Popular Posts

Saturday, February 11, 2017

እጅግ ውጤታማው የጦር መሳሪያ

በሰው ልማድ ምንም እንኳ የምንመላለስ ብንሆን፥ እንደ ሰው ልማድ አንዋጋም፤ የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፥ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው፤ የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን፥ 2 ቆሮንቶስ 10፡3-5
ስልጣን እስከሚሰራ ድረስ አይታይም፡፡ ስልጣን የሚታየው ሲሰራና እርምጃ ሲወስድ ብቻ ነው፡፡
እኛ የክርስቶስ ኢየሱስ ተከታዮች ደግሞ እንደማንኛውም የምድር ነዋሪወች ነው የምንኖረው፡፡ የምንኖረው እንደሰው ልማድ ነው፡፡ እንደ ሰው እንበላለን ፣ እንደሰው እንለብሳለን ፣ እንደሰው እንተኛለን፡፡ ያ ማለት ግን መንፈሳዊ ስልጣን የሌለን ተራ ሰዎች ነን ማለት አይደለንም፡፡
እኛ የእግዚአብሄ ልጆች የሆንን ሁሉ ታላቅ ስልጣን አለን፡፡ (ዮሃንስ 1፡12) እንደ ሰው ልማድ ብንመላለስም ወደ ስልጣን ወደ ውጊያ ወደ ማሸነፍ ሲመጣ ግን እንደሰው ልማድ አንዋጋም፡፡ የጦር እቃችንም ስጋን ብቻ መግደል የሚችል ስጋዊና ምድራዊ አይደለም፡፡ የጦር እቃችን በምድር ላይ እጅግ ከተራቀቀ ከባድ የጦር መሳሪያ ይልቅ እጅግ ውጤታማ ነው፡፡   
የጦር እቃችን ማንኛውንም ነገር መለወጥ የሚችል በእግዚአብሄር ፊት ብርቱ ነው፡፡ የጦር እቃችንን ሊቋቋም የሚችል ጠላት የለም፡፡ ስልጣናችንን ስንጠቀም ፊታችን ሊቆም የሚችል ማንም አይኖርም፡፡
የጦር እቃችን ምሽግን ለመስበር በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው፡፡ በሰው ፊት ምንም ላይመስል ይችላል በእግዚአብሄር ዘንድ ግን ሃያል ነው፡፡ ሰው ሊንቀው ይችላል በእግዚአብሄር ፊት ግን ብርቱ ነው፡፡ በምድራዊ አለም ምንም ላይመስል ይችላል በሰማያዊው አለም ግን እጅግ የተከበረ ነው፡፡
ምሽግ በጦርነት ሜዳ ለማሸነፍ እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነገር ነው፡፡ ጠላት ከመሸገ ለመሸነፍ ያለው እድል ትንሽ ነው፡፡ ነገር ግን የጦር እቃችን ምሽግን ለመስበር ብርቱ ነው፡፡ የጦር እቃችን የሚስተው የጠላት ኢላማ የለም፡፡ የጦር እቃችን የማይደመስሰው የተመሸገ የጠላት ጦር የለም፡፡
የሰይጣን ትልቁ ምሽግ ደግሞ እንደ እግዚአብሄር ቃል ያልሆነ ክፉ ሃሳብን የሚያስተናግድ የሰው አእምሮ ነው፡፡ የሰይጣን ትልቁ የጦር መሳሪያ የሰው ሃሳብ ነው፡፡ የሰይጣን ትልቁ መደበቂያ ምሽግ የሰው አእምሮ ነው፡፡ የሰይጣን ትልቁ ምሽግ በእግዚአብሄር ቃል ያልታደሰ ፣ ስርአት የሌለውና እንዳመጣለት የሚያስብ አእምሮ ነው፡፡
ሰይጣን የሰው ጠላት ነው፡፡ ሰይጣን ወደ ሰው ሲመጣ የሚመጣው ወይ ለመስረቅ ወይ ለማረድ ወይ ለማጥፋት ነው፡፡ (ዮሃንስ 10፡10) ሰይጣን ከዚህ ውጭ ምንም አላማ የለውም፡፡ ሰይጣን የሰውን ህይወት የማጥፋት አላውን የሚፈፅምበት ብቸኛው መንገድ ሃሳቡን ወደሰው አአምሮ በመላክ በመመሸግ ነው፡፡  
ሰይጣን በኢየሱስ ሞት ሙሉ ለሙሉ ድል ተነስቷል፡፡
አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው። ቆላስይስ ሰዎች 2፡15
ሰይጣን ድል ስለተነሳ በማታለል እንጂ በግድ የሚያደርገው ነገር የለም፡፡ ሰይጣን ድል ስለተነሳ አሁን የቀረው መሳሪያ ሃሳብን ወደሰው አእምሮ መላክና የሚቀበለው ሰው ካገኘ በአእምሮ በመመሸግ የሰውን ህይወት ማጥቃት ነው፡፡
ሰይጣን ሃሳቡ ተቀባይነት ካላገኘ ሰውን ሊያጠቃ በፍፁም አይችልም፡፡ ሰይጣን ደግሞ በሰው ውስጥ ሃሳቡን ልኮ ተቀባይነት ካገኘ ሰውን እንደልቡ ማጥቃት የሰውን ህይወት መስረቅ ማረድና ማጥፋት ትችላል፡፡
ይህ እግዚአብሄር የሰጠን ስልጣን የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ ለማፍረስ ብቁ ነው፡፡
በሰው ልማድ ምንም እንኳ የምንመላለስ ብንሆን፥ እንደ ሰው ልማድ አንዋጋም፤ የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፥ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው፤ የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን፥ 2ኛ ቆሮንቶስ 10፡3-5
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ፍቅር #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #የጦርመሳሪያ #ምሽግ #አእምሮ #ሃሳብ #ማታለል #ብርቱ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ




No comments:

Post a Comment