Popular Posts

Follow by Email

Thursday, September 6, 2018

ሚስቶች ላለመታዘዝ ያላቸው አራት አለማቀፋዊ ጥያቄዎች

ለእያንዳንዳችሁ በክርስቶስ ፍርሃት የተገዛችሁ ሁኑ። ሚስቶች ሆይ፥ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁ ተገዙ፤ ክርስቶስ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደ ሆነ እርሱም አካሉን የሚያድን እንደ ሆነ ባል የሚስት ራስ ነውና። ዳሩ ግን ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ እንዲሁ ሚስቶች ደግሞ በሁሉ ለባሎቻቸው ይገዙ። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 5፡22-24
ትዳር የሰው ሃሳብ አይደለም፡፡ ትዳርን ያቀደውና የመሰረተው እግዚአብሄር ነው፡፡ ትዳር የእግዚአብሄር ተቋም ነው፡፡ እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው በመልኩና በአምሳሉ ወንድና ሴት አድርጎ ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ሙሉ መልክ የሚገልጡት ወንድና ሴት ናቸው፡፡ ወንድ ብቻ የእግዚአብሄርን ሙሉ መልክ ሊገለጥ አይችልም ሴት ብቻ የእግዚአብሄርን መልክ ልትገልጥ አትችልም፡
ባልና ሚስት የእግዚአብሄርን መልክ እንዴት ሊገልጡ እንደሚችሉ በእግዚአብሄር ቃል ላይ በግልፅ ተቀምጧል፡፡ ባልና ሚስት እግዚአብሄር በቃሉ ያዘዘውን ነገር ካደረጉ በግንኙነታቸው የእግዚአብሄር መልክ ይገለጣል፡፡ ባልና ሚስት በቤተሰብ ውስጥ እግዚአብሄር በቃሉ ያስቀመጠላቸውን ሃላፊነት ከተወጡ በምድር ላይ የእግዚአብሄርን አላማ በመፈፀም እግዚአብሄርን ያከብራሉ፡፡  ባልና ሚስት ሳያሻሽሉ እና ሳይለውጡ በቃሉ የተፃፈላቸውን የእያንዳንዳቸውን የቤተሰብ ሃላፊነት ከተወጡ በቤተሰባቸው በምድር ላይ እግዚአብሄርን ያሳያሉ፡፡
ትዳር የእግዚአብሄርን መኖር በዝምታ ይናገራል የሚባለው ስለዚህ ነው፡፡
ነገር ግን ትዳር ፈተና አለው፡፡ መታዘዝ ቀላል አይደለም፡፡ ሚስት ለባልዋ እንዳትታዘዝ ትፈተናለች፡፡ መታዘዝ ትህትናን መሰጠትን እና ፍቅርን ይጠይቃል፡፡
ሰው ሰው ነው፡፡ በየትም አገር ያሉ ሚስቶች ባላቸውን እንዳይታዘዙ የሚፈተኑበት ነገር አላቸው፡፡ ሚስቶች ለባሎቻቸው እንዳይታዘዙ በሚፈተኑበት ጊዜ የሚጠይቋቸውን ጥያቄዎችና እግዚአብሄር ቃል ስለ ጥያቄዎቻቸው የሚሰጠውን መልስ እንመልከት፡፡ 
1.      ባሌ የምፈልገው ያህል ባይወደኝም መታዘዝ አለብኝ?
ሚስቶች ለባላቸው ከታዘዙ በኋላ ከባላቸው ምላሽን ይፈልጋሉ፡፡ ምላሽን መፈለግ እና መጠበቅ ተፈጥሮአዊና መልካም ነገር ነው፡፡ ነገር ግን የሚስት መታዘዝ ከባል ምላሽ ጋር በተያያዘ መጠን ሚስት እግዚአብሄር በትዳሩ ውስጥ የሰጣትን ሃላፊነት በሚገባ መፈፀም እንዳትችል እንቅፋት ይሆንባታል፡፡ እንደእውነቱ ከሆነ ሚስት ላለመታዘዝ ምክኒያት አታጣም፡፡ ሚስት ላመታዘዝ ምክኒያት የለኝም ብትል ትዋሻለች፡፡ ሚስት ባልዋን በነገር ሁሉ የምትታዘዝው ምክኒያቶችን ሁሉ ባለመቀበል ነው፡ 
አንዳንዴ ሚስቶች በራሳቸው ላይ ይቀናሉ፡፡ እኔ እየታዘዝኩ እርሱ ለምን አይወደኝም የሚል ቅናት ያድርባቸዋል፡፡
እውነት ነው የሚስት መታዘዝ ለባል መውደድ የሚያደርገው ታላቅ አስተዋጽኦ ቢኖርም የሚስት መታዘዝ በባል መውደድ ላይ መወሰን ግን የለበትም፡፡ የሚስት መታዘዝ ለባል መውደድ የሚከፈል ክፍያ ሳይሆን የሚስት መታዝዝ ለባል መውደድ የሚሰጥ ማበረታቻ ነው፡፡ ባል መታተዝሽን ቢረዳም ባይረዳም ቢያመሰግንም ባያመሰግንም እውቅና ቢሰጠውም ባይሰጠውም የእግዚአብሄር ፈቃደ አድርገሽ ጌታን ማክበር ይገባሻል፡፡  
እንዲሁ እናንተ ደግሞ የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ፦ የማንጠቅም ባሪያዎች ነን፥ ልናደርገው የሚገባንን አድርገናል በሉ። የሉቃስ ወንጌል 17፡10
