Popular Posts

Follow by Email

Tuesday, April 11, 2017

የመንግስቱ አስተሳሰብ

በምድር ላይ ህዝብን የሚያስተዳድርና የሚገዛ መንግስት እንዳለ ሁሉ በመካከላችን የእግዚአብሄር መንግስት አለ፡፡ የእግዚአብሄር መንግስት በአይን የማይታይ በስፍራ የማይወሰን መንግስት ነው፡፡ የእግዚአብሄር መንግስት ንጉስ ያለው ህዝብና የራሱ የአሰራር ህግ ያለው መንግስት ነው፡፡
ፈሪሳውያንም፦ የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ ትመጣለች ብለው ቢጠይቁት፥ መልሶ፦ የእግዚአብሔር መንግሥት በመጠባበቅ አትመጣም፤ ደግሞም፦ እንኋት በዚህ ወይም፦ እንኋት በዚያ አይሉአትም። እነሆ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናትና አላቸው። ሉቃስ 17፡20-21
በተቃራኒው አለም ማለት ሰይጣን የሚገዛበት የአሰራር ስርአት ነው፡፡ አለም ማለት ከተማ ማለት ሳይሆን ሰው ባራሱ ላይ ጌታ የሆነበት ከእግዚአብሄር መንግስት ተቃራኒ የኑሮ ዘይቤ ነው፡፡
ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም። 1ኛ ዮሐንስ 2፡15-16
የእግዚአብሄር መንግስት አስተሳሰብና የአለም አስተሳሰብ እጅግ የተለያዩ ናቸው፡፡
ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል። 1ኛ ዮሐንስ 2፡17
አለም ማለት ከእግዚአብሄር ቃል የተቃረነ የአስተሳሰብ ዘይቤና ዋጋ አመለካከት ነው፡፡
የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። ሮሜ 12፡2
የእግዚአብሄር መንግስት አስተሳሰብ ከአለም አስተሳሰብ የሚለይበት አስር መንገዶች  
1)     የፍቅርና ራስ ወዳድነት አስተሳሰብ  
የእግዚአብሄር መንግስት አስተሳብ እግዚአብሄርንና ሰውን ሁሉ የመውደድ አስተሳሰብ ነው፡፡ ከእግዚአብሄርና ከሰው ጋር በአክብሮት የምንኖርበት ስርአት ነው፡፡ የአለም መንግስት ግን ራስ ተኮር የሆነ እያንዳንዱን ነገር ከግል ጥቅም አንፃር ብቻ የሚመዘንበት ስርአት ነው፡፡
እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን። ቆላስይስ 1፡13-14
2)    የብርሃንና የጨለማ መንግስት
የእግዚአብሄር መንግስት በእግዚአብሄር ምሪት የተሞላ ነው፡፡ የአለም መንግስት ግን የእግዚአብሄር ምሪት የሌለበት ሰዎች መቼ እንደሚደናቀፉ የማያውቁበት የጨለማ መንግስት ነው፡፡ የእግዚአብሄር መንግስት የግልፅነት መንግስት ሲሆን የአለም መንግስት ድብቅ መንግስት ነው፡፡
ብርሃንም ወደ ዓለም ስለ መጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለ ወደዱ ፍርዱ ይህ ነው። ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፥ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤ እውነትን የሚያደርግ ግን ሥራው በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደ ሆነ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል። ዮሃንስ 3፡19-21
3)    የእውነትና የሃሰት አስተሳሰብ
የእግዚአብሄር መንግስት የእውነት መንግስት ነው፡፡ የእግዚአብሄር መንግስት ከእግዚአብሄርን ቃል የመጀመሪያውን የእግዚአብሄርን ሃሳብ የሚከተል መንግስት ነው፡፡ የአለም አሰራር ግን ላይ ላዩን ብቻ ማስተካል የሚፈልግ ውስጡን ግን የማያጠራ የሃሰት ማስመሰያ አስተሳሰብ ነው፡፡ የአለም አስተሳሰብ ውጭውን ብቻ በማሳመር የሚያታልል ሲሆን የእግዚአብሄር መንግስት ትኩረቱ የውስጥ የልብ ንፅህና ነው፡፡
