Popular Posts

Saturday, July 22, 2023

አንድነት የሚገለፀው በአላማ አንድነት ብቻ እንጂ በሌላ በምንም አይደለም

 


አንድነትን አንድነት የሚያደርገው የአላማ አንድነት ብቻ ነው፡፡ የተለያየ አሳብ ያለን ፣ የተለያየ ስጦታ ያለን ፣ የተለያየ ባህሪ ያለን የተለያየን ሰዎች ለአንድ አላማ መስራት እንችላለን፡፡

አላማችን አንድ እስከሆነ ድረስ ለአንድ መንግስት አላማ እንቆማለን፡፡ አላማችን አንድ እስከሆነ ድረስ በተለያየ ጦር ግንባር ብንዋጋም ለአንዱ መንግስት እንዋጋለን፡፡ አላማችን የእግዚአብሔርን መንግስት ማስፋት እስከሆነ ድረስ የተለያየ ስጦታ ቢኖረንም ለአንድ መንግስት ጥቅም እንሰራለን፡፡

ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና። የማቴዎስ ወንጌል 18፡20

ሁለት ወይም ሶስት የተለያዩ ሰዎችን አንድ በማድረግ በአንድነት የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንዲፈፅሙ የሚያደርጋቸው በስሙ መሰብሰባቸው ነው፡፡ በስሙ መሰብሰባቸው ፣ እርሱን ወክለው መሰብሰባቸው ፣ ለእርሱ ጥቅም መሰበስባቸው ፣ በእርሱ ቃል መሰብሰባቸው ፣ ለእርሱ መንግስስት አላማ መሰብሰባቸው ብቻ አንድ ያደርጋቸዋል፡፡

እግዚአብሔር ተመሳሳይ አድርጎ አልፈጠረንም፡፡ ልዩነታችን ውበታችን ጥንካሬያችን ነው፡፡ ልዩነታችንን የማይቀበል እና ተመሳሳይ ሊያደርገን የሚፈልግ ሁሉ አንድነታችንን እየናደው ነው፡፡ እግዚአብሔር ለአንድ መንግስት የተለያየን ስራን እንድንሰራ የተለያዩ ሰዎች አድርጎ ፈጥሮናል፡፡ የእግዚአብሔር አላማ የእኛ ተመሳሳይነት ሳይሆን አንድነታችን ነው፡፡

ተመሳሳይነትን ከፈለግን ሰዎችን መቀበል ስለማንችል አውጥተን እንጥላቸዋለን፡፡ ተመሳሳይነትን ከፈለግን ሰዎችን በከንቱ እንጨፈልቃለን እንጂ የምናስበውን አንድነት ልናመጣ በፍፁም አንችልም፡፡ አንድነት እንዲመጣ ማንም ሰው መጨፍለቅ የለበትም፡፡ ሁሉንም ተመሳሳይ ለማድረግ በምናደርገው ሙከራ ሰውን በጨፈለቅን ቁጥር አንድነትን ከማምጣት ይልቅ አንድነትን እየበተንን ነው፡፡ ተመሳሳይነት በሰው ልብ እንጂ በእግዚአብሔር ልብ ውስጥ የሌለ የእውነተኛው አንድነት ማስመሰያ ቅጂ እንጂ እውነተኛው ኦሪጅናል አንድነት አይደለም፡፡

#ኢየሱስ #ጌታ #አንድ #ፍቅር #አንድነት #ህብረት #አካል #ቤተክርስቲያን #መፅሐፍቅዱስ #ቃል #እግዚአብሔር #መተባበር

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa


No comments:

Post a Comment