው ያልተዘጋጀ ሰው አብረው በፍፁም የማይሄዱ ሁለት ነገሮችን አብሮ ሊያስኬድ በመሞከር ህይወቱን ያጠፋል፡፡ የማንስሃ ንስሃ ያልገባው ሰው የሚፈልገውን ነገር ቢያገኝ እንኳን የእግዚአብሄርን አብሮነት በህይወቱ ያጣዋል፡፡
ጌታን የተቀበልነው ይህ አስተሳሰቤና ኑሮዬ አያዋጣኝም ብለን ነው፡፡ ነገር ግን ጌታን የተቀበለው ለሃይማኖት ለውጥ ከሆነ ምንም ውጤት ሳናገኝ ህይወችንን አናባክናለን፡፡
ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ፥ በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፥ ኤፌሶን 4፥22-23
አንድ ጊዜ እንደዚህ ሆነ፡፡ አንድ እህት ስለአንድ አገልጋይ እየነገረችኝ ነበር፡፡ ይህ አገልጋይ በጌታ ባይሆን ኖሮ ስንት ሴቶችን ያማርጥ እንደነበረ የነገራትን ስትነግረኝ በጣም ደነገጥኩ፡፡ አልነገርኳትም እንጂ በልቤ ይህ ሰው ንስሃ አልገባም ህይወቱ አደጋ ላይ ነው አልኩ፡፡
ይህ በቤተክርስትያን ውስጥ በጣም ሲያገለግል የነበረው እግዚአብሄር ያስነሳው አገልጋይ ከአመታተ በኋላ ወደኋላ ተመለሰና ያ ሲመካበት የነበረውን ሃጢያት ማድረግ ጀመረ፡፡ ወደ ቤተክርስትያን መጥቶ ነበር እንጂ የሃጢያት ጣእም በአፉ ውስጥ ነበር፡፡ ሃጢያትን አልተፀየፈውም አላፈረበትም ነበር፡፡
እንግዲህ ዛሬ ከምታፍሩበት ነገር ያን ጊዜ ምን ፍሬ ነበራችሁ? የዚህ ነገር መጨረሻው ሞት ነውና። ሮሜ 6፥21
ያለውን ማንኛውም አስተሳሰብ ለእግዚአብሄርን ቃል ለመለወጥ የወሰነ የተሰበረ ሰው በቤተክርስትያን ሲያድግና ሲለወጥ ታያላችሁ፡፡
በአስተሳሰባችን አለምን መስለን እግዚአብሄር ይባረከናል ብሎ መገመት ራስን መታለል ነው፡፡ ስለዚህ ነው በአለም አስተሰሳሰብ በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ ስለማይሳካልን መፅሃፍ ቅዱስ አስተሳሰባችሁንና አካሄዳችሁን ለውጡ ንስሃ ግቡ የሚለን፡፡
የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። ሮሜ 12፥2
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ጌታ #ኢየሱስ #ሃሳብ #ቃል #እግዚአብሄር #መንፈስቅዱስ #ንስሃ #መንገድንመቀየር #አስተሳሰብንመቀየር #መለወጥ #በረከት #መታደስ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #አእምሮ #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

No comments:

Post a Comment