ብዘገይ ግን፥ በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለሁ፤ ቤቱም የእውነት ዓምድና መሠረት፥ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ነው። 1ኛ ጢሞቴዎስ 3፡15
4)    ማገልገልና የመገልገል መንገድ
በእግዚአብሄር መንግስት ባለን ነገር ሁሉ ለማገልገልና ሌሎችን ለመጥቀም የምንኖረው ኑሮ ሲሆን የአለም አስተሳሰብ በስልጣናችን ተጠቅመን ለመጠቀምና ሰዎች እንዲያገለግሉንና እንዲጠቅሙን የምንሄድበት አስተሳሰብ ነው፡፡
5)    የመዝራትና የማከማቸት አስተሳሰብ
የእግዚአብሄር መንግስት የመዝራትና የመስጠት አስተሳሰብ ነው፡፡ የእግዚአብሄር መንግስት ሌሎችን በመባረክና በማንሳት የሚረካ አስተሳሰብ ነው፡፡ በአለም ግን ሰው ደህንነት የሚሰማው ሲያከማች ሲሰበስብ ነው፡፡
ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ፤ ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ፤ ማቴዎስ 6፡19-20
6)    የይቅርታና የበቀል አካሄድ
የእግዚአብሄር መንግስት የምህረትና የይቅርታ መንግስት ነው፡፡ የእግዚአብሄር መንግስት በእጅጉ ይቅር የተባሉ ሰዎች በተራቸው ሌላውን ይቅር ለማለት የተዘጋጁ ሰዎች መንግስት ነው፡፡ የአለም መንግስት ግን የበቀልና የተንኮል አስተሳሰብ የገነነበት ሲሆን አንዱ በሌላው ላይ ተረማምዶ ወደላይ ከፍ የሚልበት ክፉ አሰራር ነው፡፡ በአለም አስተሰታሳብ በፊትህ የሚቆመውን አስወግደህ ማለፍ አዋቂነት ነው፡፡  
7)    የመተባበርና የፉክክር አስተሳሰብ
በእግዚአብሄር መንግስት ለሌላው መነሳትና ማሸነፍ በደስታ የሚሰራበት ሲሆን በአለም አሰራር ግን ሌላውን በመጣል ከሌላው በላይ ከፍ ብሎ ለመታየት በትእቢት የሚኬድበት የአሰራር ዘይቤ ነው፡፡ የእግዚአብሄር መንግስት የሌላውን ጉድለት ለመሙላት የመሄድ አስተሳሰብ ሲሆን የአለም አስተሳሰብ ሌላው ሁሉ ለእርሱ እንዲሰራለት ራስን ብቸኛ እንደተመረቀ መቁጠር ነው፡፡  
8)    ዘላለማዊና ጊዜያዊ አስተሳሰብ
የእግዚአብሄር መንግስት አስተሳሰብ የሚመዘነው በዘላለማዊ እይታው ነው፡፡ የእግዚአብሄር መንግስት ዜጋ ለዘላለም ከእግዚአብሄር ጋር እንደሚኖር የእግዚአብሄር ልጅ ጊዜያዊውን ደስታ ንቆ የሚኖረበት ህይወት ነው፡፡ የአለም አስተሳሰብ ግን ለጊዜያዊው ነገር ህይወትን የማባከን ህይወት ነው፡፡
9)    የትህትናና የትእቢት አስተሳሰብ
የእግዚአብሄር መንግስት መዋረድና የዝቅታን አስተሳሰብን ሲያስተምር የአለም አስተሳሰን ግን የትእቢት የከፍታ የንቀትና  አስተሳሰብን ያራምዳል፡፡ በአለም አሰራር ትህትና ሽንፈትና ደካማነት ነው፡፡
10)   የየዋህነትና የብልጠት አካሄድ
የእግዚአብሄር መንግስት አስተሳሰብ ሃይልን ለክፉ ነገር ያለመጠቀም ውሳኔ ሲሆን በአለም ግን ብልጠትና አቋራጭ ተጠቅሞ ወደላይ ከፍ ማለትን የሚያበረታታ አሰራር ነው፡፡ የእግዚአብሄር መንግስት ሰው ስለ ደህንነቱ በእግዚአብሄር ላይ የሚደገፍበት ሲሆን የአለም አሰራር ግን ባለህ ሃይል እና ተሰሚነት ሁሉ ተጠቅመህ ሌላውን በመጣልና በማዋረድ ከፍ የማለት አስተሳሰብ ነው፡፡ በአለም አንተ ከፍ እንድትል ሌሎች መዋረድ አለባቸው፡፡
ስለዚህ ነው ኢየሱስ የእግዚአብሄር መንግስት ቀርባለችና ንስሃ ግቡ እያለ ይሰብክ የነበረው፡፡ በአለም አስተሳሰብ በእግዚአብሄር መንግስት ሊሳካልን አይችልም፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ንስሃ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #አለም #ሃጢያት #ድምፅ #ቅባት #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #የህይወትፍሬ #መናገር #ቅባት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment