Popular Posts

Wednesday, February 8, 2017

አንድ አምላክ

ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ። ዘጸአት 20፡3
ይህንን ትእዛዝ ስንሰማ በጣም ቀላልና ማንም በቀላሉ ሊጠብቀው የሚችለው ይመስለናል፡፡ ይህን ትእዛዝ ስንሰማ እና ማን ሌላ አምላክ ያመልካል ብለን እንጠይቃለን፡፡
ነገር ግን አምልኮዋችንን የሚፈልጉ በየእለቱ የሚያስፈራሩን ስገዱልኝ ተከተሉኝ የሚሉ ፣ ካልሰገዳችሁልኝ አለቀላችሁ የሚሉን ብዙ ነገሮች በዙሪያችን አሉ፡፡ አንዳንድ ሰው ከእኔ በቀር ሌላ አማልክት አይሁኑልህ የሚለውን የሚያየው እንደ ሂንዱ እምነት ብዙ ጣኦቶች በእንጨት ሰርቶ አለማምለኩን ወይም ደግሞ ለዛፍና ለወንዝ አለመስገዱን ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን በአይን የማይታዩ ነገር ግን አይናችንን ከእግዚአብሄር ላይ እንድናነሳ ሊያደርጉ የሚችሉ ብዙ አማልክት አሉ፡፡
ሌላ አማልክት አይሁኑልህ ማለት የምትራው ሌላ ነገር አይኑር ማለት ነው፡፡
ሰው እንደ እግዚአብሄ የሚፈራው ነገር ካለ አምላክ ሆኖበታል፡፡ እግዚአብሄር የሚፈልገው እንድንፈራው ብቻ ሳይሆን ከእርሱ ውጭ ማንንም እንዳንፈራ ይፈልጋል፡፡
ፍርሃት ከቅጣት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የምንፈራው ሰው ይቀጣናል ብለን የምስበው ነው፡፡ በህይወታችን ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ የሚሰጠው እግዚአብሄር ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ከማንም በላይ እርሱን እንድንፈራው ይፈልጋል፡፡ ከእርሱ ውጭ ምንም እንዳንፈራ ይፈልጋል፡፡
ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ አትናወጡም፥ ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። 1ኛ ጴጥሮስ 3፡14፣15
ለምሳሌ ሰውን መፍራት በሰው ላይ መታመን ነው፡፡  ስለወደፊታችን የምንታመንበትን እድሌን ይወስናል ብለን የምናስበውን ሰው ብቻ ነው የምንፈራው፡፡ የምድሩንም የሰማዩንም የወደፊት እድላችንን ሊወስን የሚችለው እግዚአብሄር ብቻ ነው፡፡
ሰውን መፍራት ወጥመድ ያመጣል፤ በእግዚአብሔር የሚታመን ግን እርሱ ይጠበቃል። ምሳሌ 29፡25
ሰውን መፍራትና በሰው መታመን እግዚአብሄን እንዳንፈራና በእግዚአብሄ እንዳንታመን ያግደናል፡፡ ሰውን መፍራትና በሰው መታመን ትኩረታችንን ከእግዚአብሄር ላይ እንድናነሳ ያደርጋል፡፡
ለእናንተም ለወዳጆቼ እላችኋለሁ፥ ሥጋን የሚገድሉትን በኋላም አንድ ስንኳ የሚበልጥ ሊያደርጉ የማይችሉትን አትፍሩ። እኔ ግን የምትፈሩትን አሳያችኋለሁ፤ ከገደለ በኋላ ወደ ገሃነም ለመጣል ሥልጣን ያለውን ፍሩ። አዎን እላችኋለሁ፥ እርሱን ፍሩ። ሉቃስ 12፡4-5
ማዳን በማይችሉ በሰው ልጆችና በአለቆች አትታመኑ። መዝሙር 146፡3
ሌላ አማልክት አይሁንልህ ማለት የምታከብረው ሌላ ነገር አይኑር ማለት ነው፡፡ ሌላ አማልክት አይሁንልህ ማለት ተስፋ የምታደርግበት ሌላ ነገር አይኑርህ ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄን ብቻ አክብር በእግዚአብሄር ብቻ ተስፋ አድርግ ማለት ነው፡፡
ከእግዚአብሄር ውጭ ተስፋ የምናደርግበት ማንኛውም ነገር የእግዚአብሄርን አምልኮ የሚሻማና እግዚአብሄርን ብቻ እንዳናመልክ የሚያግደን ነገረ ነው፡፡   
ሌላ አማልክት አይሁንልህ ማለት ቅድሚያ የምትሰጠው ነገር አይኑር ማለት ነው፡፡ ሌላ አማልክት አይሁንልህ ማለት ሌላ ከእግዚአብሄር በላይ የምታስቀድመው ነገር አይኑር ማለት ነው፡፡ ሌላ አማልክት አይሁንልህ ማለት ከእግዚአብሄር በላይ ትኩረትህን የሚወስድ ነገር አይኑር ማለት ነው፡፡
ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ። ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ማቴዎስ ወንጌል 22፡37-38
ሌላ አምላክ አይሁንልህ ማለት ሁኔታዎችን አትፍራ ማለት ነው፡፡ ሁኔታን መፍራት እግዚአብሄርን በሙላት እንዳናመልከው ያደርጋል፡፡ አንዳንድ ሰው ማጣትን በጣም ከመፍራቱ የተነሳ ማጣት በህይወቱ እንዳይደርስበት የማይገባ ነገር ሲያደርግ ይገኛል፡፡ አንዳንድ ሰው ድሃ እንዳይሆን በመፍራት ይገድላል ይዘርፋል ይጠላል፡፡ ይህ ድህነት ፍርሃት አምላክ ሆኖበታል፡፡
መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ። ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ። ፊልጵስዩስ 4፡12-13
ሰው መዋረድን ሳይንቅ እግዚአብሄርን ማክበር አይችልም፡፡ ሰው መራብን ፈርቶ ለእግዚአብሄር በሙላት ሊኖር አይችልም፡፡ ሰው ግን መዋረድንም መራብንም ልካቸውን ካወቃቸውና ከናቃቸው በመብዛትና በመጥገብ ሳይሆን በክርስቶስ ሁሉን እንደሚችል ከተረዳ እግዚአብሄን በሙላት አገልግሎ ያልፋል፡፡
ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ። ዘጸአት 20፡3
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #አምላክ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #መታመን #ፍርሃት #ብቸኛአምላክ #መስዋእት #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment