Popular Posts

Thursday, September 13, 2018

ልባችን ሲጠራ ፀሎታችን ይመለሳል


እግዚአብሄር የመርህ አምላክ ነው፡፡ ሰው የልቡ መነሻ ሃሳብ ካልጠራ ፀሎቱ እንደማይመለስ መፅሃፍ ቅዱስ ያስተምረናል፡፡ የሰው የልቡ መነሻ ሃሳብ ወይም ሞቲቭ ከእግዚአብሄር ሃሳብ ጋረ አብሮ ካልሄደ ፀሎቱ እንደማይመለስ መፅሃፍ ቅዱስ በግልፅ ይነግረናል፡፡ ለምሳሌ ሰው የሚፀልይበት መነሻ ሃሳብ ቅንጦት ከሆነ እግዚአብሄር የለመነውን አይሰጠውም፡፡ እግዚአብሄር መሰረታዊ ፍላጎታችንን እንጂ ቅንጦታችን ለማሟላት ቃል የገባበት አንድም የመፅሃፍ ቅዱስ ክፍል የለም፡፡ እንዲያውም በተቃራኒው የቅንጦት ጸሎት እንደማይመለስ በእግዚአብሄር ቃል በግልፅ ተቀምጧል፡፡  
ትለምናላችሁ፥ በምቾቶቻችሁም ትከፍሉ ዘንድ በክፉ ትለምናላችሁና አትቀበሉም። የያዕቆብ መልእክት 4፡3
አንድን ፀሎት ስንፀልይ ሁለት መነሻ ሃሳብ ሊኖረን ይችላል፡፡ አንዱ እግዚአብሄርን ማክበር ሌላው ራሳችንን ማክበር ፣ አንዱ መሰረታዊ ፍላጎትን ማሟላት ሌላው ለቅንጦት ፣ አንዱ ለፍቅር ሌላው ለራስ ወዳድነት ሊሆን ይችላል፡፡  
ልባችን በሁለት ሀሳብ ከማንከስ ሲጠራ ከእግዚአብሄር የለመንነው ነገር እጃችን ይገባል፡፡
ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል። እናንተ ኃጢአተኞች፥ እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት አሳብም ያላችሁ እናንተ፥ ልባችሁን አጥሩ። የያዕቆብ መልእክት 4፡8
ብዙ የፀለይናቸው ፀሎቶች ተመልሰዋል፡፡ ነገር ግን የተመለሱት እኛ በፈለግንት ጊዜ እና ሁኔታ ሳይሆን እግዚአብሄር በፈለገበት ጊዜና ሁኔታ ነው፡፡ ፀሎቶቻችን ሁሉ የተመለሱት በራስ ወዳድነት በተመኘናቸው ጊዜ ሳይሆን ልባችን በጠራና ለእግዚአብሄር ክብር በእውነት ባስፈለጉን ጊዜ ነው፡፡ ብዙ ፀሎቶቻችን ሲመለሱ ያልታወቀን የራስ ወዳድነት መነሻ ሃሳባችን ሲሞት እግዚአብሄር ፀሎታችን ስለመለሰ ነው፡፡ ብዙ ፀሎቶቻችን ሲመለሱ ያልታወቀን የስጋ ጩኸታችን ጠፍቶ ለእግዚአብሄር አላማ ከልባችን በፈለግናቸው ጊዜ ስለተመለሱ ነው፡፡
ሃና ልጅ ስላልነበራት ባላንጣዋ ፍናና እጅግ ታስጨንቃት ነበር፡፡ ሃናም ትፀልይ ነበር፡፡ ሃና ግን አንድ ቀን ጸሎትዋ እግዚአብሄር ለማክበር እንደሆነ በልብዋ ወስና ተናገረች፡፡ እግዚአብሄር ልጅን ቢሰጣት ለእግዚአብሄር ክብር እንደምታውለው ቃል ገባች፡፡
እርስዋም፦ አቤቱ፥ የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ የባሪያህን መዋረድ ተመልክተህ ብታስበኝ፥ እኔንም ባትረሳ፥ ለባሪያህም ወንድ ልጅ ብትሰጥ፥ ዕድሜውን ሁሉ ለእግዚአብሔር እሰጠዋለሁ፥ ምላጭም በራሱ ላይ አይደርስም ብላ ስእለት ተሳለች። መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 1፡11
ዛሬ የፀለይናቸውን ፀሎቶች ወደኋላ ተመልሰንም እንመርምር፡፡ አብዛኛዎቹ ወደሌላ የፀሎት ጥያቄ ከተሻገርን እና ከረሳናቸው በኋላ ተመልሰዋል፡፡ ያልተመለሱ የመሰሉንን ፀሎቶች እንፈትሽ፡፡ ፀሎታችን እንዲመለስ የፈለግንው የእግዚአብሄር አላማ በምድር ላይ እንዲፈፀም ለእግዚአብሄር ክብር ወይስ ለሌላ? ልባችን በጠራ ጊዜ እያንዳንዱ የፀሎት መልሳችን ይመለሳል፡፡
ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፈትላችሁማል። የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና፥ የሚፈልገውም ያገኛል፥ መዝጊያንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል። የማቴዎስ ወንጌል 7፡7-8
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #የእግዚአብሄርፈቃድ #ፀሎት #ልመና #እንዲሰማን #ልብ #አጥሩ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #የእግዚአብሄርቃል #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #መጠየቅ #መንበርከክ #ምስጋና

No comments:

Post a Comment