Popular Posts

Follow by Email

Sunday, February 19, 2017

ምግብ ያለ ጨው


እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፍጣል? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ወደ ፊት ለምንም አይጠቅምም። ማቴዎስ 5፡13
ምግብ ለመበላት ሊጣፍጥ ይገባዋል፡፡ ምግብ የማይጣፍጠው ከሆነ ሰው ለመብላት አይበረታታም፡፡ ምግብን ለማጣፈጥ የሚጠቅመው ዋነኛው ነገር ደግሞ ጨው ነው፡፡ ጨው የምግብ ጣእምን ሰብሰብ የማድረግ አቅም አለው፡፡ ጨው የምግብ ጣእምን ወደ አንድ ደረጃ የማምጣት ችሎታ አለው፡፡ ምግብ የተለያየና እንግዳ ጣእም እንዳይኖረው ጨው መጨመር እጅግ ይጠቅማል፡፡ ጨው የሚስብ ነገር አለው፡፡ ጨው በሁሉ ሰው ታዋቂና ተፈላጊ ጣእም አለው፡፡ ምንም ያህል ድግስ ተደግሶ የሚያጣፍጥ ጨው ከሌለው በጣም ታሪካዊ ድግስ ይሆናል፡፡
ልክ ከእግዚአብሄር ጋር በክርስቶስ የመስቀል ስራ እንደታረቅን ወደ መንግስተ ሰማያት ያልገባነው በምድር ላይ ወሳኝ ስራ ስላለን ነው፡፡ ስለ ተከታዮቹ ኢየሱስ ሲናገር የምድር ጨው ናችሁ ይላል፡፡ ጨው የምግብን ደረጃ ከፍ እንደሚያደርገው እኛ የምድርን የህይወት ደረጃ ከፍ እናደርገዋለን፡፡ እኛ እግዚአብሄርን የመፍራት ከፍ ያለ የህይወት ደረጃ ካላሳየን ምድር እግዚአብሄርን ፈርቶ የሚያስፈራራው ምሳሌ አይኖረውም፡፡ እግዚአብሄርን የመምሰል ህይወት ምሳሌ ካልሆንን ምድር የእግዚአብሄርን መልክ ማየት አትችልም፡፡ እኛ እግዚአብሄርን ስለማክበር ሞዴል ካልሆንን እግዚአብሄር እንዴት እንደሚከበር ምንም ፍንጭ አይኖረውም፡፡ በእግዚአብሄር ፀጋ በራስ የማይቻል ነገር በማድረግ እግዚአብሄር እንዳለ ካልመሰከርን ስለእግዚአብሄር መኖር የሚመሰክር ሰው አይኖርም፡፡   
ጨው የምግብንን የተለያየ ጣእም እንደሚሰበስበውና አንድ ወጥ ጣእም እንደሚሰጠው እኛም የምድርን ትኩረት ወደ ሰማይ የምናመለክተው እኛ ነን፡፡ እንዲሁም ከሞት በኋላ ህይወት አንዳለ አድርገን በመኖር ሌሎችንም የምናነቃውና ምድራዊ ህይወት ጊዜያዊ እንደሆነ አድርገን በመኖር ሌሎቹ ለዘላለማዊ ህይወት እንዲዘጋጁ የምናስጠነቅቀው እኛ ነን፡፡ በሰማይ ጌታ እንዳለው ሰው በመኖር ራስን በመግዛትና በዲሲፒን ኑሮ ክርስትና እንደሚቻል ፣ እግዚአብሄርን ማስደሰት እንደሚቻልና ለእግዚአብሄር ሙሉ ለሙሉ መኖር እንደሚቻል ለሌሎች ምሳሌ የምንሆነው እኛው ነን፡፡
ሰው በእግዚአብሄር አምሳል እንደተፈጠረና ለእግዚአብሄር ክብር እንደተሰራ በህይወታችን የምናመለክተው እኛ ነን፡፡  እግዚአብሄርን ማክበር የሰው በምድር ላይ የመፈጠር አላማ  መሆኑን የምናስታውሰው እኛ ነን፡ምድርን ከሚታይ ነገርና ከስጋዊ ፍላጎት ከፍ ያለን ደረጃ የምንሰጣት እኛ የምድር ጨው ነን፡፡ በምድር ላይ የእግዚአብሄር ልጅ ሆኖ ስለመኖር ለሌሎች የምንመሰክረው እኛ ነን፡፡ በምድር ላይ እግዚአብሄርንና ሰውን በመውደድ እንዴት እንደሚኖር የምንመሰክረው እኛ ነን፡፡
ጨው ክብሩ ለምግብ ጣእም መስጠቱ ነው፡፡ የጨው ክብሩ ኮስታራነቱ ነው፡፡ እኛ ነን አለምን ማጣፈጥ የምንችለው፡፡ አለምን ለማጣፈጥ ጣእሙ ያለን እኛ ነን፡፡ እኛ ግን ይህንን ወሳኝ ሃላፊነታችንን ካልተወጣን ማንም ሊሰራልን አይችልም፡፡ እኛ አለምን ካላጣፈጥን እኛን ሊያጣፍጠን የሚችል አለም የለም፡፡ ጨው ደግሞ ካላጣፈጠ ለምንም አይጠቅምም፡፡
ስለዚህ ነው ጨው በአለም ሁሉ መበተን ያለበት፡፡ ጨው በጨው እቃ ውስጥ ቢቀመጥ ምንም አይጠቅምም፡፡ ጨው ግን ተለያየ አይነት ወጥ ውስጥ ቢጨመር ያጣፍጣል፡፡ ስለዚህ ነው ክርስትያኖች የምንሰበሰበው ለመበረታታት ፣ ለመሞረድ ፣ ለመታደስ እንጂ ስራው በምድር ፖለቲካ ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ህይወት ውስጥ ነው፡፡ ጨውነታችን በትምህርት ቤት ፣ በሆስፒታል ፣ በእርሻ ፣ በሃገር አስተዳደር ፣ በውትድር ፣ በንግድና በመሳሰሉት ሙያዎችን ሁሉ ይፈለጋል፡፡
ክርስትናን ካለራስ ወዳድነት በፍቅር ለሌሎች መልካም ምሳሌ በመሆን ክርስትናን እንዲቀበሉ የምናበረታታው የምድር ጨው በመሆን ነው፡፡
እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፍጣል? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ወደ ፊት ለምንም አይጠቅምም። ማቴዎስ 513 
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ቃል #ጨው #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና #ምድር #መጣፈጥ #ጣእም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment