Popular Posts

Thursday, June 29, 2023

በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ

 


በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ እኔም አውቃቸዋለሁ ይከተሉኝማል፤ የዮሐንስ ወንጌል 10፡27

ከጥንት ከእግዚአብሔር እረኝነት ስር ተፈጥረን ነበር፡፡

እርሱ አምላካችን ነውና፥ እኛ የማሰማርያው ሕዝብ የእጁም በጎች ነንና። መዝሙረ ዳዊት 95፡7

በሃጢያት ምክኒያት እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን እያንዳንዱ ወደገዛ መንገዱ አዘነበለ፡፡

እንደ በጎች ትቅበዘበዙ ነበርና፥ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 2፡25

ክርስቶስን እንደአዳኝ የተቀበለን ሁላችን ወደነፍሳችን እረኛ እና ጠባቂ ተመልሰናል፡፡

ኢየሱስ እረኛችን ሆኖዋል፡፡ እኛም እንደበጎች ድምፁን እንሰማለን፡፡ በጎች ከሆንን ድምፁን እንሰማለን፡፡ ክርስቶስን እንደጌታ በተቀበልንበት በዚያች ቅጽበት በጎቹ ሆነናል ድምጹንም መስማት ጀምረናል፡፡ ከቆየ በኃላ ሳይሆን ድምፁን መስማት የጀመርነው በዚያች ጀዳንንበት ቅጽበት ጀምሮ ነው፡፡

ድምፁን የምንሰማው ጌታን በመከተል ከቆየን በክርስትና ከበሰለን በኃላ አይደለም፡፡ እንደበጎች የእረኛን ድምፅ መስማት ለጥቂት ሰዎች የተሰጠ ስጦታ አይደለም፡፡ ድምፁን መስማት ለዳንን ለሁላችንም ነው፡፡

እውነት ነው በግ ካልሆንን ድምፁን አንሰማም፡፡ በግ ከሆንን ግን ድምፁን እንሰማለን፡፡  ድምፁን የምንሰማው ከእኛ ችሎታ ሳይሆን ከእረኛው ድምፁን የማሰማት ችሎታ የተነሳ ነው፡፡ እርሱ ተፈጥሮዋችንን ያውቃል እርሱ ፈቃዱን ሊያሳውቀን ሲፈልግ ይችልበታል፡፡ እርሱ ከተናገረ ደግሞ እንሰማዋለን፡፡

አባት ለልጆቹ እንደሚራራ እንዲሁ እግዚአብሔር ለሚፈሩት ይራራል፤ ፍጥረታችንን እርሱ ያውቃልና፤ መዝሙረ ዳዊት 103፡13-14

በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ እኔም አውቃቸዋለሁ ይከተሉኝማል፤ የዮሐንስ ወንጌል 10፡27

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa


No comments:

Post a Comment