Popular Posts

Wednesday, February 15, 2017

ታላቅ ሊሆን የሚወድ

ሊቃችሁ አንድ እርሱም ክርስቶስ ነውና፦ ሊቃውንት ተብላችሁ አትጠሩ። ከእናንተም የሚበልጠው አገልጋያችሁ ይሆናል። ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል፥ ራሱንም የሚያዋርድ ሁሉ ከፍ ይላል።  ማቴዎስ 23፡10-12
ኢየሱስ ግን ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ የአሕዛብ አለቆች እንዲገዙአቸው ታላላቆቹም በላያቸው እንዲሠለጥኑ ታውቃላችሁ። በእናንተስ እንዲህ አይደለም፤ ነገር ግን ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፥ ማቴዎስ 20፡25-26
በወደቀው አለም ስርአት ስልጣን መጠቀሚያ መንገድ ነው፡፡ ስልጣን መያዝ መታደል ነው፡፡ ስልጣን ጥቅም ነው፡፡ ስልጣን ያለውን ሰው ሰዎች ያገለግሉታል፡፡ ሰው ስልጣኑ ሲበዛ የሚያገለግሉት ይበዛሉ፡፡ ሰው ስልጣኑ ከፍ ሲል ጥቅሙም ከፍ ይላል፡፡
ስለዚህ ሰው የሚጋደለው ያለውን ሁሉ ተጠቅሞ ስልጣኑን ፣ ዝናውንና ተሰሚነቱን ለመጨመር ነው፡፡ ዝናው በጨመረ ቁጥር በቀላሉ መጠቀም ይችላል፡፡ ተሰሚነቱ በጨመረ ቁጥር የሰዎችን አእምሮ አላግባብ በመቆጣጠር ጥቅሙን ያበዛል፡፡ መፈራቱ በጨመረ ቁጥር ሰዎች ይንበረከኩለታል፡፡ መፈራቱ በጨመረ ቁጥረ የሚከራከረው ሳይኖር ሰዎች ይነጠቁለታል፡፡ መፈራቱ በጨመረ ቁጥር የሰዎችን አእምሮ በመቆጣጠር የፈለገውን ያስወጣቸዋል፡፡ መፈራቱ በጨመረ ቁጥር ሰዎችን በማዋከብ ይነጥቃቸዋል፡፡
ስለዚህ ነው በአለም ስርአት ተናጋሪ ሰው ይጠቀማል፡፡ ተናጋሪ ሰው ሰዎችን ወደፈለገበት መንገድ ይመራል፡፡ ተናጋሪ ሰው ሰዎችን ያስከትላል፡፡ ተናጋሪ ሰው በሰዎች ይጠቀማል፡፡ በመናገር ችሎታው ሰዎችን መጠቀሚያ ያደርጋቸዋል፡፡  
በአለም ስርአት ሰዎች ራሳቸውን ከፍ ያደርጋሉ፡፡ ከሰዎች የስልጣናቸውን ደረጃ ለማሳየት የሚነዱትን መኪና ደረጃ ከፍ ያደርጋሉ፡፡ ከሰዎች እንደ አንዱ አለመሆናቸውን ለማፅናት ብቻ የማያስፈልጋቸው ትልልቅ ቤት ውስጥ ይኖራሉ፡፡ ከሰዎች እጅግ ከፍ ብለው ለመታየት ታላላቅ ስም ለራሳቸው ይሰጣሉ፡፡ ከሰው እጅግ ከፍ ማለታቸውን ለማሳየት እጅግ ውድ ልብስ ይለብሳሉ፡፡ ታላቅ የሆነውን የስልጣን ክንዳቸውን ለማሳየት በታላላቅ ሰዎች ይከበባሉ፡፡ ከሰዎች ጋር ላለመቀላቀል የሚቀመጡበትን ቦታ እንኳን ይለያሉ፡፡
ይህ ሁሉ መልክት አለው፡፡ መልዕክቱ እኔ እጅግ ከፍ ያልኩ ሰው በመሆኔ አንደሌላ ሰው አትዩኝ ነው፡፡ መልክቱ እኔ እጅግ የከበርኩ በመሆኔ እንደሌላ ሰው አትስጡኝ ነው፡፡ መልክቱ እኔ እጅግ የከበርኩ ስለሆንከ እንደሌላ ሰው አትያዙኝ ነው፡፡
እነዚህ ሰዎች የመበለቶችን ቤት ለመበዝበዝ ፀሎታቸውን ያስረዝማሉ፡፡ ፀሎታቸው በረዘመ ቁጥር "አንቺ መበለት ሆይ መንፈሳዊ ነገር ከባድ ነው፡፡ እኔ እንዴት እየደከምኩ እንደሆነ ተመልከቺ፡፡ ስጦታዬ እንዴት እንደከበረ ማየት ትችያለሽ፡፡ እኔ እንዴት እጅግ የከበርኩ ታላቅ ሰው እንደሆንኩ ተመልከቺ፡፡ ጌታ ጋር ለመግባት ምን ያህል ጊዜ እንደፈጀብኝ ተመልከቺ፡፡ ስለዚህ ያሰብሸውን ያንን ስጦታ ወዲያ በዪና አራት እጥፍ አድርጊው፡፡ " የሚል መልክት በፀሎታቸው ርዝማኔ ያስተላልፋሉ፡፡ አንዳንዶቹ በንግግራቸው ልቀት ይህንንኑ መለክት ያስተላልፋሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ የኑሮ ዘይቤያቸው ያንንኑ ይናገራል፡፡   
ረጃጅም ልብስ ለብሰው መዞር ከሚፈልጉ፥ በገበያም ሰላምታ፥ በምኵራብም የከበሬታ ወንበር፥ በምሳም የከበሬታ ስፍራ ከሚወዱ ከጻፎች ተጠበቁ፤ የመበለቶችን ቤት የሚበሉ ጸሎታቸውንም በማስረዘም የሚያመካኙ፥ እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ አለ። ሉቃስ 20፡46-47
ኢየሱስ ግን የሚያስተምረው ያለን ነገር ሁሉ ሰዎችን ለማገልገል የተሰጠን ነገር እንደሆነ ነው፡፡ እንዲያውም ክብራችን የተፈጠርንበትን አላማ አገልግሎትን ሰዎችን መጥቀም ሰዎችን ማንሳት ለሰዎች ማድረግ ነው፡፡ ጥሪያችን ሰዎችን የማገልገል ሃላፊነታችንን መወጣት ነው፡፡ ጥሪያችን በስልጣናችን ተጠቅመን ሰዎችን ማራቆት ሳይሆን ለሰዎች በጎነት መስራት ነው፡፡ ጥሪያችን በአንደበተ ርቱእነታችን ተጠቅመን ለደሃ መሟገት ነው፡፡ ጥሪያችን ዝናችንን ተጠቅመን ሰዎችን መፈወስ ነው፡፡ ጥሪያችን ስልጣናችንን ተጠቅመን ሰዎችን መባረክ ነው፡፡ ክብራችን ከእግዚአብሄር ብቻ እየጠበቅን ሰዎች ላይ ጫና ሳንፈጥር ማገልገል ነው፡፡
ድሆች ስንሆን ብዙዎችን ባለ ጠጎች እናደርጋለን፤ አንዳች የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው። 2ኛ ቆሮንቶስ 6፡10
በክርስትና ያለው ውድድር የስልጣን ፣ የዝናና የሃብት ሳይሆን የአገልግሎት ውደድር ነው፡፡ አንዱ ካንዱ እንደሚበልጥ የሚያሳየው ከህዝብ ጥቅምን ሳይጠብቅ ለሰዎች በመድከሙ ፣ በመልፋቱና በመጥቀሙ ነው፡፡ በክርስትና ውድድሩ እንደፈሪሳዊያን ዋጋን በምድር ሳይቀበሉ በቸርነት ለእግዚአብሄር ህዝብ መኖር ፣ ያለንን ለህዝቡ ማካፈል ፣ ህዝቡን በትህትና መጥቀም መባረከ ነው፡፡ ስልጣን ሰዎችን የማገልገል የመጥቀም የማንሳት ሃላፊነት እንጂ በሰዎች የመጠቀሚያ መሳሪያ አይደለም፡፡
  
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ክብር #መዋረድ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና #እምነት #ታላቅነት #ማገልገል #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment