እምነት በክርስትያን ህይወት በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ እንዲያውም ያለእምነት ከእግዚአብሄር ጋር መገናኘት አይቻልም፡፡ ካለእምነት እግዚአብሄርን ደስ ማሰኘት አይቻለም፡፡ ያለእምነት ከእግዚአብሄር ጋር በሚገባ መኖር አይቻልም፡፡
ስሜት ደግሞ የአካባቢያችንን ሁኔታ የሚያሳውቀን የሰውነታችን ክፍል ነው፡፡ ስሜት በአምስቱ የስሜት ህዋሳቶቻችን የምንረዳውን ነገር ያሳውቀናል፡፡ ስሜት ከአምስቱ የስሜት ህዋሳታችን በማየት ፣ በመስማት ፣ በመቅመስ ፣ በመዳደስና በማሽተት ከምንረዳው ነገር በላይ መሄድ አይችልም፡፡ ስሜት ድንበሩ ተፈጥሮአዊ አለም ብቻ ነው፡፡ ከተፈጥሮአዊ ወይም ከቁሳዊ አለም ያለፈን ነገር ስሜት መረዳት አይችልም፡፡
እምነት ደግሞ በእነዚህ የስሜት ህዋሳቶቻችን ከምንረዳው ያለፈ በመንፈሳዊ አለም ያለውን ነገር ያያል ፣ ይሰማል ፣ ይቀምሳል ፣ ይዳስሳል እንዲሁም ያሸታል፡፡
የእምነት ክልል መንፈሳዊው አለም ፣ በአይን የማይታየው አለምና ልእለ ተፈጥሮአዊው አለም ነው፡፡ እምነት የሚያየው በተፈጥሮ አይን የማይታየውን ነው፡፡ እምነት የሚያየው በውስጠኛው በልቦና በመንፈስ አይን የሚታየውን ነው፡፡
ይህም የልባችሁ ዓይኖች ሲበሩ የመጥራቱ ተስፋ ምን እንዲሆን በቅዱሳንም ዘንድ ያለው የርስት ክብር ባለ ጠግነት ምን እንዲሆን ለምናምን ከሁሉ የሚበልጥ የኃይሉ ታላቅነት ምን እንዲሆን ታውቁ ዘንድ ነው፤ ኤፌሶን 1፡18-19
እምነት የሚደርሰው መንፈሳዊውን አለምን ነው፡፡ እምነት የሚደርሰው እና የሚይዘው በተፈጥሮአዊ እጃችን መያዝ የማንችለውን በመንፈሳዊ አለም ያለውን ነገር ነው፡፡
ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ዕብራውያን 11፡6
የእምነት ክልል ከስሜት ክልል ያለፈ ስለሆነ የእምነትን ነገር ፣ የእግዚአብሄርን ነገር ፣ የመንፈስን ነገር በአምስቱ የስሜት ህዋሳቶቻችን ልንረዳው አንችልም፡፡
ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም። 1ኛ ቆሮንቶስ 2፡14
እምነት የሚያየውን ነገር ስሜት በፍፁም አይረዳውም፡፡ ስሜት የሚረዳበት ክልል ተፈጥሮአዊው አለም ነው፡፡ እምነት ደግሞ የሚረዳበት ክልል መንፈሳዊው አለም ነው፡፡
ስለዚህ በእግዚአብሄር ቃል በእምነት የተረዳነው ነገር ከስሜታችን ጋር ሊቃረን ይችላል፡፡ እግዚአብሄር በቃሉ አሸናፊ ነህ ሲል ስሜታችን የእግዚአብሄርን ቃል በእምነት መረዳት ስለማይችል የአካባቢውን ሁኔታ ብቻ ይናገራል፡፡
እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው። ዕብራዊያን 10፡17
ስለዚህ ነው በእምነት የስሜትን ነገር መመልከት እና መከተል እንደሌለብን መጽሃፍ ቅዱስ የሚያስተምረው፡፡ በእንደ ጊዜ የማይታየውን በእምነት አይተንም የዙሪያችንን ሁኔታም አይተንም አይሆንም፡፡ ስለዚህ ነው በእምነት ስንኖር አካባቢያችንን የሚነግረንን ስሜታችንን መስማት እንደሌለብን መፅሃፍ ቅዱስ የሚያስተምረው፡፡
የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት፥ . . . የሚታየው የጊዜው ነውና፥ የማይታየው ግን የዘላለም ነው። 2ኛ ቆሮንቶስ 4፡17-18
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ልብ #ማመን #ቃል #መናገር #ስሜት #ሁኔታ #አካባቢ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ማሰላሰል #ማድረግ #ሁሉይቻላል #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ
No comments:
Post a Comment