Popular Posts

Friday, February 24, 2017

ከሃጢያት አለመመለስ እንጂ ሃጢያት ሰውን ከእግዚአብሄር ሊያቆራርጠው አይችልም

ሃጢያት በእግዚአብሄር ዘንድ አፀያፊ ነገር ነው፡፡ ሃጢያት ቀልድ አይደለም፡፡ ሃጢያት ሰውን ከእግዚአብሄር የለያየ ከባድ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ከባድ የሆነ አመፅ እንኳን ሰውን ከእግዚአብሄር እንዲለየው እግዚአብሄር አይፈልግም፡፡
እግዚአብሄር በሰው ላይ ያለው አላማ ፍቅር ነው፡፡ ሰው በሃጢያቱ እንዲሞት እግዚአብሄር አይፈልግም፡፡ የእግዚአብሄር ፍላጎት ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና ከእግዚአብሄር ጋር ያላቸው ህብረት እንዲታደስ ነው፡፡
ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው። 1 ጢሞቴዎስ 2፡3-4
ለሰው ካለው ፍቅር የተነሳ ሃጢያት ከሰው ጋር ያለውን ህብረትን አበላሽቶት እንዳይቀር እግዚአብሄር እቅድን አዘጋጅቷል፡፡ ሰው ንስሃ ከገባ ሃሳቡንና መንገዱን ከቀየረ ሃጢያት ሰውን ከእግዚአብሄር ሊያቆራርጠው አይችልም፡፡ እግዚአብሄር ሃጢያት በመስራታችን ሳይሆን በመመለሳችን ደስ ይሰኛል፡፡ በሃጢያታችን ስናዝንና ስንመለስ እግዚአብሄር ይረካል፡፡    
በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው። 1ኛ ዮሐንስ 1፡9
እግዚአብሄር የኢየሱስ ደም እንዲፈስና ያደረገው በሃጢያት ምክኒያት ነው፡፡ ስለዚህ ነው የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከሃጢያት ሁሉ የሚያነፃው፡፡ ስለዚህ ነው ሰው በማንኛውም ሃጢያት ውስጥ ቢገኝና ከእግዚአብሄር ጋር ያለው ህብረት ቢበላሽ በኢየሱስ ደም በኩል ተመልሶ ወደ ህብረቱ መግባት የሚችለው፡፡  
ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ በብርሃን ብንመላለስ ለእያንዳንዳችን ኅብረት አለን፥ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል። 1ኛ ዮሐንስ 1፡7
ሰው ንስሃ አለመግባቱ ፣ አለመመለሱና በሃጢያት መቀጠሉ እንጂ ሃጢያት መስራቱ ብቻ ሰውን ከእግዚአብሄር ለዘላለም ሊያቆራርጠው አይችልም፡፡ እግዚአብሄር ያዘጋጀውን የመዳኛ መንገድ አለመቀበሉና መጣሉ እንጂ ሃጢያቱ ከእግዚአብሄር ለዘላለም አይለየውም፡፡
ሃጢያት ሰውን ለዘላለም ከእግዚአብሄር የሚለይ ቢሆን ኖሮ ሁላችን ለዘላለም ከእግዚአብሄር በተለየን ነበር፡፡ እኛ ለዘላለም ከእግዚአብሄር እንዳንለያይ እግዚአብሄር በንስሃና መንገድን በመለወጥ ከእግዚአብሄር ጋር ያለን ግንኙነት እንዲታደስ አስቻለን፡፡ አሁንም ማንም የዘላለም ፍርድ ቢያገኘው ከሃጢያቱ ስላልተመለሰ ብቻ ነው፡፡  
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እምነት #ንስሃ #መመለስ #ሃጢያት #ይቅርታ #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #መናዘዝ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

No comments:

Post a Comment