Popular Posts

Friday, February 17, 2017

እውነተኛ አርነት

ኢየሱስም ያመኑትን አይሁድ፦ እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል አላቸው። ዮሐንስ 8፡31-32
እንደ አርነት ጣፋጭ ነገር የለም፡፡ ነፃነት ይጠፍጣል፡፡ የተፈጠርንበትን አላማ እንደ ማግኘት ያለ ነፃነት የለም፡፡ እንደ አፈጣጠራችን መኖርን የመሰለ ነገር የለም፡፡
ኢየሱስ ያመኑትን በቃሌ ብትኖሩ ነፃ ትወጣላችሁ ይላቸዋል፡፡ ነፃ እንድንወጣ ቃሉን መለማመድ ወሳኝ ነው፡፡ ነፃ መውጣት  ጌታን የተቀበልን ቀን በቅፅበት አግኝተን የምንጨርሰው ነገር አይደለም፡፡ ነፃ መውጣት በቃሉ በመኖር ውስጥ የምንለማመደው አርነት ነው፡፡
በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ ያለው ነፃነት ሰፊ ነው፡፡ በክርስቶስ ያለው የነፃነት መጠን ተዝቆ የሚያልቅ አይደለም፡፡ በህይወታችን ነፃ ያለወጣንበት ነገር ቢኖር የእግዚአብሄር መንግስት የነፃነት ጉድለት አይደለም፡፡ የእግዚአብሄር መንግስት ነፃነት ብዛቱ "ይህ ሁሉ ነፃነት አለ?" ብለን እንድንገረም ያደርገናል፡፡ ይህን ነፃነት ማጣጣም የሚቻለው በቃሉ በመኖር ብቻ ነው፡፡
ቃሉ እውነት ነው፡፡ የእኛን እውነተኛ ተፈጥሮና ማንነታችንን በትክክል የሚያሳየን ቃሉ ብቻ ነው፡፡ የተፈጠርንበትን ዲዛይን በተክክል የሚነግረን ቃሉ ብቻ ነው፡፡ በመጀመሪያ እንዴት እንደተፈጠርንና ለምን አላማ ወደምድር እንደመጣን የሚያሳየን ቃሉ ብቻ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ዘንድ ያለንን ክብር ሊያሳየን የሚችው ቃሉ ብቻ ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ፈቃድ የሚነግረን ቃሉ ብቻ ነው ፡፡
እነዚህ ነገሮች ለእናንተ ሆነው ቢበዙ፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች እንዳትሆኑ ያደርጉአችኋልና፤ 2ኛ ጴጥሮስ 1፡8
ከአላማ ቢስነት እስራት የሚፈታን ቃሉ ብቻ ነው፡፡ ከፍሬ ቢስነት ባርነት ሊያስለቅቀን ብቃቱ ያለው ቃሉ ብቻ ነው ፡፡ እረኛ እንደሌለው በግ እንዳንቅበዘበዝ ወደ እረኛችን የሚመልሰን ቃሉ ብቻ ነው፡፡ ትኩረታችንን ትክክለፃ ቦታ ላይ በማድረግ ውጤታማ የሚያደርገን ቃሉ ብቻ ነው፡፡ እውነተኛን ስኬት የሚሰጠን ቃሉን በመኖር ብቻ ነው፡፡ ለህይወታችን እውነተኛ ብልፅግናን የሚሰጠው ቃሉ ብቻ ነው፡፡ የእውነተኛ ነፃነት ምንጭ ቃሉ ብቻ ነው፡፡
እንግዲህ ልጁ አርነት ቢያወጣችሁ በእውነት አርነት ትወጣላችሁ። ዮሃንስ 8፡36
ከቃሉ ውጭ ነፃነትን መጠበቅ ብከነት ነው፡፡ ካለቃሉ አርነት ለመውጣት መሞከር ከንቱ ነው፡፡ ካለቃሉ እውነተኛ ስኬትን ማግኘት ዘበት ነው፡፡
አልሁም፦ ቃሌን ስሙ፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ አድርጉ፤ እንዲሁም እናንተ ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ። ኤርምያስ 11
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ቃል #መታዘዝ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና #እምነት #መስማት #መከተል #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment