Popular Posts

Saturday, January 20, 2018

እናንተ ግን ክርስቶስን እንደዚህ አልተማራችሁም

እናንተ ግን ክርስቶስን እንደዚህ አልተማራችሁም፤ ኤፌሶን 420
ይህ ትክክለኛ የህይወት ዘይቤ ነው ብለው የሚያስተምሩ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ህይወት እንዲህ ነው ብሎ ጋዜጣ ያስተምራል ፣ ፊልም ያስተምራል የተለያዩ መፅሃፍት ያስተምራሉ ሬዲዮ ያስተምራል ቴሌቪዥን ያስተምራል፡፡
እነዚህ ያስተማሩት ነገር ሁሉም ስህተት ነው ባይባልም ነገር ግን እያንዳንዱ ትምህርት እውነት በሆነው በእግዚአብሄር ቃል አስተምሮት መፈተሽ አለበት፡፡
ስለዚህ ነው ሃዋሪያው የተለያየ ትምህርት ሰምተውና ተከትለው የተለያየ የህይወት ዘይቤ የሚያሳዩትን ሰዎች እናንተ ግን ይላቸዋል፡፡
ሌላው ሊያደርገው ይችላል፡፡ ሌላው ሊከተለው ይችላል፡፡ ሌላው ሌላ ነገር ተምሮ ሊሆን ይችላል፡፡ እናንተ ግን ክርስቶስን እንደዚህ አልተማራችሁም፡፡
ክርስትና ለአንዳንዶች ከሰዎች ሃይማኖቶች አንዱ ነው፡፡ ነገር ግን ክርስትና ከሰው ሃይማኖቶች አንዱ ሳይሆን ከእግዚአብሄር ጋር ያለ የአባትና የልጅ ግንኙነት እና ፍጥረት መሆን ነው፡፡
ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ ዮሃንስ 1፡12
ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡17
አንዳንዶች ክርስትያን ነን ብለው ነገር ግን ምንም የህይወት ለውጥ በህይወታቸው አይታይም፡፡ በህይወታቸው ንስሃ አልገቡም ከአሮጌው ኑሯቸው መንገዳቸውን አልለወጡም፡፡ አስተሳሰባቸውና ህይወታቸው በምድር ላይ የፈለገውን ነገር ከሚያደርግ አለማዊ ሰው በምንም አይለይም፡፡ እናንተ ግን ክርስቶስን እንደዚህ አልተማራችሁም፡፡
የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። ሮሜ 12፡2
አንዳንዶች ክርስትናን እግዚአብሄርንና ሰውን ማገልገያ መንገድ ሳይሆን ጥቅም ማግኛ አቋራጭ መንገድ አድርገውታል፡፡ እናንተ ግን ክርስቶስን እንደዚህ አልተማራችሁም
እግዚአብሔርን መምሰል ማትረፊያ የሚሆን በመሰላቸው ሰዎች ይገኛሉ። እንደነዚህ ካሉት ራቅ። ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡4-6
አንዳንድ ሰዎች ክርስትናን ራስን መካድ ሳይሆን የልጅነት ህልማቸውን የሚያስፈፅሙበት መድረክ አድርገውታል፡፡
እናንተ ግን እንዲህ አትሁኑ፤ ነገር ግን ከእናንተ ታላቅ የሆነ በመካከላችሁ እንደ ታናሽ፥ የሚገዛም እንደሚያገለግል ይሁን። ሉቃስ 22፡26
አንዳንዶች ክርስትናን የህይወት ለውጥ ሳይሆን ወግና ስርአት የተሞላ ህይወት የሌለው ባዶ ሃይማኖት አድርገውታል፡፡ እናንተ ግን ክርስቶስን እንደዚህ አልተማራችሁም፡፡
እንግዲህ አሕዛብ ደግሞ በአእምሮአቸው ከንቱነት እንደሚመላለሱ ከእንግዲህ ወዲህ እንዳትመላለሱ እላለሁ በጌታም ሆኜ እመሰክራለሁ። ኤፌሶን 4፡17
አንዳንዶች ክርስትና ከሲኦል መጠበቂያ መድህን ድርጅት እንጂ ከሃጢያት በላይ በአሸናፊነት የምንኖረብት የድል ነሺነት ህይወት አይደለም፡፡  
በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ፤ ወይስ ምናልባት የማትበቁ ባትሆኑ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ እንዳለ ስለ እናንተ አታውቁምን? 2ኛ ቆሮንቶስ 13፡5
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #የልጅነትክብር #ሃይማኖት #መልክ #አምሳል #ልጅ #አባት #ክብር #ማእረግ #መብት #ስልጣን #ስፍራ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ቃል #ሞዴል #መምሰል #የእግዚአብሄርእቅድ #የእግዚአብሄርፈቃድ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment