Popular Posts

Follow by Email

Monday, February 13, 2017

ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም

ፍቅር የስሜት ጉዳይ አይደለም፡፡ እውነተኛ ፍቅር ያዘኝ ለቀቀኝ የምንለው ነገር አይደለም፡፡ ፍቅር ስሜትን ቢያካትተም የስሜት ጉዳይ ብቻ ግን ፈፅሞ አይደለም፡፡
ፍቅር የመረዳት ጉዳይ ነው፡፡ ፍቅር የውሳኔ ጉዳይ ነው፡፡ ፍቅር በመረዳት ለሌላው መልካም ማሰብ መልካም መናገርና መልካም ማድረግ ነው፡፡
እውነተኛ ፍቅር የሚፈተነው በርችትና በፌሽታ መካከል ሳይሆን ሌላው ሲደክም ፣ ሌላው ሲበድል ፣ ሌላው ሲያስቸግር ፣ ሌላው ሳይረዳን ፣ ሌላው ለፍቅር መልስ ሳይሰጥ ፣ ሌላው ሲጠላ መውደድ ፣ መሸከም ፣ መንከባከብ ፣ መጥቀምና ማንሳት በመቻል ነው፡፡
እውነተኛ ፍቅር ዘላቂ ነው፡፡ እውነተኛ ፍቅር "አስጨርሺኝ" የሚባል አይደለም፡፡ እውነተኛ ፍቅር ድንገት መጥቶ የሚይዘንና ድንገት ደግሞ የሚለቀን ምትሃት አይደለም፡፡ ይህ ፍቅር ሳይሆን ማንም መንገደኛ የሚያደርገው ስጋዊ ምኞት ነው፡፡
ፍቅር . . . የራሱንም አይፈልግም 1ኛ ቆሮንቶስ 13፡5
ፍቅር ፍቅር የእንካ በእንካ ጉዳይ አይደለም፡፡ ፍቅር የሆነ ነገር ፈልገን መጠጋት አይደለም፡፡ ፍቅር ራስ ወዳድነት አይደለም፡፡ ፍቅር ለማገልገል ፣ ለመባረክ ፣ ለማንሳትና ለመጥቀም መወሰን ነው፡፡
እውነተኛ ፍቅር በሁኔታዎች ሲፈተን እንዲያውም እየጨመረ ፣ እየደመቀ ፣ እየጠራና እያበበ የሚሄድ ነው፡፡
ፍቅራችሁ በእውቀትና በማስተዋል ሁሉ ከፊት ይልቅ እያደገ እንዲበዛ ይህን እጸልያለሁ። ፊልጵስዩስ 1፡9
እውነተኛን ፍቅር የማይረዳ ማንም ሰው የለም፡፡ ፍቅር የማያሸንፈው ሰው የለም፡፡ ፍቅር ሃያል ነው፡፡  ምንም አያውቅም የምንለው ሰው ፍቅርን ግን ይረዳል፡፡
እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ። ዮሃንስ 13፡35
ፍቅር የሚደገፈው በእግዚአብሄር ፍቅር ላይ ስለሆነ ለዘወትር አይወድቅም ፡፡ ፍቅር የሚያተኩረው በመስጠት ላይ ስለሆነ ለዘወትር አይወድቅም፡፡ ፍቅር ከሌላው የሚጠቀመውን ተመኝቶ ስለማያደርግ ለዘወትር አይወድቅም፡፡ ፍቅር ጥቅሙን አስቦ ስለማይጠጋ ለዘወትር አይወድቅም፡፡  
ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 13፡8
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እምነት #ፍቅር #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #ቸርነት #ትግስት #ፍርሃት #መታበይ #መመካት #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment