Popular Posts

Tuesday, September 4, 2018

እግዚአብሄር የማይሰማቸው አምስት አይነት ፀሎቶች

በብዙ ቦታዎች ደጋግመንና አብዝተን ወደ እርሱ እንድንፀልይ መፅሃፍ ቅዱስ ደጋግሞ ያስተምረናል፡፡ እግዚአብሄር የመርህ አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሄር የሚፈልገውና የማይፈክልገው ነገር አለ፡፡ እግዚአብሄር ፀሎት ስለሆነ ብቻ አይመልስልንም፡፡ እንደፈቃዱ ከፀለይን ይሰማናል፡፡ እንደ ፈቃዱ ያልሆኑ እግዚአብሄ የማይሰማቸው የፀሎት አይነቶች ከዚህ በታች ተዘርዝርዋል፡፡
በእርሱ ዘንድ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል። 1ኛ የዮሐንስ መልእክት 5፡14
1.      የቅንጦት ፀሎት
እግዚአብሄር የመሰረታዊ ፍሎጎት ፀሎቶችን የሰማል ይመልሳል፡፡ እግዚአብሄር ግን የቅንጦት በጀት የለውም፡፡ እግዚአብሄር ለቅንጦት የምንፀልየውን ፀሎት አይሰማም፡፡ እግዚአብሄር ግን የስጋ ፍላጎታችንን ለማሟላት አብሮን አይሰራም፡፡ እግዚአብሄር ለስጋ ፍጎታችን ቦታ የለውም፡፡
ትለምናላችሁ፥ በምቾቶቻችሁም ትከፍሉ ዘንድ በክፉ ትለምናላችሁና አትቀበሉም። የያዕቆብ መልእክት 4፡3
ትለምናላችሁ ግን አትቀበሉም፤ ለራሳችሁ ሥጋዊ ደስታ በማሰብ በክፉ ምኞት ትለምናላችሁና። የያዕቆብ መልእክት 4፡3 (አዲሱ መደበኛ ትርጉም)
2.     የጥርጥር ፀሎት
እግዚአብሄር ንጉስ ነው፡፡ እግዚአብሄር ባጣ ቆየኝ የምንለው መጠባበቂያ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር በፍፁም ልብ እንድንፈልገው ይፈልጋል፡፡
ነገር ግን በምንም ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፤ የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባሕርን ማዕበል ይመስላልና። ሁለት አሳብ ላለው በመንገዱም ሁሉ ለሚወላውል ለዚያ ሰው ከጌታ ዘንድ አንዳች እንዲያገኝ አይምሰለው። የያዕቆብ መልእክት 1፡6-8
እናንተ ትሹኛላችሁ፥ በፍጹም ልባችሁም ከሻችሁኝ ታገኙኛላችሁ። ከእናንተም ዘንድ እገኛለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ምርኮአችሁንም እመልሳለሁ፥ ከአሕዛብም ሁሉ ዘንድ እናንተንም ካሳደድሁበት ስፍራ ሁሉ እሰበስባችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እናንተንም ለምርኮ ወዳፈለስሁበት ስፍራ እመልሳችኋለሁ። ትንቢተ ኤርምያስ 29፡13-14
3.     የጥላቻ ፀሎት
የበደለህን ሰው እንኳን እግዚአብሄር ልክ እንዲያስገባው ብትፀልይ ፀሎትህ አይመለስም፡፡ እግዚአብሄር ሳይበድልህ በፊት እንደሚበድልህ ያውቃል፡፡ አንተ የበደሉህን ይቅር ማለት እንድትችል እግዚአብሄር የበደልከውን ሁሉ አስቀድሞ ይቅር ብሎሃል፡፡ እግዚአብሄር የበደልከውን ይቅር ካለህ ከዚያ ታላቅ ይቅርታ ላይ እየቀነስክ ሌሎችን ይቅር እንድትል እግዚአብሄር  አስቀድሞ ይቅር ብሎሃል፡፡ አሁን የበደለህ እንዳይሳካለት ብትቋጥርበት ፣ ብትመኝ ፣ ብትወጣና ብትወርድ ምንም የምታመጣው ነገር የለም፡፡  ማድረግ የምትችለው አንድ ነገር የበደለህን ለቅቀህ የራስህን ኑሮ መኖር መጀመር ነው፡፡ ሰውን እንዲቀንሰው የምትለምነውን ፀሎት ሳይሆን እንተን እንዲጨምርህ የምትለምነውን ፀሎት እግዚአብሄር ይሰማሃል፡፡ ሰውን እንዲቀጣው ሳይሆን እንተን እንዲምርህ የምትለምነውን ፀሎት ይሰማሃል፡፡
ለጸሎትም በቆማችሁ ጊዜ፥ በሰማያት ያለው አባታችሁ ደግሞ ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲላችሁ፥ በማንም ላይ አንዳች ቢኖርባችሁ ይቅር በሉት። እናንተ ግን ይቅር ባትሉ በሰማያት ያለው አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም። የማርቆስ ወንጌል 11፡25-26
4.     የውድድር ፀሎት
እግዚአብሄር የትህትናን እንጂ የትእቢትን ፀሎት አይሰማም፡፡
ጻድቃን እንደ ሆኑ በራሳቸው ለሚታመኑና ሌሎቹን ሁሉ በጣም ለሚንቁ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፥ እንዲህ ሲል፦ ሁለት ሰዎች ሊጸልዩ ወደ መቅደስ ወጡ፥ አንዱ ፈሪሳዊ ሁለተኛውም ቀራጭ። ፈሪሳዊም ቆሞ በልቡ ይህን ሲጸልይ፦ እግዚአብሔር ሆይ፥ እንደ ሌላ ሰው ሁሉ፥ ቀማኞችና ዓመፀኞች አመንዝሮችም፥ ወይም እንደዚህ ቀራጭ ስላልሆንሁ አመሰግንሃለሁ፤ በየሳምንቱ ሁለት ጊዜ እጦማለሁ፥ ከማገኘውም ሁሉ አሥራት አወጣለሁ አለ። ቀራጩ ግን በሩቅ ቆሞ ዓይኖቹን ወደ ሰማይ ሊያነሣ እንኳ አልወደደም፥ ነገር ግን፦ አምላክ ሆይ፥ እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ እያለ ደረቱን ይደቃ ነበር። እላችኋለሁ፥ ከዚያ ይልቅ ይህ ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፥ ራሱን ግን የሚያዋርድ ከፍ ይላል። የሉቃስ ወንጌል 18፡9-14
5.     የማጉረምረም ፀሎት
እግዚአብሄር ንጉስ ነው፡፡ እግዚአብሄር ጋር ሰንቀርብ እግዚአብሄር ላይ እንከን እንዳገኘንበት በማጉረምረም መሆን የለበትም፡፡ እግዚአብሄር ጋር ስንቀርብ በትህትና እና በምስጋና መሆን አለበት፡፡ እግዚአብሄር ጋር ስንቀርብ እግዚአብሄር ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ነገር እንደሚያደርግልን ሳይሆን ብዙ ነገር እንደሰጠን አንድ ተጨማሪ ነገር እንዲሰጠን እንደቀረበን አይነት በአክብሮት በደስታና በምስጋና መሆን አለበት፡፡
በደስታም ለእግዚአብሔር ተገዙ፥ በሐሤትም ወደ ፊቱ ግቡ። ወደ ደጆቹ በመገዛት፥ ወደ አደባባዮቹም በምስጋና ግቡ፤ አመስግኑት፥ ስሙንም ባርኩ፤ እግዚአብሔር እርሱ አምላክ እንደ ሆነ እወቁ፤ መዝሙረ ዳዊት 100፡2-4
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #የእግዚአብሄርፈቃድ #ፀሎት #ልመና #ማጉረምረም #ምስጋና #ቅንጦት #ጥርጥር #እንደፈቃዱ #መንፈስቅዱስ #እንዲሰማን #ቤተክርስትያን #አማርኛ #የእግዚአብሄርቃል #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #መጠየቅ #መንበርከክ #ይቃትታል

No comments:

Post a Comment