Popular Posts

Sunday, February 26, 2017

የወንድሞች ህብረት ሽቱ

ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ፥ እነሆ፥ መልካም ነው፥ እነሆም፥ ያማረ ነው። ከራስ እስከ ጢም እንደሚፈስስ፥ እስከ አሮን ጢም፥ በልብሱ መደረቢያ እንደሚወርድ ሽቱ ነው። በጽዮን ተራሮች እንደሚወርድ እንደ አርሞንዔም ጠል ነው፤ በዚያ እግዚአብሔር በረከቱን ሕይወትንም እስከ ዘላለም አዝዞአልና። መዝሙር 133፡1-3
ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ያለው ግንኙነትና ህብረት ወሳኝ ነው፡፡ ሰው ለእግዚአብሄር ክብር ስለተፈጠረ ከእግዚአብሄር ጋር ህብረት ከሌለው ህይወቱን በከንቱነት ያሳልፋል፡፡
ለእግዚአብሄር ከብር የሚኖሩ ወንድሞች ደግሞ እርስ በእርሳቸው ያላቸው ግንኙነት እንዲሁ ወሳኝ ነው፡፡ የእኛ በህብረት መቀመጣችን እግዚአብሄርን ያስደስተዋል፡፡እግዚአብሄር በእኛ አንድነት ደስ ይሰኛል፡፡
እግዚአብሄር በመልኩና በአምሳሉ ፈጥሮናል፡፡ እኛ ስሜት እንዳለን ሁሉ እርሱም ስሜት አለው፡፡ እኛን ደስ የሚለን ነገር እንዳለ ሁሉ እርሱንም ደስ የሚለው ነገር አለ፡፡ እርግጥ ነው ሰውን ደስ የሚያሰኘው ነገር ሁሉ እግዚአብሄርን ደስ አያሰኘውም ፡፡ ሰውን የሚያስደንቀው ነገር ሁሉም እግዚአብሄርን አያስደንቀውም፡፡ ሰውን የሚያምረን ነገር ሁሉ እግዚአብሄርን አያምረውም፡፡  
እግዚአብሄርን የሚያስደስተው ነገር የወንድሞች ህብረት ነው፡፡ ሽቱ መልካም ስሜት እንደሚፈጥር ሁሉና ደስ እንደሚያሰኝ ሁሉ የወንድሞች ህብረት እግዚአብሄርን ደስ ያሰኘዋል፡፡ የአርሞንዔም ጠል ምድሩን እንደሚያለመልመው ሁሉና ምድሩን እንደሚያረካው የወንድሞች ህብረት እግዚአብሄርን ያረካዋል፡፡
እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች ይዘረዝርና ሰባተኛውን በወንድሞች ህብረት ላይ የሚሰራውን በደል ነፍሱ አጥብቃ እንደምትጠየፈው መፅሃፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡
እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች ናቸው፥ ሰባትንም ነፍሱ አጥብቃ ትጸየፈዋለች፤ በሐሰት የሚናገር ሐሰተኛ ምስክር፥ በወንድማማች መካከልም ጠብን የሚዘራ። ምሳሌ 619
ስለዚህ ነው እግዚአብሄርን ለማስደሰትና የወንድሞችን ህብረት ለመጠበቅ ትጋት እንደሚጠይቅ መፅሃፍ ቅዱስ የሚያስተምረው፡፡
በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ። ኤፌሶን 4፡3
ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ፥ እነሆ፥ መልካም ነው፥ እነሆም፥ ያማረ ነው። ከራስ እስከ ጢም እንደሚፈስስ፥ እስከ አሮን ጢም፥ በልብሱ መደረቢያ እንደሚወርድ ሽቱ ነው። በጽዮን ተራሮች እንደሚወርድ እንደ አርሞንዔም ጠል ነው፤ በዚያ እግዚአብሔር በረከቱን ሕይወትንም እስከ ዘላለም አዝዞአልና። መዝሙር 1331-3
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ወንድሞች #ፍቅር #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #ህብረት #ግንኙነት #ሽቱ #ያማረ #በፍፁምሃይል #መውደድ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ


No comments:

Post a Comment