በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና። ወደ ሮሜ ሰዎች 8፡2
ከሃጢያት ነፃ የምንወጣው በውስጣችን ያለውን በክርስቶስ ያለውን የህይወት መንፈስ ህግ
ስንሰማ ብቻ ነው፡፡ በውስጣችን ያለው በክርስቶስ ያለው የህይወት መንፈስ ድምፅ አለው፡፡ በውስጣችን ያለውን የህይወት መንፈስ ከሰማን
እና ከተከተለን ሃጢያትን መስራት አንችልም፡፡
ጽድቅን በማድረግ ብቻ ከመቀፅበት ከሃጢያት እንጠበቃለን፡፡
ብልቶቻችሁንም የዓመፃ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለኃጢአት አታቅርቡ፥ ነገር ግን ከሙታን ተለይታችሁ በሕይወት እንደምትኖሩ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፥ ብልቶቻችሁንም የጽድቅ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ። ወደ ሮሜ ሰዎች 6፡13
ከሃጢያት የመጠበቂያው ፍቱን መድሃኒት ሃጢያትን አለመከተል ሳይሆን የህይወት መንፈስ
ህግን መከተል ነው፡፡ የህይወት መንፈስ ህግን በመከተል ብቻ ይህ
ሃጢያት ነው አይደለም ብለን በአእምሮዋችን መመራመር ሳይጠበቅብን እግዚአብሄር የሚወደውን የቅድስናን ህይወት መኖር እንችላለን፡፡
ሃጢያትን ብቻ እያሰብን ከሃጢያት ለመዳን ከመፍጨርጨር የመንፈስን ድምፅ በመስማት ብቻ
ሳናውቀው ከሃጢያት መጠበቅ እንችላለን፡፡
ስለመንፈስ በማሰብ ብቻ ስለስጋ ከማሰብ እንጠበቃለን፡፡
እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና፥ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን የመንፈስን ነገር ያስባሉ። ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው። ወደ ሮሜ ሰዎች 8፡5-6
እንደብሉይ ኪዳን ጊዜ አይደለም፡፡ ክርስቶስን የምንከተል ሁላችን ውስጥ መንፈስ ቅዱስ
ይኖራል፡፡ መንፈሱን ተከትለን በምንም ሃጢያት ልንኮነን እስከማንችል ድረስ ከሃጢያት አርነት መውጣት እንችላለን፡፡ መንፈሱን በመከተል
አትያዝ አትቅመስ አትንካ ሳንባል ሙሉውን የእግዚአብሄርን ህግ መፈፀም እንችላለን፡፡
እንደ ሰው ሥርዓትና ትምህርት። አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ ለሚሉት ትእዛዛት በዓለም እንደምትኖሩ ስለ ምን ትገዛላችሁ? እነዚህ ሁሉ በመደረግ ሊጠፉ ተወስነዋልና። ወደ ቆላስይስ ሰዎች 2፡22
እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም። በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና። ወደ ሮሜ ሰዎች 8፡1-2
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
No comments:
Post a Comment