እግዚአብሄር ምድርን ከፈጠረ በኋላ የፈጠረውን ነገር መዝኖ መልካም እንደሆነ ይመሰክር ነበር፡፡
እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፥ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ስድስተኛ ቀን። ኦሪት ዘፍጥረት 1፡31
እግዚአብሄር ጊዜን በቀን በወርና በአመት የከፋፈለው አንድ ቀን ወርና አመት ማብቂያ ላይ ዞር ብለን ስራችንን እንድናይና በአዲስ መልክ ለመስራት ለወደፊቱ ቀን ወርና አመት እንድናቅድ ነው፡፡
ሰው ሁሉ ሥራውን ያውቅ ዘንድ የሰውን ሁሉ እጅ ያትማል። መጽሐፈ ኢዮብ 37፡7
እርሱ የፈጠራቸው ሰዎች ሁሉ ሥራውን ያውቁ ዘንድ፣ እያንዳንዱ ሰው እንዳይሠራ ይገታዋል። መጽሐፈ ኢዮብ 37፡7 (አዲሱ መደበኛ ትርጉም)
ይህ የአመት ማብቂያ አመቱን መለስ ብሎ በእግዚአብሄር ቃል ለመመዘንና ለሚመጣው አዲስ አመት ለማቀድ አመቺ ጊዜ ነው፡፡
ያለፈውን አመት የምንለካበትን መለኪያ ከእግዚአብሄር ቃል እንመልከት
1. የሰው ህይወቱና አገልግሎቱ የሚለካው ለሌላው ሰው በተሰጠው ነገር አይደለም
እግዚአብሄር እያንዳንዳችንን ለተለየ አላማ ፈጥሮናል፡፡ ምንም እንኳን ሁላችንም በአጠቃላይ ለእግዚአብሄር ክብር አላማ ብንፈጠርም እግዚአብሄርን የምናከብርበት የተለያይ የስራ ድርሻ እና የህይወት አላማ አለን፡፡ እኔን የፈጠረበትን የተለየን አላማ ሌላውን ሰው አልፈጠረውም፡፡ ህይወትና አገልገሎት የውድድርና የፉክክር ነገር አይደለም፡፡ ህይወትና አገልግሎት እያንዳንዳችን የአካል ብልትነታችንን የተለየ አላማ የመፈፀም ጉዳይ ነው፡፡
የአንዱ መለኪያ ለሌላው መለኪያ ሊሆን አይችልም፡፡ እያንዳንዱ የራሱን የሚለካው በተሰጠው ነገር ብቻ ነው፡፡
ነገር ግን እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሥራ ይፈትን፥ ከዚያም በኋላ ስለ ሌላው ሰው ያልሆነ ስለ ራሱ ብቻ የሚመካበትን ያገኛል፤ ወደ ገላትያ ሰዎች 6፡4
ራሳቸውን ከሚያመሰግኑ ከአንዳንዶች ጋር ራሳችንን ልንቆጥር ወይም ራሳችንን ልናስተያይ አንደፍርምና፤ ነገር ግን እነርሱ ራሳቸውን ከራሳቸው ጋር ሲያመዛዝኑ፥ ራሳቸውንም ከራሳቸው ጋር ሲያስተያዩ፥ አያስተውሉም። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10፡12
የሚመካበት
2. የሰው ህይወቱና አገልግሎቱ የሚለካው በተሰጠው መጠን ብቻ ነው
የሰው ህይወቱና አገልግሎቱ የሚለካው ለእርሱ በተሰጠው ነገር ብቻ ሳይሆነ በተሰጠው መጠን ብቻ ነው፡፡ ከመሬት ተነስተን ስለሰው ህይወትና አገልግሎት መተቸት የማንችለው ስለዚህ ነው፡፡ ሊጠይቅ የሚችለው ምን ያህል እንደሰጠው የሚያውቅው እግዚአብሄር ወይም እግዚአብሄር የገለጠለት ሰው ብቻ ነው፡፡ ሰው የሚፈለግበት በተሰጠው መጠን ብቻ ነው ፡፡
ያላወቀ ግን መገረፍ የሚገባውንም ያደረገ ጥቂት ይገረፋል። ብዙም ከተሰጠው ሰው ሁሉ ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል፥ ብዙ አደራም ከተሰጠው ከእርሱ አብዝተው ይሹበታል። የሉቃስ ወንጌል 12፡48
ነገር ግን እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሥራ ይፈትን፥ ከዚያም በኋላ ስለ ሌላው ሰው ያልሆነ ስለ ራሱ ብቻ የሚመካበትን ያገኛል፤ ወደ ገላትያ ሰዎች 6፡4
3. የሰው ህይወቱና አገልግሎቱ የሚለካው በእግዚአብሄር ብቻ ነው፡፡
ሰው ተነስቶ ወድቄያለሁ ማለት አይችልም፡፡ ሰው ሌላው ሰው ወድቀሃል ሲለው ማመን የለበትም፡፡ ሰውን ወድቀሃል የሚለው እግዚአብሄ ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄር መንንም አይፈራም፡፡ እግዚአብሄር ከተሳሳትክ የዛዙዙ ጊዜ ይነግርሃል፡፡ በአብዛኛው እግዚአብሄርን እየተከተልክ እግዚአብሄር ይናገርህ ይችላል፡፡ እግዚአብሄር የሚናገርህ ስትሳሳት ነው፡፡ እግዚአብሄር ስትሳሳት ከተናገረህ ባልተናገረህ ጊዜ አልተሳሳትክም ማለት ነው፡፡ ራሰህን አትኮንን፡፡ ሰወም ሲኮንንህ አትቀበል፡፡
ነገር ግን በእናንተ ዘንድ ወይም በሌላ ሰው ዘንድ ብፈረድ ለእኔ ምንም አይደለም፤ እኔም በራሴ እንኳ አልፈርድም፤ 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 4፡3
ህይወታችንና አገልግሎታችን የሚመዘነው በታማኝነት ነው፡፡ ህይወታችንና አገልግሎታችን በሃይላችን ፣ በባለጥግነታችን ፣ በዝናችንና በእውቀታችን አይለካም፡፡ ነገር ግን ጊዜያችንን እውቀታችንን ገንዘባችንን እንዴት እንደተጠቀምንበት በታማኝነታችን ይለካል፡፡ እንዲነግድና እንዲያተርፍበት አንድ መክሊት የተሰጠው ህይወቱና አገልግሎቱ የሚለካው በሶስት መልሊት ሳይሆን በአንድ መክሊት ነው፡፡
አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና ሌላ አምስት መክሊት አስረክቦ፦ ጌታ ሆይ፥ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ አምስት መክሊት አተረፍሁበት አለ። ጌታውም፦ መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው። የማቴዎስ ወንጌል 25፡20-21
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #መሪ #ታማኝነት #መክሊት #ትጋት #ጥቂት #ብዙ #ጊዜ #ጉልበት #እውቀት #ሃይል #ዝና #ምሳሌ #ፍቅር #ምህረት #ይቅርታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አገልጋይ #መንፈስቅዱስ #ምስክር #ልብ #መሪ
No comments:
Post a Comment