Popular Posts

Monday, July 24, 2023

አንድነት የትጉሃን ብቻ ነው

 

እኔ ከተረዳሁት ውጭ መረዳት የለም ፣ እኔ ካሰብኩት ውጭ ሃሳብ የለም ፣ እኔ ካየሁት ውጭ እይታ የለም የሚል አስተሳሰብ አንድነትን ይንዳል፡፡

እኔ ይህንን አይቻለሁ ከማለት ባሻገር አንተ ምን አየህ ብሎ የሌላውን እይታ በቅንነት ለመረዳት መሞከር ለአንድነት አንድ እርምጃ ነው፡፡

ነገሮችን ከሌላው ሰው ማእዘን በኩል ለማየት መሞከር አንድነትን ያመጣል፡፡ የራስን እይታ እንደ አንድ እና ብቸኛ እይታ አድርጎ ቀኑን ሙሉ ሌላውን ለማሳመን ብቻ መሞከር ይከፋፍላል፡፡ አንተ እንደተማመንከው ሁሉ እርሱም ይተማመናል፡፡ አንተ አሳብህ የተሻለ ሃሳብ ነው ብለህ በቅንነት እንዳሰብክ ሁሉ እርሱም የተሻለ አሳቡ የተሻለ አሳብ ነው ብሎ በቅንነት ያስባል፡፡ አንተ የተረዳሁት መንገድ ብቸኛው መንገድ ነው ብለህ እንዳሰብክ እርሱም እንዲሁ የተረዳው ብቸኛው መንገድ እንደሆነ ያስባል፡፡ አንተ ሌሎቹ ሁሉ ተሳስተዋል ብለህ እንዳሰብክ ሁሉ እርሱም ሌሎቹ ሁሉ ተሳስተዋል ብሎ ያስባል፡፡

ሌላውን እንደራስ መቀበል ፣ ሌላውን እንደራስ ማክበር ፣ ሌላውን እንደራስ መረዳት አንድነትን ያመጣል፡፡

በራስ ማእዘን በኩል ነገሮችን ማየት ቅጽበታዊ ነው፡፡ ነገሮችን በራስ ማእዘን በኩል መረዳት ጥረት አይጠይቅም፡፡

በእኔም መንገድ ባንሄድ ነገር ግን በእርሱ መንገድ ብንሄድ ልንደርስ እንችላለን ብሎ ማሰብ አስተዋይነት ነው፡፡ እኛ ብቻ ሳንሆን ሌላው መልካም ሃሳብ ሊያመጣ ይችላል ብሎ ልብን ማስፋት አንድነት ነው፡፡ ፍቅር ራሱን እንደሚያምን ሌላውን ሰው ደግሞ ያምናል፡፡

ሁሉን ይታገሣል፥ ሁሉን ያምናል፥ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፥ በሁሉ ይጸናል። 1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13፡7

ራስን በሌላ ሰው ቦታ አስቀምጦ ነገሮችን ማየት ግን አንድነት ነው፡፡ ከእኛ የተለየን ሰው መስማት የተለመደ አይደለም፡፡ ከእኛ የተለየን ሰው ማክበር በቀላሉ አይመጣም፡፡ ከእኛ የተለየን ሰው እንደ ሰውነቱ መቀበል የአንድነቱ አንድ እርምጃ ነው፡፡

ስለዚህ እኛ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም፤ ክርስቶስንም በሥጋ እንደ ሆነ ያወቅነው ብንሆን እንኳ፥ አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ አናውቀውም። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 5፡16

#ኢየሱስ #ጌታ #አንድ #ፍቅር #አንድነት #ህብረት #አካል #ቤተክርስቲያን #መፅሐፍቅዱስ #ቃል #እግዚአብሔር #መተባበር

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa


No comments:

Post a Comment