Popular Posts

Wednesday, November 29, 2017

ለውግዘት የተሳሳቱ መልሶች

በህይወታችንና በአገልግሎታችን ውግዘትና ተቃውሞ ይብዛም ይነስም በየጊዜው የሚከሰቱ ነገሮች ናቸው፡፡
ሰዎች በትክክለኛውም መንገድ ይሁን በተሳሳተ መንገድ ሊቃወሙንና ሊያወግዙን ይችላሉ፡፡ ሰዎች የእግዚአብሄርን ቃል ተከትለው ትክክለኛውን እርምጃ ጠብቀው ሊያወግዙን ይችላሉ፡፡
ወንድምህም ቢበድልህ፥ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ውቀሰው። ቢሰማህ፥ ወንድምህን ገንዘብ አደረግኸው፤ ባይሰማህ ግን፥ በሁለት ወይም በሦስት ምስክር አፍ ነገር ሁሉ እንዲጸና፥ ዳግመኛ አንድ ወይም ሁለት ከአንተ ጋር ውሰድ፤ እነርሱንም ባይሰማ፥ ለቤተ ክርስቲያን ንገራት፤ ደግሞም ቤተ ክርስቲያንን ባይሰማት፥ እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ። ማቴዎስ 18፡15-17
ሰዎች ለትክክለኛውም ሆነ ለተሳሳተ ምክኒያት ሊቃወሙንና ሊያወግዙን ይችላሉ፡፡ ሰዎች ከፍቅር ተነስተው እኛን ለማዳንና ከደከምንበት ለማቅናት የእኛን መመለስና እንደገና ጠቃሚ መሆን አልመው ሊያወግዙን ይችላሉ፡፡ ወይም ደግሞ ከቅናት ከጥላቻ መነሻ ሃሳብ /motive/ ስለ በለጥናቸው ፣ ስላደግንና ስለሰፋን ሊያወግዙንና ሊቃወሙን ይችላሉ፡፡
አንዳንዶቻችን እስከዛሬ ተወግዘን ሊሆን ይችላል፡፡ ሌሎቻችን ደግሞ ከአሁን በኋላ ልንወገዝ እንችላለን፡፡ አንዳንዶቻችን በአደባባይ እንወገዛለን ሌሎቻችን ደግሞ በቤተሰባችን በትምህርታችንም ይሁን በአካሄዳችን ልንወገዝ እንችላለን፡፡ በምንም መልኩ ቢሆን የሚመጣን ተቃውሞና ወገዛ የምንቀበልበትና የምናስተናግድበት የተሳሳተና ትክክለኛ መንገድ አለው፡፡ ወገዛን በትክክለፃው መንገድ ካስተናገድነው ይጠቅመናል በተሳሳተ መልኩ ከመለስነው ደግሞ አይጠቅመንም፡፡
ለተቃውሞ የምንመልስበት አምስት የተሳሳቱ መንገዶች
ጥላቻ
ሰውን ሁሉ ከመውደድ በስተቀር ማንንም ሰው እንድንጠላ መብት የለንም፡፡ ሰው ጠላኝ ብለን ብንጠላ የምንጎዳው እኛው ነን፡፡ የተሳሳተ ሰውን እንኳን ለመጥላት መብት የለንም፡፡  
እርስ በርሳችሁ ከመዋደድ በቀር ለማንም ዕዳ አይኑርባችሁ፥ ሌላውን የሚወድ ሕግን ፈጽሞታልና። ሮሜ 13፡8
መልሶ ማውገዝ
ያወገዘንን ሰው መልሶ ማውገዝ ተሳስቷል የምንለውን ነገር እኛው መድገም ሊሆን ይችላል፡፡ ሁለት ስህተቶች አንድ ትክክል አያስገኙም፡፡ ትክክለኛ መፅሃፍ ቅዱሳዊ መንገዱን ሳይጠብቅ ነው ያወገዘኝ ብለን የምንለውንም ሰው ትክክለኛ መንገዱን ሳንጠብቅ በስሜታዊነት ማውገዝ ስህተትን በስህተት ለማረም እንደ መሞከር ከንቱ ጥረት ነው፡፡
ዓይን ስለ ዓይን ጥርስም ስለ ጥርስ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ክፉውን አትቃወሙ፤ ዳሩ ግን ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት፤ ማቴዎስ 5፡38-39
እልኽ ውስጥ መግባት
እግዚአብሄር በህይወታችን የጠራን የተወሰነ ነገር እያለ ያንን ሃላፊነት ትተን የተቃውሞ መልስ ለመመለስ ጉልበታችንን ጊዜያችንን እውቀታችንምን ሁሉ ማባከን ስህተት ነው፡፡ ጥሪያችንን ትተን እልክ ውስጥ መግባት እግዚአብሄር የሰጠንን ተሰሚነት ፣ ፀጋና ፣ ጉልበትና ጊዜ አላስፈላጊ አታካራ ላይ ማዋል የህይወትና የአገልግሎት ብክነት ነው፡፡ እግዚአብሄር የሰጠንን ሃላፊነት እርግፍ አድርገን ትተን ለተቃውሞ የመልስ እርምጃ መራመድ ብክነት ነው፡፡ የተሳተን ተቃውሞን የምናሸንፍበት አንዱ መንገድ ትክክለኛውንም ነገር በማድረግ በመቀጠል ባለማቋረጥ ነው፡፡
ቃሉን ስበክ፥ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና፥ ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርህ፥ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም። 2 ጢሞቴዎስ 4፡2
መራገም
በተሳሳተም ይሁን በትክክለኛ መነሻ ሃሳብ እንዲሁም በትክክለኛው መፅሃፍ ቅዱሳዊው መንገድ ይሁን በሌላ መንገድ የተቃወመንን  ሰው ለመርገም አልተጠራንም፡፡ ሰውን ለመባረክ መልካምነቱን ለመፈለግ ለመልካምነቱ ለመስራት ብቻ ተጠርተናል፡፡ አጋጣሚውን ተጠቅመን የሚቃወመንን በእውነት በማመስገን በማክበር እድሉን ሌላውን ለማነፅ ልንጠቀምበት ይገባናል፡፡
ክፉን በክፉ ፈንታ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ በዚህ ፈንታ ባርኩ እንጂ፥ በረከትን ልትወርሱ ለዚህ ተጠርታችኋልና። 1ኛ ጴጥሮስ 3፡9
የተወገዝንበትን ነገር ይበልጥ ማጋነን
በተወገዝን ማግስት የተወገዝንበትን ነገር ይበልጥ ማፋፋም ማጋነን ትክክለኛው መንገድ አይደለም፡፡ ትምህርታችንና የህይወት መርሆዋችን ከሆነ ተቃውሞ ሲመጣ ካልለወጥነው እንኳን በዚያው ይቀጠላል እንጂ ይበልጥ ይበልጥ አይለጠጥም፡፡ ሌላው ፅንፍ የተሳሳተውን ሚዛናዊ አያደርገውም፡፡
በትምህርትህም ደኅንነትን፥ ጭምትነትን፥ ጤናማና የማይነቀፍ ንግግርን ግለጥ። ቲቶ 2:8
እራስን ከሰው ጋር አብሮ ማውገዝ
በተሳትነው ነገር ላይ ካልሆነ በስተቀር ስለተወገዝን በደፈናው ራስን ማውገዝ ሌላው ስህተት ነው፡፡ የተወገዝንበትን ነገር ራሱ መንፈስ ቅዱስ ሊመሰክርልን ይገባል እንጂ ሰዎች ስለፈረዱብን ብቻ ራሳችን ላይ መፍረድ ዋናው ስህተት ነው፡፡
ነገር ግን በእናንተ ዘንድ ወይም በሌላ ሰው ዘንድ ብፈረድ ለእኔ ምንም አይደለም፤ እኔም በራሴ እንኳ አልፈርድም፤ 1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 4፡3
ተቃውሞን በአጠቃላይ እንደ ክፉ ማየት
ተቃውሞ በራሱ ክፉም መልካምም አይደለም፡፡ ለተቃዋሚው ክፉ የሚያደርገው በንፁህ የልብ መነሻ ሀሳብ ካላደረገው ወይም ትክክለኛውን መፅሃፍ ቅዱሳዊ መርህ ሳይከተል በግብታዊነት ካደረገው ስህተት ይሆናል እንጂ ተቃውሞ በራሱ ስህተት አይደለም፡፡ ተወጋዡም ተቃውሞን እንከ እንቅፋትና እንደ ሰይጣን ስራ ካየው ከተቃውሞ ውስጥ ማውጣት ያለበትን ወሳኝ ጥቅም መጠቀም ያቅተዋል፡፡
እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ። ኤፌሶን 5፡15-16
እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን። ሮሜ 8፡28
ተቃውሞን ከሰው ጋር ማያያዝ
ተቃውሞ ሲደርስብን የተቃውሞውን ይዘት ከመመልከት ይልቅ አከሌ የተቃወመኝ እንደዚህ ስለሆነ ነው ብብሎ ምክኒያት መስጠትና ከሰው ጋረ ማያያዝ ከተቃውሞ የሚገባንን ጥቅም እንዳናገኝ ያደርገናል፡፡ ተቃውሞ ያጠራናል፡፡ ተቃውሞን በሚገባ ከያዝነው ትሁት ያደርገናል በዚያም የእግዚአብሄር ፀጋ እንዲበዛለን ያደርገናል፡፡  
እንዲሁም፥ ጐበዞች ሆይ፥ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፥ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል። 1ኛ ጴጥሮስ 5፡5
እግዚአብሄር ቢፈቅድ በሚቀጥለው ፅሁፍ ትክክለኛው የውግዘትን መልሶች ሃሳብ ይዤላችሁ እቀርባለሁ፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #አገልጋይ #ወገዛ #ስህተተ #ልብ #መሪ #ህሊና #ቀራጭ #ወገዛ #ትህትና #ፀጋ #ተቃውሞ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መነሻሃሳብ #ነቢይ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment