እግዚአብሄር ፍቅር ነው፡፡ ሰው የተፈጠረው ፍቅር በሆነው በእግዚአብሄር ነው፡፡ ሰው የተፈጠረው ለፍቅር ነው፡፡ ሰው ዲዛይን የተደረገው ለፍቅር ህይወት ነው፡፡
ፍቅር ስለሰው መልካም ማሰብ መልካም መናገርና መልካም ማድረግ ነው፡፡
ሰው በፍቅር ሲኖር እግዚአብሄር የፈጠረውን አላማ ስለሚፈፅም ደስተኛ ይሆናል፡፡ ሰው በፍቅር ሲኖር እግዚአብሄር ስለሚረዳው በእግዚአብሄር እርዳታ መንገዱ ይቀልለታል፡፡
ሰው በጥላቻ ሲኖር ግን ህይወቱ ያልተነደፈበትንና ያልተሰራበትን ስራ ስለሚሰራ ህይወቱ ይጨልማል፡፡
ጥላቻ ከማንም በላይ የሚጎዳው የሚጠላውን ሰው ነው፡፡ እንዲያውም ጥላቻ ሌላውን ይገድልኛል ብሎ ራስ መርዝ እንደመጣጣት ነው የሚባለው፡፡
በጥላቻ የሚኖር ሰው በጨለማ ይሄዳል፡፡ በብርሃን አለሁ የሚል ወንድሙንም የሚጠላ እስከ አሁን በጨለማ አለ። ወንድሙንም የሚወድ በብርሃን ይኖራል ማሰናከያም የለበትም፤ ወንድሙን የሚጠላ ግን በጨለማ አለ፥ በጨለማም ይመላለሳል፥ የሚሄድበትንም አያውቅም፥ ጨለማው ዓይኖቹን አሳውሮታልና። 1ኛ ዮሐንስ 2፡9-11
ጥላቻ ከእግዚአብሄር አይደለም፡፡ በጥላቻም የሚጠቀመው ሰይጣን ብቻ ነው፡፡ የሰይጣን አላማ ሰውን መስረቅ ማረድና ማጥፋት ነው፡፡ ሰይጣን ከመስረቅ ከማረድና ከማጥፋት ሌላ አላማ የለውም፡፡ ሰይጣን ጥላቻ ውስጥ ካስገባን በቀላሉ አላማውን ይፈፅማል፡፡ ከጥላቻ ራሱን ያልጠበቀ ሰው ለዲያብሎስ ፈንታ ሰጥቶት ለምን ሰይጣን በህይወቴ ሰረቀ ፣ አረደና አጠፋ ማለት አይችልም፡፡
በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፥ ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት። ኤፌሶን 4፡27
ሰይጣን የመስረቅ የማረድና የማጥፋቱን አላማ የሚያሳካው በሰዎች ውስጥ ጥላቻን በመጨመር ነው፡፡ በሰው ውስጥ የጥላቻን ሃሳብ ካልጨመረ በስተቀር ሰይጣን ሊሰርቅ ሊያርድና ሊያጠፋ አይችልም፡፡ ሰይጣን ከጥላቻ ራሱን በሚጠብውቅ ሰው ህይወት ውስጥ እንዳች እድል ፈንታ አይኖረውም፡፡
ኢየሱስ የበደሉትን እንኳን ይቅር በማለት ህይወቱን ከጥላቻ ይጠብቅ ስለነበር ይህንን አለ፡፡
ከእንግዲህ ወዲህ ከእናንተ ጋር ብዙ አልናገርም፥ የዚህ ዓለም ገዥ ይመጣልና፤ በእኔ ላይም አንዳች የለውም፤ ዮሃንስ 14፡30
ሰይጣን በሰው ውስጥ ጥላን ከጨመረ ደግሞ የማያሰራው ክፋት የለም፡፡ ጥላቻ ላለበት ሰው መግደል ቀላል ነው፡፡ ስለዚህ ነው መፅጽሃፍ ቅዱስ ወንድሙን የሚጠላ ነፍሰ ገዳይ ነው የሚለው፡፡
እኛ ወንድሞችን የምንወድ ስለ ሆንን ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገርን እናውቃለን፤ ወንድሙን የማይወድ በሞት ይኖራል። ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፥ ነፍሰ ገዳይም የሆነ ሁሉ የዘላለም ሕይወት በእርሱ እንዳይኖር ታውቃላችሁ። 1ኛ የዮሐንስ መልእክት 3፡14-15
ማንንም ሰው እንድንጠላ አልተፈቀደልንም፡፡ ልንጠላው የሚገባው ሊሰርቅ ሊያርድና ሊያጠፋ የሚመጣውን ሰይጣንነ ብቻ ነው፡፡ እንድንጠላው የሚገባው ሰዎችን ክፋት የሚያሰራውን ሰይጣንን ብቻ ነው፡፡ ልንጠላው የሚገባው ውሸታምና የውሸት አባት የሆነውን በውሸት ሰዎችን የሚያጠላላውን በጥላቻ የሚያገዳድለውን ሰይጣንን ብቻ ነው፡፡
እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፥ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና። ዮሃንስ 8፡44
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ጥላቻ #ውሸት #ግድያ #ሰይጣን #ሊሰርቅ #ሊያርድ #ሊያጠፋ #ፍቅር #ምህረት #ይቅርታ #እምነት #ፀሎት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ
No comments:
Post a Comment