Popular Posts

Thursday, January 18, 2018

እምነት ይጠይቃል

ከእግዚአብሄር ጋር ያለን ግንኙነት እንዲሰምር እምነት ይጠይቃል፡፡ እግዚአብሄር መንፈስ ነው፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር ያለን ማንኛውም ግንኙነት መንፈሳዊውን አለም የእግዚአብሄርን መንግስት ማየት ይጠይቃል፡፡ በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ ለመኖር በመካከላችን ያለችውን በአይን የማትታየውን መንፈሳዊውን አለም ማየት ይጠይቃል፡፡
ደግሞም፦ እንኋት በዚህ ወይም፦ እንኋት በዚያ አይሉአትም። እነሆ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናትና አላቸው። ሉቃስ 17፡21
መንፈሳውን አለም ማየት የማይችል ሰው ከእግዚአብሄርም ጋር ይሁን በአጠቃላይ ከመንፈሳዊ አለም ጋር ግንኙነት ማድረግ አይችልም፡፡ በተፈጥሯዊ አይንህ የሚታየውን ነገር ብቻ የሚያይ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ሊግባባ ፣ አብሮ ሊሰራና ውጤት ሊያገኝ አይችልም፡፡ ለመንፈሳዊ አለም አይኑ የታወረ ሰው እግዚአብሄርን ሊያየው እና ሊከተለው አይችልም፡፡  
ስለዚህ ነው ካለእምነት አግዚአብሄርን ደስ ማሰኘት የማይቻለው፡፡ እግዚአብሄርን ለማሰደስት እምነት ይጠይቃል፡፡ እግዚአብሄር እኛን በሚያስደንቁን ብዙ ነገሮች አይደነቅም፡፡ እኛን የሚያስደስቱን ነገሮች ሁሉ እግዚአብሄርን ላያስደስቱት ይችላሉ፡፡ እምነት ግን በእርግጥ እግዚአሔርን ደስ ያሰኘዋል፡፡
ሰው በምድር የሚፈለጉት ጥበብ ፣ ሃይልና ባለጠግነት ሁሉ ቢኖረው እምነት ግን ከሌለው እግዚአብሄርን አያስደስተውም፡፡ ጠቢብ ይሁን ያልተማረ ፣ ሃያልም ይሁን ደካማ ፣ ባለጠጋም ይሁን ደሃ እግዚአብሄርን የሚያሰደስተው ጠብቡ ሃይሉ ባለጠግነቱ ሳይሆን እምነቱ ነው፡፡ እግዚአብሄርን የሰው ጥበብ አያበረታታውም ፣ እግዚአብሄርን የሰው አለማወቅ ተስፋ አያስቆርጨውም ፣ የሰው ሃይል አያስገርመውም የሰው ድካም አያስደነግጠውም ፣ የሰው ባለጠግነት አያስገርመውም የሰው ድህነት አይከብደውም፡፡
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጠቢብ በጥበቡ አይመካ፥ ኃያልም በኃይሉ አይመካ፥ ባለ ጠጋም በብልጥግናው አይመካ፤ ነገር ግን የሚመካው፦ ምሕረትንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ፤ ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ ኤርምያስ 9፡23-24
የሰው ጥበብ ምንም እንደማያመጣ ፣ የሰው አለማወቅ ምንም እንደማይቀንስ ፣ የሰው ሃይል ከቁጥር እንደማይገባ ፣ የሰው ድካም ነገሩን እንደማይለውጥ ፣ የሰው ባለጠግነት ምንም እንደማይጨምር ፣ የሰው ድህነት ምንም እንደማይቀንስ ማወቅና ሁሉን በሚችል በእግዚአብሄር መታመን እግዚአብሄርን ያስደስተዋል፡፡  
እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሐይ በታችም ሩጫ ለፈጣኖች፥ ሰልፍም ለኃያላን፥ እንጀራም ለጠቢባን፥ ባለጠግነትም ለአስተዋዮች፥ ሞገስም ለአዋቂዎች እንዳልሆነ አየሁ፤ ጊዜና እድል ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል። መክብብ 9፡11
የሰው ፈጣንነት እግዚአብሄርን አያንቀሳቅሰውም፡፡ እግዚአብሄርን የሚያንቀሳቅሰው እምነት ነው፡፡
ካለእምነት እግዚአብሄርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፡፡ ወደእግዚአብሄርን በእምነት የሚደርስ ሰው ከእግዚአብሄር ዋጋን ይቀበላል፡፡ በእምነት ከእግዚአብሄር ጋር የሚገናኝ ሰው በእግዚአብሄር ጥበብ ፣ ሃይልና ባለጠግነት ይኖራል፡፡
ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ዕብራውያን 11፡6
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ልብ #ማመን #ቃል #መናገር #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ዋጋ #ማድረግ #ሁሉይቻላል #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment