Popular Posts

Tuesday, February 28, 2017

እንቅጩን የሚናገር መስተዋት

ስለዚህ ርኵሰትን ሁሉ የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ፥ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ። ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ። ቃሉን የሚሰማ የማያደርገውም ቢኖር የተፈጥሮ ፊቱን በመስተዋት የሚያይን ሰው ይመስላል፤ ራሱን አይቶ ይሄዳልና፥ ወዲያውም እንደ ምን እንደ ሆነ ይረሳል። ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹሙን ሕግ ተመልክቶ የሚጸናበት፥ ሥራንም የሚሠራ እንጂ ሰምቶ የሚረሳ ያልሆነው፥ በሥራው የተባረከ ይሆናል። ያዕቆብ መልእክት 1፡21-25
እግዚአብሄር ቃሉን የሰጠን እንድናደርገው ነው፡፡ ቃሉን ስናደርገው ብቻ ነው የሚጠቅመን፡፡ መዋጥ የሚገባንን መድሃኒት ባንውጠውና ከሰውነታችን ጋር ባናዋህደው እንደማይጠቅመን ሁሉ ቃሉም የሚጠቅመን በተግባር ስናደርገውና ከእኛ ጋር ሲዋሃድ ብቻ ነው፡፡
ቃሉን መስማትና ማወቅ ወሳኝ ነው፡፡ ነገር ግን በህይወታችን በእውነት አወቅነው የምንለው ቃል የተገበርነውን ቃል ብቻ ነው፡፡ ምክኒያቱም ፍሬያማ የሚያደርገን የተገበርነው ቃል ብቻ ነው፡፡ ቃሉ በውስጡ ነፃ የሚያወጣ የተጠራቀመ ጉልበት አለው፡፡ ያ የተጠራቀመ ሃያል ጉልበት ሊሰራልን የሚችለው እኛ ውስጥ ሲተገበርና በህይወታችን ስናደርገው ብቻ ነው፡፡ ወሳኙ ውድድር የመስማትና የማወቅ ብቻ ሳይሆን የማድረግም ነው፡
የሰማነው ግን ያልተገበርነው ቃል የእኛ አይደለም፡፡ ያልተገበርነው ቃል እንዲያውም ያታልለናል፡፡ ወይ አላወቅኩትም ብለን እውቀቱን አንፈልግም፡፡ ወይም ደግሞ አውቀነው አልተጠቀምንበት፡፡ ስለዚህ በመሃል ቤት እንቀራለን ራሳችን እናታልላለን፡፡
ሰው ቤቱ ውስጥ ምርጥ መስታወት አስቀምጦ ነገር ግን ያየውን ነገር ቶሎ ካላስተካከለው የመስታወቱ ጥቅም ምኑ ላይ ነው፡፡ እንዲሁም ሰው ቃሉን ሰምቶ ቶሎ መንገዱን ካልወጠና እንደቃሉ ካልተገበረው ቃሉን መስማት ብቻ ምንም አይጠቅመውም፡፡ የሰማው ቃል በእውነት የሚጠቅመው ያደረገው ጊዜ ነው፡፡  
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ቃል #መታዘዝ #አማርኛ #ስብከት #መስተዋት #መፅሃፍቅዱስ #ነፃነት  #እምነት #መስማት #መከተል #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment