Popular Posts

Follow by Email

Friday, April 6, 2018

የስግደት አደጋው

በእነዚህ ቀናት ከእግዚአብሄር ውጭ ለሰው ለመላእክት ለቅዱሳን ለሰማእታት ስግደት ይገባል አይገባም ስግደት ከተገባስ እስከምን ድረስ ነው ስግደት የሚገባው የሚለው ጥያቄ ሲያከራክር ቆይቶዋል፡፡
የዚህ ፅሁፍ አላማ የስግደትን አይነቶችና መጠን ለመተንተን ሳይሆን ከእግዚአብሔር ውጭ ያለ ስግደት ያለውን አደጋና ለምን ስግደት አደገኛ እንደሆነ ጥቂት ለማለት ነው፡፡
ስግደት ማለት እገዛልሃለሁ እታዘዝሃለሁ አንተ ጌታዬ ነህ ባንተ እታመናለሁ ማለት ነው፡፡ ስግደት ማለት አንተ ፈጣሪዬ ነህ እኔ ያንተ ነኝ ባንተ ተስፋ አደርጋለሁ ማለት ነው፡፡ ስግደት ማለት ለምንሰግድለት ነገር ራሳችንን አሳልፈን መስጠት ማለት ነው፡፡
በመፅሃፍ ቅዱስ ውስጥ ስግደትን በተመለከተ ለእግዚአብሄር መስገድ እንደሚገባ በብዙ ቦታዎች ተጠቅሶዋል፡፡
ትኩረታችንን የሚፈልጉ እንድንሰግድላቸው በየጊዜው የሚፈትኑ የሚማርኩን ካልሰገድክልኝ ብለው የሚያስፈራሩ ብዙ ነገሮች በአለም ላይ አሉ፡፡ ጉልበት ሁሉ መንበርከክ ያለበት ግን ለእግዚአብሄር ነው፡፡
እኔ ሕያው ነኝ፥ ይላል ጌታ፥ ጉልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል መላስም ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግናል ተብሎ ተጽፎአልና። ሮሜ 14፡11
በመፅሃፍ ቅዱስ ውስጥ የእግዚአብሄር ህዝብ ለእግዚአብሄር እንዲሰግዱ በብዙ ቦታዎች ታዞዋል፡፡ እግዚአብሄር ስለፈጠረን ስግደት እንደሚገባው መፅሃፍ ቅዱስ ያስተምራል፡፡
ኑ፥ እንስገድ ለእርሱም እንገዛ፤ በእርሱ ባደረገን በእግዚአብሔር ፊት እንበርከክ፤ መዝሙር 95፡6
በመፅሃፍ ቅዱስ ውስጥ የእግዚአብሄር ህዝብ ለእግዚአብሄር ብቻ እንጂ ለመልአክት እንዳይሰግዱ ታዞዋል፡፡
ልሰግድለትም በእግሩ ፊት ተደፋሁ። እርሱም፦ እንዳታደርገው ተጠንቀቅ፤ ከአንተ ጋር የኢየሱስም ምስክር ካላቸው ከወንድሞችህ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ፤ የኢየሱስ ምስክር የትንቢት መንፈስ ነውና አለኝ። ራእይ 19፡10
በመፅሃፍ ቅዱስ ውስጥ የእግዚአብሄር ህዝብ ለእግዚአብሄር ብቻ እንጂ እግዚአብሄርን ለሚመስል ነገር ስእል ወይም ምስል እንኳን እንዳይሰግዱ ታዞዋል፡፡
በላይ በሰማይ ካለው፥ በታችም በምድር ካለው፥ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ፥ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ። አትስገድላቸው፥ አታምልካቸውምም፤ ዘፀአት 20፡4-5
ስግደት ለእግዚአብሄር ለአምላክነቱ ክብር የምናሳይበት መንገድ ነው፡፡ በመፅሃፍ ቅዱስ እግዚአብሄር ሊከበር እንደሚገባ በብዙ ቦታዎች ተጠቅሶዋል፡፡
ለእግዚአብሔር ክብርን ይስጡ፥ ምስጋናውንም በደሴቶች ይናገሩ። ኢሳያስ 42፡12
አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ በልቤ ሁሉ አመሰግንሃለሁ፥ ለዘላለምም ስምህን አከብራለሁ፤ መዝሙር 86፡12
በመፅሃፍ ቅዱስ ከእግዚአብሄር በላይ ይሁን ከእግዚአብሄር እኩል ማንም እንዳይከበር በብዙ ቦታዎች ታዞዋል፡፡ እግዚአብሔር ከምንም ሰው ጋር ፣ ከማንም መላክእት ጋር ፣ ከየትኛውም ቅዱሳን ጋር አንደ አንዱ እንዲቆጠር አይፈልግም፡፡ እግዚአብሄር ታላቅ ነው፡፡  
እግዚአብሔርን ከእኔ ጋር ታላቅ አድርጉት፥ በአንድነትም ስሙን ከፍ ከፍ እናድርግ። መዝሙር 34፡3
በመፅሃፍ ቅዱስ እግዚአብሄር ክብሩን ለማንም እንደማይሰጥ ተመልክቶዋል፡፡  
እኔ እግዚአብሔር ነኝ ስሜ ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ፥ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም። ኢሳያስ 42፡8
በመፅሃፍ ቅዱስ እግዚአብሄር ክብሩን ለማንም ለስጋ ለባሽ እንደማይሰጥ ተመልክቶዋል፡፡ 
ለእግዚአብሔርም ክብር ስላልሰጠ ያን ጊዜ የጌታ መልአክ መታው በትልም ተበልቶ ሞተ። ሐዋሪያት 12፡23
በመፅሃፍ ቅዱስ እግዚአብሄር ክብሩን ለማንም መልአክ እንደማይሰጥ ተመልክቶዋል፡፡ 
እርሱም፦ እንዳታደርገው ተጠንቀቅ፤ ከአንተ ጋር ከወንድሞችህም ከነቢያት ጋር የዚህንም መጽሐፍ ቃል ከሚጠብቁ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ አለኝ። ራእይ 22፡9
ሰይጣን የወደቀው እንደእግዚአብሄር መመለክ ስለፈለገ ነው፡፡ ሰይጣን የሚፈልገው መመለክንና እንዲሰገድለት ነው፡፡
ደግሞ ዲያብሎስ እጅግ ረጅም ወደ ሆነ ተራራ ወሰደው፥ የዓለምንም መንግሥታት ሁሉ ክብራቸውንም አሳይቶ፦ ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ አለው። ማቴዎስ 4፡9
እግዚአብሄርን የሚያመልክና ለእርሱ የሚሰግድ ሰው ለሰይጣን አይሰግድም፡፡ ለእግዚአብሄር የማናመጣውን ማንኛውንም ስግደት የሚቀበለው ሰይጣን ነው፡፡ ለሰው ብንሰግድ ፣ ለመላእክት ብንሰግድ ፣ ለምስል ብንሰግድ ፣ ለዛፍም ብንሰግድ ፣ ለወንዝም ብንሰግድ ስግደቱን በተዘዋዋሪ የሚቀበለው ሰይጣን ነው፡፡ ሰው ለእግዚአብሄር እንዲሰግድ ሰይጣን አይፈልግም፡፡
ሰው ለእግዚአብሄር አይስገድ እንጂ ለምንም ነገር ቢሰግድ ሰይጣን ደስ ይለዋል፡፡ ሰው ለእግዚአብሄር ካልሰገደ በተዘዋዋሪ ለእርሱ እንደሚሰግድ ሰይጣን ያውቃል፡፡   
ዲያብሎስም፦ ይህ ሥልጣን ሁሉ ክብራቸውም ለእኔ ተሰጥቶአል ለምወደውም ለማንም እሰጠዋለሁና ለአንተ እሰጥሃለሁ፤ ስለዚህ አንተ በእኔ ፊት ብትሰግድ፥ ሁሉ ለአንተ ይሆናል አለው። ሉቃስ 4፡6-7
ትኩረታችሁ በእግዚአብሄር ላይ አይሁን እንጂ በምንም ነገር ላይ ቢሆን ሰይጣን ደስተኛ ነው፡፡ ትኩረታችሁ ከእግዚአብሄር ላይ ይነሳ እንጂ ትኩረታችንሁ ምንም ነገር ላይ ቢሆን ሰይጣን ተጠቃሚ ነው፡፡ ለእግዚአብሄር አትስገዱ እንጂ ለምንም ነገር ብትሰግዱ ሰይጣን ይጠቀማል፡፡ እግዚአብሄርን ብቻውን አትስገዱለት እንጂ ከምንም ነገር ጋር አብራችሁ ብትሰግዱለት ሰይጣን ግቡን ይመታል፡፡
የሰይጣን ግብ እግዚአብሄር ብቻውን እንዳይመልክ ነው፡፡ የሰይጣን ግብ እግዚአብሄር ከሌሎች ሰዎች ፣ ከሌሎች ቅዱሳን ፣ ከሌሎች መላእክት ጋር አብሮ እንደ አንዱ እንዲመለክ ነው፡፡ የሰይጣን ግንብ የእግዚአብሄርን ክብር በሰዎች ፣ በቅዱሳን ፣ በመላእክት ፣ በምስል መሸፈን ነው፡፡
እግዚአብሄር ደግሞ የሁሉም ፈጣሪ እና አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሄር እንደ አንዱ እንዲመለክ አይፈልግም፡፡ እግዚአብሄር ብቻውን መመለክ ነው የሚፈልገው፡፡ እግዚአብሄር ከምንም ከምንም ጋር እንዲቆጠር አይፈልግም፡፡ እግዚአብሄርን ብቻውን ካላመለካችሁት ከማንም ጋር አብራችሁ እንድታመልኩት አይፈልግም፡፡
እኔ እግዚአብሔር ነኝ ስሜ ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ፥ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም። ኢሳያስ 42፡8
ስለዚህ ነው በአዲስ ኪዳን ለእግዚአብሄር የሚሰግዱ ሰዎች በተወሰነ ቦታ ሳይገደቡ በእውነትና በመንፈስ ባሉበት ቦታ ለእግዚአብሄር እንደሚሰግዱለት መፅሃፍ ቅዱስ የሚያስተምረው፡፡
ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፤ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና፤ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል። ዮሃንስ 4፡23-24
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #እግዚአብሄር #አምልኮ #ስግደት #ጣኦት #መላእክት #መመካት #ቅዱሳን #ጌታ #ሰማእታት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #እምነት #ክብር #ፍቅር #ምስል #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ኦርቶዶክስ #ማርያም #አንድ #ብቻ #ሰይጣን 

No comments:

Post a Comment