Popular Posts

Follow by Email

Saturday, September 1, 2018

መንፈስ ቅዱስን የማሳዘናችን ምልክቶች


ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 4፡30
እግዚአብሄር በክብሩ ፈጥሮናል፡፡ እግዚአብሄር በመልኩ እና በአምሳሉ ፈጥሮናል፡፡ እኛ ስሜት እንዳለን እና የሚያስደስቱንና የሚያሳዝኑን ነገሮች እንዳሉ ሁሉ እግዚአብሄርን የሚያስደስቱትና የሚያሳዝበኑት ነገሮች አሉ፡፡
ለምሳሌ በህይወታችን እምነት እግዚአብሄርን እንደሚያስደስተው ሁሉ እንዲሁም እግዚአብሄርን የሚያሳዝኑንት ነገሮች አሉ፡፡
መፅሃፍ ቅዱስ በግልፅ የእግዚአብሄርን መንፈስ አታሳዝኑት ብሎ ያስጠነቅቀናል፡፡
ምክኒያቱም የእግዚአብሄር መንፈስ እግዚአብሄር ወደ አየልን የክብር ደረጃ ሊወስደን ሲመጣ ስራውን በህይወታችን ልናጠፋው በህይወታችን እንዳይሰራ ልናግደው እና የመንፈስን ስራ በሌላ በራሳችን ጥበብ ልንተካው እንችላለን፡፡  
መንፈስን አታጥፉ፤ 1ኛ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 5፡19
የእግዚአብሄርን መንፈስ እንዳሳዘንን ስንረዳ በፍጥነት በመመለስ እንደገና የእግዚአብሄርን መንፈስ ማስደሰት እንችላለን፡፡ ነገር ግን በትእቢት ስንቀጥል የእግዚአብሄር መንፈስ እንዳዘነ የሚያሳዩ ምልክቶችን ከእግዚአብሄር ቃል እንመልከት ፡-
1.      የመዳን ደስታችን ሲጠፋ
የእግዚአብሄር መንፈስ ከእኛ ጋር በሃይል የሚሰራ ከሆነ በምንም ነገር ውስጥ ብናልፍ ልባችንን ያፅናናዋል፡፡ የምናልፍበትን አስቸጋሪ ነገር በተስፋ እንታገሰዋለን፡፡ነገር ግን የመዳን ደስታችን ከጠፋ የክርስትና ጣእም እየጠፋብን ይሄዳል፡፡
የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ። ከፊትህ አትጣለኝ፥ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ። የማዳንህን ደስታ ስጠኝ፥ መዝሙረ ዳዊት 51፡10-12
2.     የፀሎት ፍላጎታችን ሲጠፋ
ፀሎት ከእግዚአብሄር ጋር ህብረት የምናደርግበት አስደሳች ነገር ሳይሆን ተራራ መግፋት ሲሆን የእግዚአብሄርን መንፈስ እንዳሳዘንን ራሳችንን ማየት ይገባናል፡፡
የእግዚአብሄር መንፈስ እንዳያዝንብን የምንጠነቀቅ ከሆንን እና የእግዚአብሄር መንፈስ የሚያዝንበትን ነገር ከተውን ፀሎታችን የጣፈጠ ይሆናል፡፡ ከእግዚአብሄር አባታችን ጋር ተነጋገርን እንጠግብም፡፡ በሃጢያታችን ንስሃ ሳንገባ  የእግዚአብሄር መንፈስ የሚያዝንበትን ነገር በተደጋሚ ማድረግ ከቀጠልን ግን ከእግዚአብሄር ጋር በፀሎት ያለውን ያለው የህብረት ደስታ እናጣዋለን፡፡
ከእርሱ ጋር ኅብረት አለን ብንል በጨለማም ብንመላለስ እንዋሻለን እውነትንም አናደርግም፤ ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ በብርሃን ብንመላለስ ለእያንዳንዳችን ኅብረት አለን፥ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል። 1ኛ የዮሐንስ መልእክት 1፡6-7
በዚያን ቀንም ከእኔ አንዳች አትለምኑም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል። እስከ አሁን በስሜ ምንም አልለመናችሁም፤ ደስታችሁ ፍጹም እንዲሆን ለምኑ ትቀበሉማላችሁ። የዮሐንስ ወንጌል 16፡23-24
3.     ነገሮችን በእምነት ሳይሆን በሙከራ ስናደርግ
የእግዚአብሄርን መንፈስ በቀጣይነት እያሳዘንን እንደሆነ የምናውቅበት አንደኛው ምልክት ከእምነት አለም ቀስ በቀስ መለየት ነው፡፡ በፊት እግዚአብሄርን ለእያንዳንዱ ነገር እናምን የነበረው አሁን ግን እምነታችንን በቴክኒክና በሰው ጥበብ እንተካዋለን፡፡ በእግዚአብሄር ነገር እያደግን ስንሄድ በእግዚአብሄር መታመን ያለው አስፈላፈጊነት መጨመር ሲገባው ቀስ በቀስ እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ የእግዚአብሄርን መንፈስ አብሮነት ስናጣው እምነትን ከሚያመጣው ከእግዚአብሄር ቃል ከባቢ እንለያለን፡፡ የእምነት ማጣታችንን እንዲተካልን ከኑሮ ፍርሃት የመነጨ የሰው ጥበብ ቃል እንተካበታለን፡፡  
ማንም በሚያባብል ቃል እንዳያስታችሁ ይህን እላለሁ። ወደ ቆላስይስ ሰዎች 2፡4
የእግዚአብሔርን ቃል ቀላቅለው እንደሚሸቃቅጡት እንደ ብዙዎቹ አይደለንምና፤ በቅንነት ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተላክን በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 2፡17
የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት ማታለል የሌላውም ነገር ምኞት ገብተው ቃሉን ያንቃሉ፥ የማያፈራም ይሆናል። የማርቆስ ወንጌል 4፡19
4.     በሰው ጥበብ ስንኖር
ሁሉንም ነገር በእግዚአብሄር ምሪት ሳይሆን በስሌትና በራሳችን ጥበብ ስናደርገው የእግዚአብሄርን መንፈስ በቀጣይነት በማዛዘን እንደኖርን እናውቃለን፡፡
የእግዚአብሄርን መንፈስ በቀጣይነት ስናሳዝን በእግዚአብሄ ምሪት ፋንታ የራሳችንን እቅድ መተካት እንጀምራለን፡፡ እግዚአብሄር ለእኛ እንደሚየታስብልን ስለማንተማመን ለራሳችን በማሰብ እና ለግል ጥቅማችን በመስራት ስራ ላይ እንጠመዳለን፡፡ ከእግዚአብሄር ያለን ቅንንት እና ንፅህና ይበላሻል፡፡
በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፥ እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና፤ ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ። 2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 11፡2-3
5.     ለሰዎች ያለን ፍቅር ሲቀዘቅዝ  
የእግዚአብሄርን መንፈስ በቀጣይነት የሚያሳዝን የሰው የእገዚአብሄርን ፍቅር ስለማይሰማን በፍቅሩ መኖር አንችልም፡፡ በእግዚአብሄር እንደተወደድን በደንብ ካልተረዳን የመወደድን ፍላጎት ራሳችንን በመውደድ እንተካዋለን፡፡ በእግዚአብሄር ፍቅር ያረፈ ሰው ሰዎችን በመውደድና በማገልገል ፍቅሩን ይገልፃል፡፡ በእግዚአብሄር ፍቅር እርግጠኛ ያለሆነ ሰው ግን በሰዎች ለመወደድና ለመገልገል ይሮጣል፡፡ ሰዎችን እንደ መጠቀሚያ መሳሪያ እንጂ በአገልግሎቱ ሊገለገሉ እንደሚገባቸው እንደ ክቡር የእግዚአብሄር ፍጥረቶች ማየት እናቆማለን፡፡
እግዚአብሄርን ማገልገል እንደጠቅም ሳይሆን እንመታለል እንቆጥረዋለን፡፡ እግዚአብሄርን ቃሉን እንዳለ ሳይሆን በጥርጣሬ እንመለከተዋለን፡፡ በእግዚአብሄር ላይ ያለንን እምነት እንዳጣን የሚያስታውቀው በእግዚአብሄር አሰራር ፋንታ የራሳችንን የማምለጫ መንገድ እንተካበታለን፡፡
አንድ መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፦ ጌታ ሆይ፥ ካልዘራህባት የምታጭድ ካልበተንህባትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ፥ መክሊትህ አለህ አለ። የማቴዎስ ወንጌል 25፡24-25
6.     ከመፀፀት ይልቅ ጥፋታችንን ለመደበቅ ሌላ ጥፋት ስንጨምርበት
በቅንነታ ተሳሳችላሁ ብለን ራሳችን ከማዋረድ ይልቅ ለጥፋታችን መሸፈኛ ሌላ ጥፋት ውስጥ ስንገባ ለውሸታችን መሸፈኛ ሌላ ውሸት ውስጥ ስንገባ የእግዚአብሄርን መንፈስ እንዳሳዘንን ምልክቱ ነው፡፡
ኃጢአቱን የሚሰውር አይለማም፤ የሚናዘዝባትና የሚተዋት ግን ምሕረትን ያገኛል። መጽሐፈ ምሳሌ 28፡13
ስለዚህ ውሸትን አስወግዳችሁ፥ እርስ በርሳችን ብልቶች ሆነናልና እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 4፡25
7.     ለውጭው እንጂ ለውስጡ ንፅህናችንና ጤንነታችን መጠንቀቅ ስናቆም
የእግዚአብሄርን መንፈስ ካሳዘንን እና በምናደርገው ነገር የእግዚአብሄር መንፈስ እሺታውን እንዳለሰጠን ስንረዳ በሰው ፊት ለመከበር እንጂ በእግዚአብሄር ፊት ያለውን ክብር አንፈልግም፡፡ 
እናንተ እርስ በርሳችሁ ክብር የምትቀባበሉ ከአንዱም ከእግዚአብሔር ያለውን ክብር የማትፈልጉ፥ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ? የዮሐንስ ወንጌል 5፡44
አቤቱ፥ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፥ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ። ከፊትህ አትጣለኝ፥ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ። የማዳንህን ደስታ ስጠኝ፥ በእሽታ መንፈስም ደግፈኝ። መዝሙረ ዳዊት 51፡10-12
ሁልጊዜ እግዚአብሔርን በፊቴ አየዋለሁ፤ በቀኜ ነውና አልታወክም። መዝሙረ ዳዊት 16፡8
የሕይወትን መንገድ አሳየኸኝ፤ ከፊትህ ጋር ደስታን አጠገብኸኝ፥ በቀኝህም የዘላለም ፍሥሐ አለ። መዝሙረ ዳዊት 16፡11
ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 4፡30
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ማካፈል share ማድረግ ቢወዱለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ልብ #መዳን #እምነት #መንንፈስንአታጥፉ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #የዘላለምህይወት #ፅናት #መንፈስ #መንፈስቅዱስ

No comments:

Post a Comment