Popular Posts

Follow by Email

Monday, September 3, 2018

ሰዎች የሚከተሏቸው ህይወትን የማይለውጡ አምስት ነገሮች


ብዙ ሰዎች ህይወታቸውን የሚለውጠውን ነገር አይከተሉም፡፡ ብዙ ሰዎች የህይወት ለውጥ ምክኒያት የሚሆናቸውን ነገር ችላ ይላሉ፡፡ ብዙ ሰዎች ህይወታቸውን የሚለውጥ እየመሰላቸው ህይወታቸውን የማይለውጠውን ነገር በከንቱ ሲከተሉ ህይወታቸውን ይፈጃሉ፡፡

የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። ወደ ሮሜ ሰዎች 12፡2
1.      ሃብት
ብዙ ሰዎች ሃብትን የሚፈልጉት ሃብት ቢኖረኝ ህይወቴ ይለወጣል ብለው ስለሚያስቡ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች የሃብት አፈላለፈጋቸው ሁኔታ ሃብት ህይወትን የሚለውጥ ይመስላቸዋል፡፡ ሃበተ ውስን ነው፡፡ ሃበተ ህይወትን የመለወጥ አቅም የለውም፡፡ ሃብት ህይወትን እንደማይለውጥ ሃብት ኖሯቸው ከሚመሰክሩ ሰዎች በላይ ሃብት በራሱ ህይወትን እንደማይልወጥ ሊመሰክረ የሚችል እውነተኛ ምስክር የለም፡፡
ሃብት ስጦታ ነው፡፡ ስጦታ ደግሞ ሃላፊነትም እንጂ ስልጣን ብቻ አይደለም፡፡ ሃብት ሲመጣ አብረው የሚመጡ አዳዲስ ሃላፊነቶች  አሉ፡፡ ሰው በባህሪ ማደጉ ሃብቱን በሚገባ እንዲያስተዳደር ይስችለዋል፡፡ ሰው ሃብት ከሚፈለግ ይልቅ ሃብቱን የሚይዝበትን የባህሪ እድገት ቢፈልግ ፍሬያማ ይሆናል፡፡ ሃብት ባህሪ ወዳለው ሰው ይመጣል፡፡ ባህሪ ካለው ሰው ጋር ይቆያል፡፡ ሃብት ባህሪ የሌለውን ሰው ይጎዳዋል እንጂ ሃብቱ ባህሪን አያመጣለትም፡፡ ሃብት ባህሪ የሚጎድለውን ሰው ያስጨንቀዋል ወይም ያጠፋዋል እንጂ ሃብት ደስታን አይሰጥም፡፡  
አሁን ለባህሪው መለወጥ በትጋት የማይሰራ ሰው ሃብት ባገኝ እለወጣለሁ ብሎ ቢያስብ ይሞኛል፡፡
ጥበብን የሚያገኝ ሰው ምስጉን ነው፥ ማስተዋልንም ገንዘቡ የሚያደርግ፤ በወርቅና በብር ከመነገድ ይልቅ በእርስዋ መነገድ ይሻላልና። መጽሐፈ ምሳሌ 3፡13-14
2.     እውቀት
ብዙ ሰዎች ከዚህ በላይ እውቀት ቢኖራቸው ትልቅ ደረጃ የሚደርሱ ይመስላቸዋል፡፡ እውቀት የራሱ ድርሻ አለው፡፡ እውቀት የሚያደርጋቸው ነገሮች አሉ፡፡ እውቀት ግን ህይወትን አይለውጥም፡፡ ሰው ባወቀው እውቀት የሚያደርግው ነገር እንጂ ሰውን የሚለውጠው የሰው እውቀት በራሱ ምንም አያመጣለትም፡፡
ብዙ እውቀት ካለውና ምንም ነገር ከማያደረግበት ሰው ይልቅ ያለውን ትንሽ እውቀት በአግባቡ የሚጠቀም ሰው ይበልጥ ፍሬያማ ይሆናል፡፡
ከትምህርት እውቀት በላይ የህይወት ችሎታ ወይም /life skill/ ሰውን በህይወት ስኬታማ ያደርገዋል፡፡ ከእውቀት ሁሉ ይልቅ ከፈጠረን ከእግዚአብሄር ጋር እንዴት መኖር እንዳለብን የሚያስተምረን እግዚአብሄርን የመፍራት ጥበብ ይበልጣል፡፡  
ከዚህም ሁሉ በላይ፥ ልጄ ሆይ፥ ተግሣጽን ስማ፤ ብዙ መጻሕፍትን ማድረግ ፍጻሜ የለውም፥ እጅግም ምርምር ሰውነትን ያደክማል። የነገሩን ሁሉ ፍጻሜ እንስማ፤ ይህ የሰው ሁለንተናው ነውና፤ እግዚአብሔርን ፍራ፥ ትእዛዙንም ጠብቅ። እግዚአብሔር ሥራን ሁሉ የተሰወረውንም ነገር ሁሉ፥ መልካምም ቢሆን ክፉም ቢሆን፥ ወደ ፍርድ ያመጣዋልና። መጽሐፈ መክብብ 12፡12-14
3.     ዝና
ብዙ ሰዎች ለዝነኝነት ቀን ከሌሊት ይሰራሉ፡፡ ሰው ለዝነኝነት የሚሰራው እግዚአብሄር በምድር እንዲሰራ በሰጠው ጊዜና ጉልበት ነው፡፡ ሰው ዝና ለማግኘት ቀን ከሌሊት ከሚሰራ እግዚአብሄር የሰጠውን የህይወት ሃላፊነት ለመፈፀም ቢተጋ አስፈላጊ ከሆነ እግዚአብሄር ራሱ በራሱ መንገድ ዝነኛ ያደርገዋል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ለዝነኝነት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ ዝነኛ ሲሆኑ ግን ዝነኝነት ካስወጣቸው ወጪ አንፃር ያሰቡትን የዝነኝነት ጥቅም ገቢ ስለማያስገቡ በህይወታቸው ደስተኛ አይሆኑም፡፡
