ብዙ ጊዜ አመት ሲጠቀስ አብሮ ዓ.ም. ወይም አመተ ምህረት ተብሎ ይጠቀሳል፡፡ ይህ አመተ ምህረት የሚለው ቃል የሚያመለክተው ኢየሱስ ስለሃጢያታችን በመስቀል ላይ ሊሰቀል ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ያለውን ጊዜ ነው፡፡ አመተ ምህረት የሚባለው ለሃጢያታችን እዳን ለመክፈል በመስቀል ላይ ለመሞት ከመጣበት ከሁለት ሺህ አመት ጀምሮ ኢየሱስ ተመልሶ እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ ነው፡፡
ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ። የማቴዎስ ወንጌል 1፡21
እስካሁን ያለውን ጊዜ ያልኩበት ምክኒያት ኢየሱስ በየትኛውም ጊዜ ተመልሶ ስለሚመጣ ነው፡፡ ኢየሱስ ተመልሶ የሚመጣበት ጊዜ ስለማይታወቅ ወይም እያንዳንዳችን ከዚህ አለም የምንወሰድበት ጊዜ ስለማይታወቅ ነው፡፡ አንድ የማውቅው ነገር ኢየሱስ እስካሁን ተመልሶ አለመምጣቱን ነው፡፡
ከሞትን በኋላ ኢየሱስን ለመቀበል አንችልም፡፡ ኢየሱስን አዳኝ አድርጎ የመቀበል እና ከዘላለም ጥፋት የመዳን እድል ያለው በአመተ መህርት በህይወት ያለ ሰው ብቻ ነው፡፡
ለሰዎችም አንድ ጊዜ መሞት ከእርሱ በኋላም ፍርድ እንደ ተመደበባቸው፥ ወደ ዕብራውያን 9፡27
አመተ ፍዳ የሚባለው ደግሞ ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት የነበረው አመታት ነው፡፡ አመተ ፍዳ ሁላችን ከሃጢያት በታች ተዘግተን በባርነት ስንኖርበት የነበረውን ከሃጢያታችን የመዳን እድል ያልነበረበትን አመታት ነው፡፡
ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤ ወደ ሮሜ ሰዎች 3፡23
በጣም የሚያሳዝነው ነገር ግን በአመተ ምህረት ውስጥ በፍዳ የሚኖሩ ሰዎች መኖራቸው ነው፡፡ እግዚአብሄር በተከታታይ አዲስ አመታትን ቢሰጣቸውም ግን ንስሃ በመግባት ከእግዚአብሄር ጋር ለመታረቅ በዚህ በምህረት አመት የማይጠቀሙበት ሰዎች ምስኪን ሰዎች ናቸው፡፡ ኢየሱስ ለሃጢያታቻው በመስቀል ላይ ቢሰቀልም ነገር ግን ይህን ምህረት ያልተቀበሉ ሰዎች የምህረት አመቱ ተጠቃሚ ያልሆኑ ሰዎች ናቸው፡፡ ኢየሱስ የሃጢያታችውን እዳ ሁሉ በመስቀል ላይ ቢከፍልም ለሃጢያታችው በራሳቸው ስራ ለመክፈል የሚፈልጉና የእግዚአብሄርን የፀጋ ስጦታ ያልተቀበሉ ሰዎች ከእግዚአብሄር የመዳኛ መንገድ የራቁ ሰዎች ናቸው፡፡
ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 2፡8-9
አሁን ይህን ፅሁፍ የምታነቡ ኢየሱስ ከሙታን በልባችሁ በማመን እንደምትፀድቁ ኢየሱስ ከሙታን እንደተነሳ እና ጌታ እንደሆነ በአፋችሁ በመመስከር መዳን እንደምትችሉ የእግዚአብሄር ቃል ይናገራል፡፡
ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና። ወደ ሮሜ ሰዎች 10፡9-10
ይህንን ፀሎት ከልብህ በመፀለይ የእግዚአብሄር ልጅ አድርጎ እግዚአብሄር እንዲቀበልህ ማድረግ ትችላለህ፡፡
እግዚአብሄር ሆይ ሃጢያተኛ ነኝ፡፡ የሃጢያት ደሞዝ ደግሞ ለዘላለም ከአንተ መለየት ነው፡፡ እግዚአብሄር ከሃጢያት ለመዳኛ ያዘጋጀኸውን የሃጢያት መስዋእት ኢየሱስን እቀበላለሁ፡፡ እየሱስ ስለሃጢያቴ በእኔ ምትክ በመስቀል ላይ እንደተሰቀለና እንደሞተ ከሞትም እንደተነሳ አምናለሁ፡፡ ኢየሱስን በህይወቴ ላይ ጌታ አድርጌ እሾመዋለሁ፡፡ ኢየሱስን በህይወቴ ዘመን ሁሉ እከተለዋለሁ፡፡ እግዚአብሄር ሆይ ልጅህ አድርገህ ስለተቀበልከኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ የዘላለም ህይወት ስለሰጠኸኝ አመሰግናለሁ፡፡ በኢየሱስ ስም፡፡ አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment