Popular Posts

Follow by Email

Sunday, September 2, 2018

የራዕይ ጠቀሜታ


እግዚአብሄር የፈጠረን ለክብሩ ነው፡፡ እግዚአብሄር በምድር ላይ ያስቀጠን የፈለግነውን ነገር እንድናደርግ ሳይሆን የእርሱን ተልእኮ በምድር ላይ እንድንፈፅም ነው፡፡ ራእይ እግዚአብሄር ለህይወታችን ያለውን አላማ መገለጥ ነው፡፡ ራእይ ግዚአብሄር በህይወታችን ምን እንድንሰራለት እንደሚፈልግ የመረዳት እውቀት ነው፡፡ ራእይ በእግዚአብሄር ልብ እንዳለ አድርገን አገልግሎታችን እንድንፈፅም የሚመራን ጠቋሚያችን ነው፡፡
አሁን ካለንበት እግዚአብሄር ወደ አሳየን እንደምንሄድ ማረጋገጥ የምንችለው ራእይ ሲኖረን ብቻ ነው፡፡ በትክክለኛው ጊዜ በትክክለኛው መንገድ ላይ መሆናችንን የምናውቅው ራእይ ሲኖረን ብቻ ነው፡፡ ስንደርስ መድረሳችንን የምናውቀው ራእይ ሲኖረን ነው፡፡ ሃላፊነታችንን ስንጨርስ ለሌላ ሃላፊነት የምንዘጋጀው ራእይ ሲኖረን ነው፡፡ ግብ የሚኖረን ራእይ ሲኖረን ብቻ ነው፡፡
ራእይ ከሌለን ግን የሚመራን የሰዎች ሃሳብ ነው፡፡ ራእይ ከሌለን የሚመራን የትምህርት ነፋስ ነው፡፡ ራእየ ከሌለን የሚመራን የዘመኑ ፋሽን ነው፡፡ ራእይ ከሌለን ባለን ነገር አንፀናም፡፡ ራእይ ከሌለን የጀመርነውን አንጨርስም፡፡ ራእይ ከሌለን ፍሬያማ ልንሆን እንችልም፡፡ ራእይ ከሌለን የህይወታችን ግብ መምታቱን አናውቅም፡፡ ራእይ ከሌለን የዘፈቀደ ኑሮ እንኖራለን፡፡ ራእይ ከሌለን እግዚአብሄር ያላለንን በመስራት ህይወታችንን እናባክነዋለን፡፡  
ራእይ በህይወታችን ፣ በቤተሰባችን ፣ በትዳራችን ፣ በአገልግሎታችን እና በቤተክርስቲያናችን የምንሄድበትን ትክክለኛውን መንገድ የሚያሳየን ጠቋሚ ብርሃን ነው፡፡ 
ራእይ በምድር ላይ ምን እንደምንሰራ ያስተምረና
የተፈጠርነው ለምድር ስራችን ከሚያስፈልገው ስጦታ ሁሉ ጋር ነው፡፡ በምድር ላይ የሚሳካልን ከስጦታችንም ጋር የሚሄደውን ራእይ ከእግዚአብሄር ስናገኝ ብቻ ነው፡፡ እያንዳንዳችን የተጠራነው ለተለየ አላማ ነው፡፡ መልካም ቢሆኑም እንኳን ሌላው ሰው ስላደረገው ብቻ እኛ ማድረግ የሌለብን ብዙ ነገሮች አሉ፡፡
በምድር ላይ ብዙ መልካም ነገሮች አሉ፡፡ አንድን ነገር መልካም ስለሆነ ብቻ ካደረግነው እግዚአብሄር እንድናደርገው የሰጠንን ያንን የተለየ መልካም ነገር ማድረግ አንችልም፡፡ በእግዚአብሄር አይን መልካም የሚባለው አኛ ለራሳችን መልካም የምንለው ነገር ሳይሆን እርሱ ያዘጋጀልን መልካም ስራ ነው፡፡ እግዚአብሄር የሚየየው የሆነ መልካም ነገር ማድረጋችንን ብቻ ሳይሆን እርሱ እንድናደርግ የፈጠረንን መልካም ነገር ማድረጋችንን ነው ፡፡
እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 2፡10
የራእይ ጥቅሙ ማድረግ ያለብንን ብቻ በማሳየት ማድረግ ከሌለብን እንድንጠነቀቅ ማስተማሩ ነው፡፡ ባለራእይ ምን እንደሚያደርግ  ብቻ ሳይሆን ምን እንደማያደረግም ያውቃል፡፡ ባለራእይ ለምን እንደተጠረ ብቻ ሳይሆን ለምን እንዳልተጠራም ያውቃል፡፡ ምንም ያህል ሰዎች የተለቀቁበት ፋሽን ቢሆንም ባለራእይ እግዚዚአብሄር ያሳየውን ራእይ እንጂ እንጂ የዘመኑን ፋሽን አይከተልም፡፡ ምንም ያህል ሰዎች ቢሳካላቸው በሰው አይን ያልተሳካ የመሰለውን የእግዚአብሄርን ራእይ እንጂ የሰውን አሰራር አይከተልም፡፡
ራእይ የት እንደምንንሰራ ያሳየናል
አንዳንድ ሰዎች ምን እንደሚሰሩ እንጂ እግዚአብሄር ያላቸውን የት እንደሚሰሩ ግድ የላቸውም፡፡ ምን እንደምንሰራ ማወቃችን አስፈላጊ እንደመሆኑ መጠን የት እንደምሰራው ቦታውን ማወቃችን ለፍሬያማነት ይጠቅማል፡፡
በመፅሃፍ ቅዱስ ሎጥ በአይን ደስ የሚየሰኘውን ሰዶምን መረጠ ነገር ግን ሚስቱን እንኳን ይዞ ሊወጣ አልቻለም፡፡
ሎጥም ዓይኑን አነሣ፥ በዮርዳኖስ ዙሪያ ያለውንም አገር ሁሉ ውኃ የሞላበት መሆኑን አየ፤ እግዚአብሔር ሰዶምንና ገሞራን ከማጥፋቱ አስቀድሞ እስከ ዞዓር ድረስ እንደ እግዚአብሔር ገነት በግብፅ ምድር አምሳል ነበረ። ኦሪት ዘፍጥረት 1310
የዛን ጊዜ ደረቅ እና ምራጭ የመሰለውን የወሰደው ባለራእዩ አብርሃም ግን ስለ ልምላሜው ምሳሌ የሚሆንን ከነአንን በራእይ መረጠ፡፡
አብራም በከነዓን ምድር ተቀመጠ ሎጥም በአገሩ ሜዳ ባሉት ከተሞች ተቀመጠ፥ እስከ ሰዶምም ድረስ ድንኳኑን አዘዋወረ። ሎጥ ከተለየው በኋላም እግዚአብሔር አብራምን አለው፦ ዓይንህን አንሣና አንተ ካለህበት ስፍራ ወደ ሰሜንና ወደ ደቡብ ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ እይ፤ የምታያትን ምድር ሁሉ ለአንተና ለዘርህ ለዘላለም እሰጣለሁና። ኦሪት ዘፍጥረት 13፡12፣14-15
ራእይ መቼ እንደምንሰራ ያስተምረናል
ሰው በድንገት እና በእድል ስኬታማ አይሆንም፡፡ ሰው እግዚአብሄር ያሳየውን ነገር በጊዜውና በቦታው በመፈፀም ስኬታማ ይሆናል፡፡  ለምን ስራ እንደተጠራን ማወቅ ብቻ ሳይሆን የት እንድምንሰራ ማወቅ ለስኬታማነት ወሳኝ ነው፡፡ ምን እንደምሰራና የት እንደምንሰራ ብቻም ሳይሆን መቼ እንደምንሰራ ትክክለኛውን ጊዜም ማወቅ እግዚአብሄር የሰጠንን ስጦታ ለራእያችን መሳካት እንድንጠቀምበት ያስችለናል፡፡
ኢየሱስ በምድር ላይ ምን እንደሚሰራ የት እንደሚሰራና እንዲሁ መቼ አንደሚሰራ ያውቅ ነበር፡፡
የራእይን አሰራር የማይረዱ ሰዎች የተጠራበትን አላማ እንዲፈፅም ሲገፋፉት ኢየሱስ ጊዜዬ አልደረሰም በማለት ራእይ የመፈፀሚያው የራሱ ጊዜ እንዳለው ተናገረ፡፡ ራእይ ተሰጠን ማለት ጊዜው አሁን ነው ማለት አይደለም፡፡ ራአይ ኖሮን ጊዜወን ካላወቅን እንስታለን፡፡   
እንግዲህ ወንድሞቹ፦ ደቀ መዛሙርትህ ደግሞ የምታደርገውን ሥራ እንዲያዩ ከዚህ ተነሣና ወደ ይሁዳ ሂድ፤ ራሱ ሊገለጥ እየፈለገ በስውር የሚሠራ የለምና። እነዚህን ብታደርግ ራስህን ለዓለም ግለጥ አሉት። ወንድሞቹ ስንኳ አላመኑበትም ነበርና።ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ ጊዜዬ ገና አልደረሰም፥ ጊዜያችሁ ግን ዘወትር የተመቸ ነው። የዮሐንስ ወንጌል 7፡3-4-6
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ ABIY Wakuma Dinsa  
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ራዕይ #ምሪት #የእግዚአብሄርአጀንዳ #የእግዚአብሄርፈቃድ #ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #እምነት #ተስፋ #ፍቅር #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment