Popular Posts

Friday, February 24, 2017

የድንጋይ ልብ

ወንድሞች ሆይ፥ ምናልባት ሕያው እግዚአብሔርን የሚያስክዳችሁ ክፉና የማያምን ልብ ከእናንተ በአንዳችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፤ ዕብራውያን 312
ልብ በጣም ወሳኙ የሁለንተናችን ማእከላዊ ክፍል ነው፡፡ ልብ ከጠነከረ ሁሉም ነገር ይጠነክራል፡፡ ልብ ከሳሳ ደግሞ ሁሉም ነገር ይሳሳል፡፡ ልብ እግዚአብሄርን ማመን ካቃተው ነገር ሁሉ ይበላሻል፡፡ እግዚአብሄርን የሚታመን ስስ የስጋ ልብ ካለን ደግሞ ሁሉም ነገር የሰመረ ይሆናል፡፡  
ስለዚህ ነው ኢየሱስን ስንቀበል ልባችን የሚለወጠውና የድንጋይ ልባችን በስጋ ልብ የሚተካው፡፡ ጭካኔን ትተን ርህራሄን የምንለብሰው ፣ ጭለማን ገፍፈን ብርሃንን የምንታጠቀው ፣ ጥላቻን ትተን ፍቅርን የምንለማመደው ልባችን በጌታ በመለወጡ ነው፡፡  የድንጋይ ልብ ደግሞ የሚባለው ለእግዚአብሄር ነገር ምንም ቅናት የሌለው ፣ እሳቱ የጠፋበት ፣ ለእግዚአብሄር ነገር ግድ የሌለው እምነቱ የጠፋበት በጥርጥር የተሞላ ልብ ነው፡፡ ልበ ጠንካራ ሰው ትሁት መሆን ያቃተው ፣ አንገተ ደንዳና ፣ ለእግዚአብሄር እሺ የማይልና ለቃሉ የማይንቀጠቀጥ የእልከኛ ሰው ልብ ነው፡፡
ዛሬ ድምፁን ብትሰሙት ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ በፊት እንደ ተባለ፥ ይህን ከሚያህል ዘመን በኋላ በዳዊት ሲናገር፦ ዛሬ ብሎ አንድ ቀን እንደ ገና ይቀጥራል። ዕብራውያን 4፡7
የህይወት መውጫ ከእርሱ ዘንድ ነውና ልብንህን ጠብቅ ብሎ መፅሃፍ ቅዱስ ያስተምረናል፡፡  
አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፥ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና። ምሳሌ 4፡23
ልባችንን እንዴት እንድንጠብቅ መፅሃፍ ቅዱስ ያስተምራል፡፡ ልባችንን የምንጠብቅበት መንገድ እለት በእለት በመትጋተ መሆኑን የእግዚአብሄር ቃል ያስተምረናል፡፡
ልቡን አለመጠበቅ ያለበት ሰው የለም፡፡ ማንም ሰው ከዚህ አደጋ ነፃ አይደለም፡፡ ከክፉና እልከኛ ልብ የምንድነው እለት በእለት በትጋት ስንሰበሰብና ስንመካከር ብቻ ነው፡፡ ማንም እኔ ይሄ አይነካኝም በሚል አጉል ትምክት በእያንዳንዱ ቀን በእግዚአብሄር ቃል መመካከሩን ቸል ቢል ሳያውቀው ክፉና እግዚአብሄርን የሚያስክድ ልብ ይኖረዋል፡፡
ወንድሞች ሆይ፥ ምናልባት ሕያው እግዚአብሔርን የሚያስክዳችሁ ክፉና የማያምን ልብ ከእናንተ በአንዳችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፤ ነገር ግን ከእናንተ ማንም በኃጢአት መታለል እልከኛ እንዳይሆን፥ ዛሬ ተብሎ ሲጠራ ሳለ፥ በእያንዳንዱ ቀን እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ፤  ዕብራውያን 3፡12-13
እግዚአብሄርን የሚያምን ፣ ለእግዚአብሄር ቃል ስስ የሆነ ፣ የዋህና የስጋን ልብ ለመጠበቅ ትጋት ይጠይቃል፡፡ አጥብቀን እንጂ በቸልታና በስንፍና ልባችንን አንጠብቅም፡፡ ልባችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ተለውጧል ፡፡ ያንን የተለወጠ የስጋ ልብ ፣ የሚያምን ልብ መጠበቅ ግን የእየለቱ ትጋታችንን ይጠይቃል፡፡
ይህንን ፅሁፍ ሼር ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ተመካከሩ #ከሃዲ #እልከኛ #ልብ #ቃል #ምስጉን #ሃሳብ #ማሰላሰል #ወንጌል #ደቀመዝሙር #ኢየሱስ #ጌታ #መዳን #አማርኛ #ኢትዮጲያ #አቢይዋቁማ #ፌስቡክ #አዋጅ

No comments:

Post a Comment