በአለም በጥላቻና በንቀት የተሞሉ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ ሰዎች ይንቋችኋል፡፡ ሰዎች በክፋት ይሰድቧችኋል፡፡ ሰዎች ፍላጎታቸውን ለማሟላት ውሸትን ይናገሩባችኋል፡፡ ሰዎች በክፉ ስማችሁን ያጠፋሉ፡፡ ሰዎች እናንተን ለማዋረድ ይዋሹባችኋል፡፡ ሰዎች እግዚአብሄር የሰጣቸውን ስራ ትተው ስራዬ ብለው ያሳድዱዋችሁዋል፡፡
ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ። ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና። የማቴዎስ ወንጌል 5፡11-12
ማንንም ሳይጠላ ይህን ሁሉ ማለፍ የሚችል ሰው የተባረከ ሰው ነው፡፡ ብዙ ገንዘብ ካለው ሰው በላይ ብዙ ፍቅር ያለው ሰው ይሻላል፡፡ ብዙ ዝና ካለው ሰው ይልቅ ሲበደል ማለፍ የሚችል ሰው ይበልጣል፡፡ ብዙ እውቀት ካለው ሰው ይልቅ ለሚያሳድዱት ሰዎች ትእግስት ያለው ሰው ይበልጣል፡፡ ከሃያል ሰው ይልቅ የሚንቁትን ሰዎች መልሶ ከመናቅ ይልቅ በርህራሄ የሚያከብር ሰው ይበልጣል፡፡ ክፉን በክፉ ፋንታ ከሚመልስ ሰው ይልቅ በደልን የማይቆጥር ሰው ይበልጣል፡፡
ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን አስቡ። ወደ ሮሜ ሰዎች 12፡17
የሰውን ክፋት ስቆ የሚያልፍ ልብ ያለው ሰው የተባረከ ሰው ነው፡፡ የበደሉትን ሰዎች በይቅርታ የሚለቅቅ ሰው የነፃነትን አየር ይተንፍሳል፡፡ ለሰዎች የክፋት ንግግር ቦታ የማይሰጥ ሰው የተባረከ ነው፡፡ የሰዎች የንቀት ንግግር ህይወቱን የማይነካው ሰው የተባረከ ነው፡፡
የሚያሳድዱአችሁን መርቁ፥ መርቁ እንጂ አትርገሙ። ወደ ሮሜ ሰዎች 12፡14
ሰዎች የፈለጉትን እና የቻሉትን ያህል ክፋት ሲናገሩበት በክፉ ፋንታ ክፉ የማይመልስ ሰው የተባረከ ነው፡፡ ሰዎች ሲሰድቡት መልሶ ከማይሳደብ ነገር ግን ከሚባርክ ሰው በላይ የተባረከ ሰው የለም፡፡
ክፉን በክፉ ፈንታ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ በዚህ ፈንታ ባርኩ እንጂ፥ በረከትን ልትወርሱ ለዚህ ተጠርታችኋልና። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 3፡9
የሚያሙትን ሰዎች የሚያሳፍር ለሁሉም ሰው በጎ ህሊና እንዳያጣ የሚጠነቀቅ ሰው የተባረከ ነው፡፡
በክርስቶስ ያለውን መልካሙን ኑሮአችሁን የሚሳደቡ ሰዎች ክፉን እንደምታደርጉ በሚያሙበት ነገር እንዲያፍሩ በጎ ሕሊና ይኑራችሁ። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 3፡16
ኢየሱስን መከተል ኢየሱስ ሲሰድቡት መልሶ እንዳልተሳደበ ሰዎች ሲሰድቡን መልሰን አለመሳደብ ነው፡፡
እርሱም ኃጢአት አላደረገም፥ ተንኰልም በአፉ አልተገኘበትም፤ ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል አልዛተም፥ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤ 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 2፡22-23
እግዚአብሄር ክፉን በክፉ የመመለስ ሳይሆን ክፉን በመልካም የመመለስ መንፈስ ነው፡፡ ክፉን በክፉ የመመለስ የበቀል መንፈስ ከእግዚአብሄር የተሰጠን መንፈስ አይደለም፡፡
እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና። 2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 1፡7
ተወዳጆች ሆይ፥ ራሳችሁ አትበቀሉ፥ ጠላትህ ግን ቢራብ አብላው፤ ቢጠማ አጠጣው፤ ይህን በማድረግህ በራሱ ላይ የእሳት ፍም ትከምራለህና። ክፉውን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ። ወደ ሮሜ ሰዎች 12፡19-21
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #እግዚአብሔር #ይቅርታ #ምህረት #በቀል #ጠላት #ዲያቢሎስ #ስፍራ #ኢየሱስ #ጥላቻ #ትእቢት #መራርነት #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ
No comments:
Post a Comment