4.     ትዳር
ሁሉም ባትሆኑም ያላገቡ ብዙ ሰዎች ትዳር ቢኖራቸው ህይወታቸው የሚሟላ ይመስላቸዋል፡፡ ትዳር ሙሉ ሰዎች ለቤተሰብ ለመስጠት ለመባረክና ለመጥቀም ያላቸውን ነገር ይዘው የሚመጡበት ህብረት እንጂ ጎዶሎ ሰዎች ራሳቸውን ሊሞሉ የሚፍጨረጨሩበት ህብረት አይደለም፡፡ ትዳር የሙሉ ሰዎች የመስጫ የመባረኪያ የመጥቀሚያ መድረክ እንጂ ትዳር የህይወት ማሟያ አይደለም፡፡ ሚስቴ ወይም ባሌ ህይወቴን ይለውጣል ብሎ የሚጠብቅ ሰው ካለ ይሳሳታል፡፡ የሰውን ህይወት የሚለውጠው ለመለወጥ ያለው ፍላጎትና ለመለወጥ የእግዚአብሄርን ቃል ለመታዘዝ ከእግዚአብሄር ጋር አብሮ በትጋት መስራት እንጂ ለህይወት ለውጥ በሌላው ሰው ላይ መደገፍ አይደለም፡፡ ትዳር ጉድለታቸው እንዲሞላላቸው የሚፈልጉ የሁለት የጎዶሎ ሰዎች ህብረት ሳይሆን ትዳር በእግዚአብሄር ሙሉ የሆኑ ለትዳሩ አስተዋጽኦ ለማድረግ ለመስጠት ለመባረክና ለመጥወቀም የሚመጡ የሁለት ሰዎች ውህደት ነው፡፡
በትዳርረ ውስጥ መሆንም ወይም ደግሞ በትዳር ውስጥ አለመሆንም ህይወትን አይለውጥም፡፡ ህይወትን የሚለውጠው የእግዚአብሄርን ቃል መከተል ነው፡፡
ዳሩ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እናገራለሁ፤ ዘመኑ አጭር ሆኖአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌላቸው ይሁኑ፥ 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 7፡30
5.     የአገር ለውጥ
አንዳንድ ሰዎች ያለመለወጣቸው ምክኒያት ያሉበት አገር እንደሆነ ያስባሉ፡፡ ኢትዮጲያም ኑር ደቡብ አፍሪካ አሜሪካም ኑር እንግሊዝ አገሩ ራሱ የተለወጠን ሰው ይፈለጋል እንጂ አገሩ አንተን ሊለውጥ አይችልም፡፡ የህይወት ለውጥ በልብህ ውስጥ እንጂ በአገር ውስጥ የለም፡፡ ውስጥህ ከተለወጠ አገሩ ይሰራልሃል ፍሬያማም ያደርገሃል፡፡
በምድርም ቀድሞ በአብርሃም ዘመን ከሆነው ራብ በላይ ራብ ሆነ፤ ይስሐቅም ወደ ፍልስጥኤም ንጉሥ ወደ አቢሜሌክ ወደ ጌራራ ሄደ። እግዚአብሔር ተገለጠለት፥ እንዲህም አለው፦ ወደ ግብፅ አትውረድ፥ እኔ በምልህ ምድር ተቀመጥ እንጂ። ኦሪት ዘፍጥረት 2612
ይስሐቅም በዚያች ምድር ዘርን ዘራ፥ በዚያች ዓመትም መቶ እጥፍ አገኘ እግዚአብሔርም ባረከው። ኦሪት ዘፍጥረት 26፡12
ውስጠህ ካልተለወጠ በአመፅህ ከቀጠልክ አገሩ ይተፋሃል፡፡
ከእናንተ በፊት የነበሩ የአገሩ ልጆች ይህን ርኵሰት ሁሉ ሠርተዋልና፥ ምድሪቱም ረክሳለችና፤ ባረከሳችኋት ጊዜ ምድሪቱ ከእናንተ በፊት የነበረውን ሕዝብ እንደ ተፋች እናንተን እንዳትተፋችሁ። ኦሪት ዘሌዋውያን 18 18፡27-28
እንግዲህ ትቀመጡባት ዘንድ የማገባችሁ ምድር እንዳትተፋችሁ ሥርዓቴን ሁሉ፥ ፍርዴንም ሁሉ ጠብቁ፥ አድርጉትም። ኦሪት ዘሌዋውያን 20፡22
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa 
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ራዕይ #ምሪት #የእግዚአብሄርአጀንዳ #የእግዚአብሄርፈቃድ #ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #ለውጥ #የህይወትለውጥ #ዝና #ጌታ #ትዳር #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እውቀት #ሃበት #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment