Popular Posts

Monday, May 8, 2017

የስህተት ገድል

በህይወታችን በፍፁም መሳተፍ የሌለብን መልካም ያልሆኑ የገድል አይነቶች አሉ፡፡ እንደ እነዚህ አይነት የገድል አይነቶች ውስጥ መሳተፍ አላስፈላጊ ዋጋ ያስከፍለናል፡፡ በተሳሳተ ገድል ላይ መካተት ህይወታችን ፍሬ ቢስ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ መልካሙን ገድል እንድንጋደል እንጂ መልካም ያልሆነውን ገድል አንዳንጋደል መፅሃፍ ቀዱስ በብርቱ ያስጠነቅቀናል፡፡ ለመልካም ገድል በቂ ፀጋና ሃይል ተሰጥቶናል፡፡ ነገር ግን መልካም ያልሆነውን ተጋድሎ ስናደርግ እግዚአብሄር ከእኛ ጋር አይሆንም እንዲሁ እንደክማለን እንጂ ምንም ውጤተ አናገኝም፡፡     
መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል፥ 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡12
1.      ስለደረሰብን በደል ራስ የመበቀል ገድል
እግዚአብሄር የሁላችን ፈራጅ ነው፡፡ ሰው ግን እራሱን በእግዚአብሄር ቦታ ከፍ አድርጎ እንደፈራጅ ሲሆን እግዚአብሄር አብሮት አይሆንም፡፡ የእግዚአብሄርን ቦታ ወስዶ ፈራጅ ለመሆን መሞከር ብክነትና ፍሬ ቢስነት ነው፡፡ ሰው ምንም ቢበደል ለእግዚአብሄር ፈራጅነት ስፍራ መስጠት አለበት እንጂ ራሱ የመበቀል ተጋድሎ ውስጥ መግባት የለበትም፡፡  
ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን አስቡ። ተወዳጆች ሆይ፥ ራሳችሁ አትበቀሉ፥ ለቍጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና። ሮሜ 12፡17፣19
ሕግን የሚሰጥና የሚፈርድ አንድ ነው፤ እርሱም ሊያድን ሊያጠፋም የሚችል ነው፤ በሌላው ግን የምትፈርድ አንተ ማን ነህ? ያዕቆብ 4፡12
2.     ሰውን እንደምንጭ የመመልከትና ተስፋ የማድረግ ገድል
የበጎ ነገር ሁሉ ምንጭ እግዚአብሄር ነው፡፡ ሰው ግን ስለ መልካም ነገርና እድገት ስለማግኘት ወደ እግዚአብሄር ማየት ትቶ ወደ ሰው ካየና ሰውን ተስፋ ካደረገ ስለዚህ ስህተቱ አላስፈላጊ ዋጋ ይከፍላል፡፡ የሰው በረከት በእግዚአብሄር እጅ ነው፡፡ የእርሱን እጣ ፈንታ የያዘው ሰው እንደሆነ አድርጎ ከሰው ጋር ከተጋደለ ህይወቱን በከንቱ ያባክናል፡፡
በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን? ትመኛላችሁ ለእናንተም አይሆንም፤ ትገድላላችሁ በብርቱም ትፈልጋላችሁ፥ ልታገኙም አትችሉም፤ ትጣላላችሁ ትዋጉማላችሁ ነገር ግን አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም፤  ያዕቆብ 4፡1-2
3.     ሰውን የመጥላት ገድል
እግዚአብሄር የፈጠረንና ዲዛይን ያደረገን ለፍቅር ነው፡፡ እግዚአብሄር የሰጠን ፀጋ ሰውን ለመውደድ በቂ ነው እንጂ ሰውን ለመጥላት አይተርፍም፡፡ ሰውን የምንጠላውና በሰው ላይ ክፋትን ለማድረግ የምንተጋው በራሳችን ወጭ ነው፡፡ ሰውን ለመጥላት የምናደርገው ማንኛውም ተጋድሎ ውጤት የሌለውና የአቅም ብክነት ብቻ ነው፡፡
ክፉን በክፉ ፈንታ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ በዚህ ፈንታ ባርኩ እንጂ፥ በረከትን ልትወርሱ ለዚህ ተጠርታችኋልና። 1ኛ ጴጥሮስ 3፡9
4.     በቅንጦት ለመኖር የሚደረግ ተጋድሎ
እግዚአብሄር እረኛችን ነው የሚያሳጣን አንድም ነገር የለም፡፡ ነገር ግን ከመሰረታዊ ፍላጎት አልፈን የምንፈልገውንና በምቾትና በቅንጦት ለመኖር በምናደርገው ተጋድሎ ጉዞ እግዚአብሄር አብሮን ስለማይሆን ከባድ ዋጋ ያስከፍለናል፡፡ እግዚአብሄር የሰጠን ነገር ሳይበቃን ሲቀር እጃችንን ዘርግተን እግዚአብሄር ያልሰጠንን ከወሰድን እግዚአብሄር አብሮን አይቆምም፡፡ ይህ ለቅንጦት ኑሮ እና ለኑሮ ትምክት የሚደረግ ተጋድሎ እግዚአብሄር የሌለበትና እኛው በራሳችን የምናደርገው ስለሆነ ውጤት የሌለው ድካም ነው፡፡
ትለምናላችሁ፥ በምቾቶቻችሁም ትከፍሉ ዘንድ በክፉ ትለምናላችሁና አትቀበሉም። ያዕቆብ 4፡3
ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፥
አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል። 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡6-8
5.     እግዚአብሄር ያላለንን ለማድረግ ያለ ተጋድሎ
እግዚአብሄር በስራ ላይ ነው፡፡ ለእግዚአብሄር የአገልግሎት ሃሳብ አንሰጠውም፡፡ እግዚአብሄር ነገሮች እንዴት መሆን እንደለባቸው ያውቃል፡፡ እግዚአብሄር ዘወትር በስራ ላይ ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ስራ ለመስራት እግዚአብሄር በህይወታችን ያሰበውን በነገር ማግኘት አለብን፡፡ የእግዚአብሄርን ስራ ለመስራት አስቀድሞ ያዘጋጀልንን ስራ ከእርሱ ከራሱ ፈልገን ማግኘትና መረዳት አለብን፡፡ ሰው ግን በራሱ አነሳኝነት እግዚአብሄር እንደዚህ ሳይፈልግ አይቀርም ብሎ መልካም የመሰለውን ነገር ለእግዚአብሄር ለማድረግ የሚያደርገው ተጋድሎ እግዚአብሄር ጎሽ የማይለው ከንቱ ተጋድሎ ነው፡፡
ስለዚህ ኢየሱስ መለሰ እንዲህም አላቸው፦ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም፤ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋልና። እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም፤ እንደ ሰማሁ እፈርዳለሁ ፍርዴም ቅን ነው፥ የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻምና። ዮሃንስ 5፡19፣30
መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል፥ 1 ጢሞቴዎስ 612
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እምነት #ማየት  #ቃል #የሰውበቀል #ቅንጦት #ጥላቻ #የእምነትተጋድሎ #የእግዚአብሄርቃል #ቃሉንመስማት #እወጃ #ማስተዋል #ማሰላሰል #መናገር #መፅናት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

No comments:

Post a Comment