የሚስት መታዝዝ የባልን መውደድ መቼና እንዴት እንሚያመጣ ፎርሙላ የለውም፡፡ ነገር ግን ሚስት የባልዋ ምላሽ ሳያግዳት በባልዋ ላይ መታዘዝ በዘራች መጠን ባልዋ እንዲወዳት ሃይልን ትሰጠዋለች፡፡ ሚስት የባልዋ ምላሽ ሳያግዳት ባልዋ በታዘዘች መጠን የእግዚአብሄርን ሃሳብ መፈፀም ትችላለች፡፡ ሚስት ባልዋን በመታዘዝ ሃላፊነትዋ ላይ ብቻ ካተኮረች ትባረካለች፡፡ ሚስት የባልዋን መውደድ ለእርስዋ መታዘዝ ቅድመ ሁኔታ ካላደረገች ዋነኛው ባልዋ እግዚአብሄር ይባርካታል፡፡
ፈጣሪሽ ባልሽ ነው፥ ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው፤ የእስራኤልም ቅዱስ ታዲጊሽ ነው፥ እርሱም የምድር ሁሉ አምላክ ይባላል። ትንቢተ ኢሳይያስ 54፡5
እግዚአብሄር ባልዋንም ተጠቅሞ ይሁን በቀጥታ እንደሚባርካት ካወቀች በቀጣይነይት ለባልዋ በመታዘዝ የክርስቶስን ህግ ትፈፅማለች፡፡ ሚስት የቤተሰብ ሃላፊነትትዋን በመወጣትዋ ላይ እንጂ ከባልዋ በምታገኘው የትዳር ጥቅም ላይ ከመጠን በላይ መደገፍ የለባትም፡፡
ዳሩ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እናገራለሁ፤ ዘመኑ አጭር ሆኖአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌላቸው ይሁኑ፥ 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 7፡29
2.     ባሌ ቢሳሳት መታዘዝ አለብኝ?
ሚስት ባልዋን የምትከለተለው እግዚአብሄር ይመራዋል ብላ አምና ነው፡፡ ሚስት ባልዋን የምታምነው እግዚአብሄርን በማመን ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ሃይልና ጥበብ የተረዳች ሚስት ሁሉን ለራሱ ማስገዛት በሚችል አሰራሩ ባሌን ይመራዋል ብላ ታምናለች፡፡ እግዚአብሄር ባልን የቤተሰቡ መሪ አድርጎ ፈጥሮታል፡፡ ስለተማረ ስላለተማረ ሳይሆን ባል በውስጡ ከቤተሰብ መሪነት ክህሎት ጋር ተወልዷል፡፡
ባል ሊሰሳት አይችልም ማለት አይቻልም፡፡ ሚስትም ልትሳሳት እንደምትችል ባልም ሊሳሳት ይችላል፡፡ ባል ቢሳሳት መንገርና ማስረዳ የመጨረሻውን ውሳኔ ለራሱ መተው ይጠይቃል፡፡ ሚስት ባልክዋን በመታዘዝ ላትስት ትችላለች፡፡ ሚስት ባልዋን ባለመታዘዝ ከምትሳሳት ይልቅ ባል ቤተሰቡን ለመመራት በሚወስድው ውሳኔ ቢሳሳት እግዚአብሄር ያርመዋል፡፡ ባል ከተሳት እግዚአብሄር ለመልካም እንደሚለውጠው በእግዚአብሄር ማመን የቤተሰቡን አንድነት ለመጠበቅ ይረዳል፡፡  
ነገር ግን የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፥ የሴትም ራስ ወንድ፥ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር እንደ ሆነ ልታውቁ እወዳለሁ። 1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 11፡3
3.     ባሌ በምን በምን ይበልጠኛል?
ባልና ሚስት የተለያዩ እንጂ የሚበላለጡ አይደሉም፡፡ የባልና የሚስት ሃላፊነት የውድድርና የፉክክር ሳይሆን የአንድነትና የህብረት ነው፡፡ ባል ቤተሰብን በመምራት ሲያገለግል ሚስት ቤተሰብን በማስተዳደር ታገለግላለች፡፡ ባል ቤተሰብን በማረም ሲያገለግል ሚስት ለቤተሰብ ምቾትና ደስታን በመስጠት ታገለግላለች፡፡ ባል ችግሮችን ከፊት ሆኖ በመጋፈጥ ሲያገልግል ሚስት ከኋላ ሆና ነገሮችን በማስተዳደር ታገለገላለች፡፡ የባል መሪነት የጥቅም ጉዳይ ሳይሆን ሃላፊነት ነው፡፡ ባልን የምትታዘዘው ስለሚበልጥ የማትታዘዘው ስለሚያነሰ ሳይሆን የመምራት ሃላፊነቱ የተሰጠው ባል ስለሆነ ስልእግዚአብሄ ስርአት ነው፡፡ ባል መታዘዝ የሚገባው ስለ ባልነት ስልጣኑ እና ቦታው እንጂ ስለ እከሌነቱ እና ስለመብለጡ አይደለም፡፡ የአገር ሚኒስትር የሆነች ሚስት ለባልዋ ሚስት እና ታዛዥ ነች፡፡ የአገር ሚንስትር የሆነች ሚስት ለእግዚአብሄር ስርአት ለባልዋ የባልነት ስልጣን በመታዘዝዋ እግዚአብሄር ይባርካታል፡፡
ስለዚህ ደግሞ ትገብራላችሁና፤ በዚህ ነገር የሚተጉ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸውና። ለሁሉ የሚገባውን አስረክቡ፤ ግብር ለሚገባው ግብርን፥ ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን፥ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፥ ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ። ወደ ሮሜ ሰዎች 13፡ 5-7
አንድ ያለው ውድድር ሃላፊነትን በመወጣት አንዱ ሌላውን ይበልጥ የማገልገል የመሸከም አና የመጥቀም እንጂ የስልጣን ውድድር አይደለም፡፡  
ኢየሱስ ግን ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ የአሕዛብ አለቆች እንዲገዙአቸው ታላላቆቹም በላያቸው እንዲሠለጥኑ ታውቃላችሁ። በእናንተስ እንዲህ አይደለም፤ ነገር ግን ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፥ ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የእናንተ ባሪያ ይሁን፤ የማቴዎስ ወንጌል 20፡24-27
4.     ባሌ ቢጎዳኝም መታዘዝ አለብኝ ?
ትዳር ታእምር ነው፡፡ ሁለት የተለያየ አስተዳደግ የተለያየ ባህል የተለያ አመለካከት የተለያየ ቤተሰብ ውስጥ ያደጉ ወንድና ሴት በአንድ ቤተሰብ በአንድ ሃሳብ ለአንድ አላማ መስራታቸው የእግዚአብሄር አሰራር ድንቅ እንደሆነ ይመሰክራል፡፡ 
በቤተሰብ ፍቅር ትህትናና የዋህነት ያስፈለገበት ምክኒያት አለመስማማት መጣላት መጎዳዳት ሊመጣ ስለሚችል ነው፡፡ በተለያየ ምክኒያት ሰዎች ይጎዱናል፡፡ እኛም በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ሰዎችን ልንጎዳ እንችላለን፡፡ አንዲትን ሴት መንገደኛ ቢጎዳት መልካም ነገር አይደለም፡፡ አንድን ወንድ ሌላ እንግዳ ሰው ቢጎዳው ዋጋ ሊከፈልለት የሚገባው መልካም ምክኒያት አይደለም፡፡   
ለማያውቅ የሚዋስ ክፉ መከራን ይቀበላል፤ ዋስነትን የሚጠላ ግን ይድናል። መጽሐፈ ምሳሌ 11፡15
ለማያውቀው ከተዋሰ ሰው ልብሱን ውሰድ፥ ለእንግዳ የተዋሰውንም እርሱን አግተው። መጽሐፈ ምሳሌ 11፡16
አንዲት ሴት በማያገባት ገብታ ዋጋ ብትከፍል ብልህ ውሳኔ አይደለም፡፡ በቤተሰብ ውስጥ ባል በሚስቱ የሚጎዳው መጎዳትና ሚስት በባልዋ የምትጎዳው መጎዳት ከኢንቨስትመንቶች ሁሉ አዋጪ ኢንቨስትመንት ነው፡፡ ባልና ሚስት ትዳርን ለመስራት በሚያደርጉት ጉዞ የሚከፈል ክፍያ የሚገባው ክፍያ ነው፡፡
ለትዳር የሚከፈል ዋጋ ግን ከምንችለው በላይ እንድንፈተን ለማይፈቅድ ለታማኙ ለእግዚአብሄር አሰራር የሚከፈል የሚገባው ዋጋ ነው፡፡  
ለእያንዳንዳችሁ በክርስቶስ ፍርሃት የተገዛችሁ ሁኑ። ሚስቶች ሆይ፥ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁ ተገዙ፤ ክርስቶስ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደ ሆነ እርሱም አካሉን የሚያድን እንደ ሆነ ባል የሚስት ራስ ነውና። ዳሩ ግን ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ እንዲሁ ሚስቶች ደግሞ በሁሉ ለባሎቻቸው ይገዙ። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 5፡22-24
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ህይወት #ጋብቻ #ትዳር #ባል #ሚስት #ፍቅር #መውደድ #መታዘዝ #መገዛት #ራስ #አንድስጋ #እውነት #ትህትና #ትንሳኤ #ህይወት #ወንጌል #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ  #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

No comments:

Post a Comment